አቶ ፓውሎ ሩፊኒ፥ በሂሳባዊ ቀመር ሳይሆን በሰው ልጆች ላይ የተመሠረተ ግንኙነት እንደሚያስፈልግ ገለጹ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
የቫቲካን መገናኛዎች ጽሕፈት ቤት ተጠሪ አቶ ፓውሎ ሩፊኒ፥ ወደ ሙሉ የሰው ልጅ የመግባቢያ መንገድ እንደገና ለመመልስ የሚያስችለው የልብ ጥበብ እንደሆነ ገልጸው፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለዘንድሮው የዓለም የማኅበራዊ መገናኛ ቀን ያስተላለፉትን ጥሪ በብራዚል ማናውስ ከተማ ሲካሄድ ቆይቶ ሰኞ ነሐሴ 20/2016 ዓ. ም. ለተጠናቀቀው የአማዞን ቤተ ክርስቲያን ሁለተኛ ጠቅላላ ጉባኤ ለላኩት የቪዲዮ መልዕክታቸው መሠረት አድርገዋል።
የተከፋፈለውን ማኅበረሰብ አንድ ማድረግ
በስፔን ቋንቋ የተጻፈው የአቶ ፓውሎ ሩፊኒ መልዕክት፥ የባሕል ልዩነቶችን ጠብቆ በሕዝቦች መካከል አንድነትን ለማጎልበት የሚደረግ የእርስ በርስ ግንኙነት ወሳኝ እና አስፈላጊ መሆኑን አፅንዖት ሰጥቷል። አቶ ሩፊኒ እንደተናገሩት መግባባት የተከፋፈለውን አንድ ለማድረግ የሚያገለግል ሲሆን፥ እንደዚሁም የጋራ ስጦታ የሚነሳው በመናገር፣ በማዳመጥ እና ሌላውን በመረዳት ከሚገኝ ግንኙነት እንደሆነ ገልጸው፥ የጋራ ስጦታው ልዩነቶቻችንን በመሻር እርስ በእርሳችን በማገናኘት ሁሉም ነገር እንዴት እርስ በርስ እንደተገናኘ ያስረዳል ብለዋል።
በልብ ጥበብ የተቃኘ የሰው ልጅ ግንኙነት
አቶ ሩፊኒ አክለው እንደተናገሩት፥ “የተሻለ ዓለምን ለመገንባት የመገናኛ ብዙኃን የቅኝ ግዛት ወረራን የሚከላከል ሰብዓዊ ግንኙነት ያስፈልጋል” ብለዋል። “ለክፉ የማይገዛ ልዩ ትረካ እና መልካም የመገናኛ ዘዴ ያስፈልገናል ያሉት አቶ ሩፊኒ፥ በቴክኖሎጂ ወይም በሂሳባዊ ቀመር ላይ የተመሠረተ ሳይሆን የጋራ ውይይትን፣ እርስ በርስ የመገናኘት ባሕልን እና የጋራ መኖሪያ ምድራችንን መንከባከብን የሚያበረታታ እና በሰው ልጅ ላይ የተመሠረተ ሥርዓት እንደሚያስፈልግ የተናገሩትን የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስን መልዕክት አስተጋብተዋል።
መንፈሳዊ ዕይታው
በማደግ ላይ በሚገኙ የዲጂታል ሥርዓቶች እና በሰው ሠራሽ አስተውሎት “አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ” ፊት ለፊት ከራስ ወዳድነት የተነሳ የተከፋፈልነውን የሰውን ልጅ ወደ አንድነት ለመመለስ መንፈሳዊ ዕይታ ያለው ግንኙነት እና ቀጣይነት ያለው ትምህርት እንዲሰጥ የሚያግዝ የጋራ ኃላፊነት እንዲኖር በድጋሚ ጠይቀዋል።
የአማዞን አካባቢ አገራት ጉባኤ “CEAMA”
የአማዞን አካባቢ አገራት ጉባኤ “CEAMA” የአማዞን አካባቢ አገራት ልዩ የጳጳሳት ሲኖዶስ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በጥቅምት ወር 2019 ዓ. ም. በቫቲካን ከተካሄደ በኋላ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ 2020 ዓ. ም. መመሥረቱ ይታወሳል። ጉባኤው በአኅጉር አቀፍ እና በዓለም አቀፍ ደረጃ በተለያዩ የቤተ ክርስቲያን ማኅበራዊ እና አካባቢያዊ ውጥኖች መካከል ግንኙነት በመፍጠር ከሲኖዶሱ የተገኙት በርካታ ሃሳቦች ተግባራዊ እንዲሆን አስተዋጽኦን አበርክቷል።
በብራዚል ማናውስ የተካሄደው ስብሰባ፥ ከመስከረም 22 እስከ ጥቅምት 17/2017 ዓ. ም. በቫቲካን ሊካሄድ ከታቀደው የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ ሁለተኛ ጉባኤ ቀደም ብሎ ከብራዚል፣ ከቦሊቪያ፣ ከኮሎምቢያ፣ ከኤኳዶር፣ ከጉያና፣ ከፔሩ፣ ከሱሪናም፣ ከቬነዙዌላ እና ከፈረንሳይኛ ተናጋሪ የአማዞን አካባቢ አገራት የተወጣጡ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ተወካዮችን በማሰባሰብ፥ “ኢየሱስ ክርስቶስ የአማዞን አካባቢ አገራት ሕዝቦችን አንድነትን፣ ተልዕኮን እና ተሳትፎን ያሳያል” በሚል መሪ ሃሳብ ላይ ተወያይተዋል።
ተሳታፊዎቹ በአራት ቀናት ውይይታቸው በአማዞን አካባቢ አገራት ውስጥ ባለው ወቅታዊ ሁኔታ ላይ በማትኮር ተወያይተው፥ ምስክርነቶችን እና መንፈሳዊ ንግግሮችን በማዳመጥ ሃሳብ ተለዋውጠዋል።