ፈልግ

ጃካርታ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስን ተቀብላ እያስተናገደች ነው ጃካርታ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስን ተቀብላ እያስተናገደች ነው  (AFP or licensors)

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት በኢንዶኔዥያ ጉብኝት እያደረጉ ባለበት ወቅት የተለያዩ ሃይማኖቶች መሃል ውይይት ይደረጋል ተባለ

ኢንዶኔዢያ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስን ተቀብላ እያስተናገደች ባለችበት ወቅት የሃይማኖት ተቋማት ምክክር ጽ/ቤት ሃላፊ የሆኑት ኢንዶኔዥያዊ ካህን አባ ማርከስ ሶሎ ስለ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ 45ኛ የውጪ ሐዋርያዊ ጉዞ አስፈላጊነትን አብራርተዋል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ ወደ እስያ እና ኦሺኒያ አህጉራት ውስጥ ወደሚገኙት አራት ሀገራት በሚያደርጉት 45ኛው የውጪ ሐዋርያዊ ጉዞ 87 በመቶው ህዝቧ ሙስሊም የሆነባት ኢንዶኔዢያን ለመጎብኘት ነሃሴ 28 ቀን 2016 ዓ.ም. ጃካርታ ገብተዋል።

ኢንዶኔዥያ ከዚህም ባለፈ በርካታ ሃይማኖቶች ጥልቅ በሆነ ትብብር የሚኖሩባት እንዲሁም የተለያየ ዘር፣ ሃይማኖት እና እምነት ያላቸው ህዝቦች ተቻችለው የሚኖሩባት እና የ “ፓንካ-ሲላ” መርሆዎች መሰረት በሆኑት ስምምነት፣ መተሳሰብ እና ከሌሎች ጋር ተከባብሮ መኖር የሚተገበርባት ሃገር ናት።

በውቧ የኢንዶኔዥያ ደሴት ፍሎሬስ ከተማ የተወለዱት አባ ማርከስ ሶሎ ኪውታ የሃይማኖት ተቋማት ውይይት ጽ/ቤት ሃላፊ ሲሆኑ፥ በሃይማኖት ተቋማት፥ በተለይም በካቶሊኮች እና በእስያ እና በፓስፊክ ውቅያኖሶች መካከል ባሉ ሙስሊሞች ጋር በመስራት ሰፊ ልምድ ያላቸው ናቸው።

በኢንዶኔዥያ ውስጥ የሃይማኖቶች ውይይት
ከርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ሐዋርያዊ ጉዞ በፊት በተደረገ ቃለ ምልልስ አባ ማርከስ በብዝሃነቱ የሚታወቀውን በሀገራቸው ያለውን የሃይማኖት ተቋማት ውይይቶች ማዕከላዊነትን አጽንኦት ሰጥተው በመግለጽ፥ “ኢንዶኔዥያ በጣም ብዙ ቁጥር ያለው ማህበረሰብ ያለባት እና ሰፊ ሀገር ነች” ሲሉ አብራርተዋል።

የሀገሪቱን አስደናቂ ብዝሃነት ያነሱት ካህኑ፥ 17,000 ደሴቶች እና እልፍ አእላፍ ብሄረሰቦች፣ ሃይማኖቶች እና ቋንቋዎች ያሏት ሃገር እንደሆነች ገልጸዋል። ይህ ብዝሃነት እንደ “የሕይወት ውይይት፣ የትብብር ውይይት፣ የመንፈሳዊ ልውውጦች ውይይት እና የሥነ መለኮት ውይይት” የመሳሰሉ የተለያዩ ይዘቶችን የሚያጠቃልል በሃይማኖታዊ ውይይቶች ውስጥ በየዕለቱ መሳተፍን ይጠይቃል ካሉ በኋላ፥ “እንዲሁም ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዮሃንስ ጳውሎስ ዳግማዊ በትክክል እንደተናገሩት የልብ ለልብ ንግግሮችም ጭምር እንዳሉና፥ እነዚህ ሁሉ ንግግሮች በየቀኑ በኢንዶኔዥያ ውስጥ ይከናወናሉ” ብለዋል። 

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ በኢንዶኔዢያ ከሚያደርጉት ጉብኝቶች ውስጥ አንዱ መርሃግብር በጃካርታ በሚገኘው ኢስቲቅላል መስጊድ የጋራ መግባባትን እና ሰላምን የመፍጠር አስፈላጊነትን የሚያበረታታ የጋራ ሰነድ ላይ መፈረምን ያካትታል።

አባ ማርከስ አክለውም የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳቱ በቦታው መገኘት የሃይማኖት ተቋማት ውይይት አስፈላጊነትን አጉልቶ ከማሳየቱም ባለፈ “በተሻለ መንገድ እንድንሠራ መነሳሳትን ይፈጥርልናል” ካሉ በኋላ፥ “የሃይማኖት ተቋማት ውይይት መርሃ ግብር የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ የኢንዶኔዥያ ጉብኝት ዋና ማዕከል በመሆኑ በግሌ በጣም ደስተኛ ነኝ” ብለዋል።

