ካርዲናል ሆሌሪች፥ ካቶሊክ ምዕመናን እምነት የጣሉባትን ቤተ ክርስቲያን እንደሚያገኙ ገለጹ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
ብጹዕ ካርዲናል ሆሌሪች ለዜና አገልግሎቱ ባደረጉት ገለጻ፥ ካቶሊክ ምዕመናን እምነት የጣሉባትን ቤተ ክርስቲያን እንደሚያገኙ ተናግረው፥ በቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ ፍሬዎች በዓለም አቀፍ ደረጃ በካቶሊክ ምዕመናን የዕለተ ዕለት ሕይወት ላይ ተጽዕኖ በማሳደር እንደሚያበረታቷቸው አስረድተዋል።
በዓለም ዙሪያ የሚገኙ ካቶሊካዊ ምዕመናን በጥምቀት በተቀበሉት ጸጋ አማካይነት በየቀኑ ተስፋ የሚያደርጉባትን፣ ተሰጥኦአቸው፣ ስጦታቸው እና የሕይወት ልምዳቸው የሚገኝባትን ቤተ ክርስቲያን እንደሚያገኟት ተናግረዋል።
ብፁዕ ካርዲናል ዣን ክላውድ ሆሌሪች ቅዱስ ሲኖዶስ በሲኖዶሳዊነት ላይ ያደረገው ጉባኤ የማጠቃለያ መስዋዕተ ቅዳሴ ሥነ-ሥርዓት ቀደም ብለው ቅዳሜ ጥቅምት 16/2017 ዓ. ም. ጸድቆ የቀረበውን የጉባኤውን የመጨረሻ ሠነድ በማስመልከት ከቫቲካን መገናኛ ብዙኃን ጋር ውይይት አድርገዋል።
የሲኖዶሱ አካሄድ በሂደት የሚለካ መሆኑን የገለጹት ብፁዕ ካርዲናል ዣን ክላውድ ሆሌሪች፥ በሲኖዶሳዊነት ላይ ሲደረግ የቆየው ውይይት ከሦስት ዓመት በፊት ማለትም እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ2021 መጀመሩን አስታውሰው የ2023 እና 2024 የጳጳሳት ሲኖዶስ ጉባኤ የሂደቱ የመክፈቻ ምዕራፍ ብቻ እንደ ነበሩ አስረድተዋል።
ከዚህ በኋላ ያለው የማሰላሰል ሂደት እንዲቀጥል ለማድረግ ሠነዱን ለርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እንደሚያቀርቡት የገለጹት ብፁዕ ካርዲናል ሆሌሪች፥ ቅዱስነታቸው በተወሰነ መልኩ የጉባኤውን ፍሬ በየአገራቱ ለሚገኙት ቤተ ክርስቲያናት አሳልፈው የሚሰጡ በመሆኑ ይህ 16ኛው የጳጳሳት ሲኖዶስ ጠቅላላ ጉባኤ የጠናቀቀ ቢሆንም ነገር ግን ሂደቱ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።
“ምናልባት ምዕመናን በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የሚታዩ ለውጦችን ወዲያው ላያዩ ይችላሉ” ያሉት ብፁዕ ካርዲናል ሆሌሪች፥ ምክንያቱም ለውጦች ጊዜ እንደሚያስፈልጋቸው እና መንፈስ ቅዱስም ልባችንን ሊለውጥ ጊዜ ያስፈልገዋል ሲሉ አስረድተዋል።
ነገር ግን ምዕመናን የጥምቀት ጸጋን ያገኙ በመሆናቸው ከጊዜ በኋላ ተስፋ ያደረጉባትን፣ አስፈላጊ የሆኑባትን፣ ተሰጥኦአቸው፣ ስጦታቸው እና የሕይወት ልምዳቸው አስፈላጊ የሆኑባትን ቤተ ክርስቲያን ከጊዜ በኋላ እንደሚያገኙ ተናግረዋል።
“ምዕመናን የእግዚአብሔር ቅዱስ ሕዝቦች ናቸው” ያሉት ብጹዕነታቸው፥ በጥምቀት እና በሜሮን ምስጢራት በኩል የተቀበሉት የወንጌል ተልዕኮ ግዴታ እንዳለባቸው ገልጸው፥ እንደ ቤተ ክርስቲያን አባልነታችን ይህን ተልዕኮ በቁምስናዎች፣ በትናንሽ መንፈሳዊ ማኅበራት፣ በሀገረ ስብከት እና በሌሎች የጋራ አገልግሎቶች በኩል አብረን እንፈጽማለን ብለዋል።
የ16ኛ ጠቅላላ የብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ የመረጃ ክፍል ሃላፊ ብጹዕ ካርዲናል ዣን ክሎድ ሆሌሪች በዚህ የሲኖዶስ ጉባኤ መሳተፍ መቻላቸው እንዳስደሰታቸው እና ክብርን እንዳጎናጸፋቸው ገልጸው፥ ከሲኖዶሱ ያገኙትን አወንታዊ ተሞክሮ ሁሉም ሰው እንዲያገኝ የሚል ምኞት እንዳላቸው ለቫቲካን የዜና አገልግሎት ገልጸዋል።