ፈልግ

የር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ መልዕክተኛ ብጹዕ ካርዲናል ማቴዎ ዙፒ ሞስኮ ውስጥ መስዋዕተ ቅዳሴን ሲካፈሉ  የር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ መልዕክተኛ ብጹዕ ካርዲናል ማቴዎ ዙፒ ሞስኮ ውስጥ መስዋዕተ ቅዳሴን ሲካፈሉ   (ANSA)

የር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ልዩ የሰላም መልዕክተኛ ብጹዕ ካርዲናል ማቴዎ ዙፒ ለሥራ ጉብኝት ሞስኮ ደርሰዋል

የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ልዩ የሰላም መልዕክተኛ የሆኑት ብፁዕ ካርዲናል ማቴዎ ዙፒ ሰኞ ጥቅምት 4/2017 ዓ. ም. ወደ ሩሲያ በመጓዝ ሁለተኛ ጉብኝታቸውን በሞስኮ ጀምረዋል። ብጹዕነታቸው ወደ ሥፍራው የተጓዙት በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የተሰጣቸው ተልዕኮ አካል የሆነውን፥ የዩክሬን ሕጻናትን ከቤተሰቦቻቸው ጋር እንዲገናኙ ለማድረግ እና ሁለቱ አገራት የጦር እስረኞቻቸውን የሚለዋወጡበትን መንገድ ለማመቻቸት መሆኑ ታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የጣሊያን ካቶሊክ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዝዳንት እና የቦሎኛ ከተማ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ ካርዲናል ማቴዎ ዙፒን በሰኔ ወር 2015 ዓ. ም. ልዩ መልዕክተኛ አድርገው መሰየማቸው የሚታወስ ሲሆን፥ የሞስኮ ጉብኝታቸው ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የሰላም መልዕክተኛነት ተልዕኮ አካል መሆኑን የቅድስት መንበር መግለጫ ክፍል ዳይሬክተር አቶ ማቴዎ ብሩኒ ገልጸዋል።

ብፁዕ ካርዲናል ማቴዎ ዙፒ በዚህ ጉብኝታቸው ከሩሲያ ባለስልጣናት ጋር ተገናኝተው የዩክሬን ሕጻናት ከቤተሰቦቻቸው ጋር እንዲቀላቀሉ እና አገራቱ እስረኞቻቸውን እንዲለዋወጡ ለማድረግ የሚያግዙ ተጨማሪ ጥረቶችን እንደሚገመግሙ እና ይህም ብዙ ተስፋ የተደረገበትን ሰላም ለማምጣት በማሰብ መሆኑን የቅድስት መንበር መግለጫ ክፍል ዳይሬክተር አቶ ማቴዎ ብሩኒ አስረድተዋል።

ቀደም ሲል የተደረጉ የሰላም ጥረት ጉብኝቶች 
የር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ልዩ የሰላም መልዕክተኛ ብጹዕ ካርዲናል ማቴዎ ዙፒ በዩክሬን ከግንቦት 28-29/2015 ዓ. ም. ድረስ ጉብኝት በማድረግ ከአገሪቱ ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዘሌንስኪ እና ሌሎች ከፍተኛ የመንግሥት ባለስልጣናት ጋር ተገናኝተው መወያየታቸው ይታወሳል። ብጹዕነታቸው በውይይታቸው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለዩክሬን ሕዝብ ያላቸውን አሳቢነት ገልጸው፥ የጦርነቱ ተሳታፊ አካላት ለውይይት ቅድሚያን እንዲሰጡ እና ለጦርነቱ ፍትሃዊ መፍትሄን በመፈለግ ወደ ጋራ መግባባት መድረስ አስፈላጊ እንደሆነ እና የሕዝቡን ስቃይ ማቃለል፣ በሁለቱ ወገኖች መካከል መተማመንን መልሶ በመገንባት ወደ እርቅ ለመድረስ በሚያግዙ እርምጃዎች ላይ ለመወያየት ዕድል መስጠት አስፈላጊ መሆኑን አፅንዖት መስጠታቸው ይታወሳል።

የቅዱስነታቸው ልዩ የሰላም መልዕክተኛ ብጹዕ ካርዲናል ማቴዎ ዙፒ በሞስኮ ከሰኔ 21 – 22/2015 ዓ. ም. ጉብኝት በማድረግ በሩስያ እና በዩክሬን መካከል በመካሄድ ላይ ለሚገኘው ጦርነት ሰላማዊ መፍትሄን ለማግኘት የሚደረጉ ጥረቶችን ለማበረታታት እና በአገራቱ መካከል ለሚታየው አሳዛኝ ሁኔታ መፍትሄን በማግኘት ወደ ፍትሃዊ ሰላም የሚያመሩ መንገዶችን ለማግኘት የሚረዱ ተስፋዎችን ለማጠናከር መወያየታቸው ይታወሳል።

ብፁዕ ካርዲናል ማቴዎ ዙፒ በቅዱስነታቸው የተሰጣቸውን የሰላም ተልዕኮ ለማስቀጠል በአሜሪካ ከሐምሌ 10-12/2015 ዓ. ም. ድረስ የሦስት ቀናት ጉብኝት ማድረጋቸው የሚያወስ ሲሆን በዚህ ጉብኝታቸው ከፕሬዚዳንት ጆ ባይደን እና ከኮንግረስ አባላት ጋር ተገናኝተው በጦርነት የተጎዳውን የዩክሬን ሕዝብ ስቃይ በማቃለል ወደ ሰላም ጎዳና ለማምጣት የሚደረጉ ጥረቶችን ለማጠናከር መወያየታቸው ይታወሳል። በተጨማሪም ወደ ሩሲያ የተወሰዱትን የዩክሬን ሕጻናት ለመመለስ ቅድስት መንበር በምታደርገው ጥረት ላይም ተወያይተዋል።

የር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ልዩ የሰላም መልዕክተኛ ብፁዕ ካርዲናል ማቴዎ ዙፒ በቻይና ከመስከረም 2-4/2016 ዓ. ም. ድረስ ባደረጉት ጉብኝት በቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአውሮፓ እና የሩስያ ጉዳዮች ልዩ ተወካይ ከሆኑት ሊ ሁይ ጋር ተገናኝተው መወያየታቸው ይታወሳል። የብጹዕነታቸው ጉዞ ዓላማ በዩክሬን ውስጥ ያለውን ውጥረት ለማርገብ የሚያግዝ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስን ሃሳብ ለአገሪቱ ባለስልጣናት ለማድረስ እንደነበር ይታወሳል። ብጹዕ ካርዲናል ማቴዎ ዙፒ በቤጂንግ ያደረጉት ጉብኝት ሰብዓዊ ተነሳሽነቶችን እና ወደ ፍትሃዊ ሰላም የሚያመሩ መንገዶችን ለመደገፍ ተጨማሪ እርምጃ እንደሚሆን ቅድስት መንበር መግለጿ ይታወሳል። ብጹዕ ካርዲናል ማቴዎ በበኩላቸውም፥ “የብዙ ሰዎች ጸሎት አስቸጋሪ የሆነውን የሰላም ጥረት በድል እንድወጣው ያግዘኛል” ማለታቸው ይታወሳል።
 

15 October 2024, 16:19