ፓንካሲላ “Pancasila” ፡ የኢንዶኔዥያ አንድነት መሠረት
በኢንዶኔዥያ በሃይማኖቶች መካከል ስምምነትን ለማምጣት ቁልፍ ሚና የሚጫወተው የ ‘ፓንካሲላ’ ጽንሰ-ሀሳብ ሲሆን፥ የኢንዶኔዢያ ህዝባዊ እና መሠረታዊ የፍልስፍና ፅንሰ-ሀሳብን የሚገልጽ ጥንታዊ የህንድ ቃል ነው።

አባ ማርከስ እንደገለጹት ፓንካሲላ በሀገሪቱ መስራች አባት በሆኑት ሱካርኖ እ.አ.አ. በ1945 የተመሰረተ እና አምስት ምሰሶዎች ያሉት ሲሆን፥ እነሱም በአንድ አምላክ ማመን፣ ማህበራዊ ሰብአዊነት፣ የኢንዶኔዥያ አንድነት፣ ማህበራዊ ዲሞክራሲ እና ማህበራዊ ፍትህ የሚባሉት እንደሆነ አስረድተው፥ “ፓንካሲላ ማለት አምስት ምሰሶዎች ማለት ሲሆን፥ የሀገሬው ህዝብ እና የመንግስት መሰረታዊ የፍልስፍና መሰረታችን ሲሆን፥ በሃገራችን ህገ-መንግስት ውስጥም የተካተተ ነው” ብለዋል።

እነዚህ ምሰሶዎች የሀገሪቱን አስተዳደር ብቻ ሳይሆን፥ ሃይማኖታቸውም ሆነ ጎሣቸው ምንም ይሁን ምን በኢንዶኔዥያውያን መካከል የጋራ ማንነትን ያበረታታል ብለዋል።

አባ ማርከስ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ እነዚህን መርሆዎች እንደሚያደንቁ በመጥቀስ፥ “እርግጠኛ ነኝ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ እሳቸው ከሚከተሉት መንገድ ጋር ተመሳሳይ ስለሆነ ይሄንን ያደንቃሉ” በማለት አመልክተዋል።

በሃይማኖቶች መካከል አብሮ የመኖር ተግዳሮቶች
ኢንዶኔዥያ ብዙ ጊዜ በሃይማኖቶች መካከል የተሳካ አብሮ የመኖር ሞዴል ተደርጋ የምትጠቀስ ሃገር ብትሆንም፣ አሁን አሁን አለመቻቻል እና ሃይማኖታዊ ጽንፈኝነት እየጨመረ የመጣ ተግዳሮት መሆኑን አባ ማርከስ አምነዋል።

“በርካታ ሃይማኖቶችን የሚከተሉ ብዝሃ-ማህበረሰቦች ባሉባት እንደ ኢንዶኔዢያ ያሉ ሃገራት ውስጥ መኖር ሁልጊዜ ቀላል አይደለም” ሲሉ የገለጹት ካህኑ፥ እንደ ናህድ-ላቱል ኡላማ እና መሃመድያ ባሉ ድርጅቶች የተወከሉት የኢንዶኔዥያ ሙስሊሞች በአብዛኛው ግልጽ አስተሳሰብ እና አካታች ተፈጥሮአዊ ባህሪ ያላቸው ቢሆንም፥ የአካባቢ ባህሎች ውህደትን የሚቃወሙ እና መከፋፈልን የሚያበረታቱ በህብረተሰቡ ውስጥ ያሉ አንዳንድ አካላት ግን አሉ በማለት አብራርተዋል።

የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ ጉብኝት ወሳኝ በሆነ ወቅት ላይ የተደረገ መሆኑን ጠቁመው፣ የመቻቻልና የአንድነት እሴቶችን ለማጠናከር ዕድል ይሰጣል ብለዋል።

የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ሚና
የካቶሊክ ማህበረሰብ በአከባቢው አናሳ ቢሆንም፣ በኢንዶኔዥያ የምትገኘው የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን “በጣም ሕያው እና ንቁ ነች” ያሉት አባ ማርከስ፥ አንዳንድ የቤተክርስቲያኒቷ አገልግሎቶች እና ኩነቶች ግን ብዙ ጊዜ ከቁጥር ባለፈ ምዕመን እንደሚጥለቀለቁ ገልጸዋል።

                                  “አብያተ ክርስቲያናት ሁል ጊዜ በጣም ትንሽ ናቸው!”

