ብጹዕ ካርዲናል ፓሮሊን ከሩሲያው የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽነር ጋር መወያየታቸው ተገለጸ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ ብፁዕ ካርዲናል ፒየትሮ ፓሮሊን እና የሩሲያ ፌዴሬሽን የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽነር ወ/ሮ ታቲያና ሞስካልኮቫ ያደረጉት ውይይት ግንባር ቀደም ርዕሥ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶችን ማስጠበቅ የሚል እንደ ነበር ታውቋል።
የቅድስት መንበር ጋዜጣዊ መግለጫ ጽሕፈት ቤት ረቡዕ መስከረም 8/2017 ዓ. ም. በሰጠው መግለጫ፥ የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ ብጹዕ ካርዲናል ፔትሮ ፓሮሊን ከሩሲያ ፌዴሬሽን የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽነር ወ/ሮ ታቲያና ሞስካልኮቫ ጋር ሰኞ መስከረም 6/2017 ዓ. ም. የቪዲዮ ኮንፈረንስ ማድረጋቸውን አስታውቋል።
ሁለቱን የዩክሬን ካኅናት ለማስፈታት ወ/ሮ ታቲያና ሞስካልኮቫ ላደረጉት ጥረት ብጹዕ ካርዲናል ፓሮሊን ምስጋና ማቅረባቸውን መግለጫው ገልጾ፥ በዓለም አቀፍ ስምምነቶች መሠረት አሁን ካለው ግጭት አንፃር መሠረታዊ የሰብዓዊ መብቶችን በማስጠበቅ አስፈላጊነት ካርዲናል ፓሮሊን አጽንኦት መስጠታቸውን መግለጫው አስታውቋል።
በተጨማሪም ሰብዓዊ ጉዳዮችን በተመለከቱ ሌሎች ጉዳዮች ላይ መወያየታቸውን በተለይም ሩሲያ ውስጥ በእስር ለሚገኙ የዩክሬን ወታደሮች ስለሚደርገው ዕርዳታ እና በሩሲያ እና በዩክሬን ውስጥ በታሰሩ ወታደሮች መካከል የሚደረግ የምርኮኞች የጋራ ልውውጥን ጠቅሰው መወያየታቸውን መግለጫው አክሎ አስታውቋል።