በቦርንዮ ደሴት ላይ በምትገኘው በአዲሱ የኑሳንታራ ዋና ከተማ እየተገነባ የሚገኘው ትልቅ እና ማራኪ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ግንባታም ይህንኑ እውነታ ይመሰክራል ብለዋል።

በተጨማሪም በጃካርታ የሚገኘው የእመቤታችን ቅድስት ማሪያም ካቴድራል በጃካርታ ከሚገኘው የከተማዋ ትልቁ መስጊድ ትይዩ እንደሚገኝም ጠቁመው፥ ይህ ቅርበት እና “በወዳጅነት ድልድይ” አማካይነት በካቴድራሉና በመስጊዱ መካከል ያለው አካላዊ ግንኙነት የሃይማኖት ወንድማማችነት እና የመከባበር ምልክት ሆኖ ያገለግላል ብለዋል።

አባ ማርከስ ይሄንን አስመልክተው “ይህ በጣም ቆንጆ ነገር ነው፣ እናም ይህን ተነሳሽነት በጣም አደንቃለሁ፣ በጃካርታ የሚገኙትን የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ካቴድራል እና መስጊድ ለማገናኘት ድልድይ ማዘጋጀት ወንድማማችነትን፣ መቻቻልን እና የኢንዶኔዥያን የአንድነት ታሪክ ያጎለብታል” ብለዋል።

የሃይማኖታዊ ውይይት ጽ/ቤት ሥራ
በሃይማኖት ተቋማት ውይይት ጽ/ቤት ውስጥ የአባ ማርከስ ሚና በዓለም ዙሪያ ካሉ የሃይማኖት ድርጅቶች ጋር ግንኙነት መፍጠርን ያካትታል። ሆኖም ኢንዶኔዢያ ውስጥ የሚደረጉ አንዳንድ የሃይማኖታዊ እንቅስቃሴዎች ውስብስብነት በአገሪቱ ውስጥ ካሉ የሙስሊም ድርጅቶች ጋር አንድ ወጥ ትብብር ለመፍጠር ተግዳሮቶችን እንደፈጠረ አስረድተዋል።

እነዚህ ፈተናዎች ቢኖሩም ጽ/ቤቱ እና ቅድስት መንበር ከኢንዶኔዥያ ሙስሊሞች ጋር አወንታዊ ግንኙነት እንዳላቸው በማረጋገጥ፥ “ከብዙ ዓመታት በፊት አንዳንድ ወሳኝ የኢንዶኔዥያ ሰዎች በቫቲካን ከሚገኘው ጳጳሳዊ የሃይማኖት ተቋማት ውይይት ምክር ቤት ጋር ጥሩ ግንኙነት መሥርተው ስለነበር በአንዳንድ ውይይቶች ላይ እንዲሳተፉ እና ወደ ዓለም አቀፍ ስብሰባዎች ላይ እንዲገኙ አዘውትረን እንጋብዛቸዋለን ካሉ በኋላ፥ እነሱም መጥተው በደስታ ይሳተፉ ነበር፥ ይህም በሃይማኖቶች መካከል የሚደረግ ውይይት የሕይወታችን አንዱ አካል መሆኑን ለማረጋገጥ ብቻ ነው ብለዋል።

ጉብኝቱ ተስፋ ሰጪ ነው
አባ ማርከስ እንደገለጹት ኢንዶኔዢያ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳትን ተቀብላ እያስተናገደች ባለችበት ወቅት፥ ብጹእነታቸው በሀገሪቱ ውስጥ ባለው የበለጸገ የባህል እና የሃይማኖቶች አንድነት በእጅጉ እንደሚደነቁ ያላቸውን እምነት በመግለጽ፥ “ብጹእነታቸው በጉብኝታቸው ወቅት የተለያዩ ሰዎችን ያያሉ፣ የፊት መሸፈኛ የለበሱ ሴቶችን እና የተለያየ አይነት ልብስ የለበሱ ሙስሊሞችን እንዲሁም በርካታ ቁጥር ያላቸው ቡድሂስቶችን እና ሂንዱዎችን ያያሉ፥ ይህ በጣም አስገራሚ እና የሚያምር ነገር ነው” ሲሉ ይህ ጉብኝት ከመደበኛው ጉብኝትም በላይ እንደሆነ እና ሀገሪቱ በሃይማኖቶች መካከል መግባባት እና አንድነት ለመፍጠር ያላትን ቁርጠኝነት የሚያረጋግጥ እንደሆነ ገልጸዋል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ “ሁልጊዜ ለሰላምና ስምምነት፣ ፍትህ እና የአብሮ መኖር እሴቶች እንዲጠነክሩ ይታገላሉ” ያሉት አባ ማርከስ፣ ከጉብኝቱ የሚያገኙት ልምድ በጥልቅ እንደሚነካቸው ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።

አባ ማርከስ በመጨረሻም ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት በኢንዶኔዥያ ውስጥ ካሉት የሁሉም የሃይማኖት ተቋማት ሰዎች ጋር እንዲሁም በብጹእነታቸው ብዙ ጊዜ አጽንዖት የሚሰጠውን የመግባባት ባህልን የሚያበረታታውን እና በአንድነት ለመኖር እርስ በርስ መገናኘት መርህ ያለውን የ ‘ሲላ-ቱራህሚ’ ልምምድን ሙሉ በሙሉ ከተቀበለ ህዝብ ጋር ተገናኝተው ይወያያሉ ተብሎም ይጠበቃል ብለዋል።
 

04 September 2024, 14:59