ቫቲካን በግጭት አካባቢዎች በሰላማዊ ሰዎች ላይ የሚፈጸም ጥቃት ተቀባይነት የለውም ስትል አስታወቀች
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
መካከለኛው ምሥራቅን እና ዩክሬንን ጨምሮ በመላው ዓለም እየተከሰቱ ባሉ ግጭቶች መካከል ዓለም አቀፍ የሰብዓዊነት ሕግን (IHL) ስልታዊ በሆነ መልኩ መጣስን እንደምታወግዘው እና ሰላማዊ ዜጎችን ያለ ልዩነት ማጥቃት ከሥነ-ምግባር አኳያ ተቀባይነት እንደሌለው ቅድስት መንበር ገልጻለች።
በጦርነት የተጨፈጨፉ ዜጎች እንደ “ያልታቀደ ጥቃት” ሰለባነት ሊቆጠሩ አይችሉም!
በጄኔቫ ስዊዘርላንድ በተካሄደው 34ኛ የቀይ መስቀል እና ቀይ ጨረቃ ዓለም አቀፍ ጉባኤ ላይ የተገኙት የቫቲካን ቋሚ ታዛቢ ሊቀ ጳጳስ ኤቶር ባሌስትሬሮ እንደተናገሩት፥ ዓለም አቀፍ ሕግን በሚጻረር መልኩ ሰላማዊ ዜጎች የግጭቶች ሰለባ መሆናቸውን ገልጸው "የተጨፈጨፉ ሰላማዊ ዜጎች ያልታቀደ ጥቃት ሰለባዎች ተብሎ ሊወሰድ እንደማይችል ገልጸዋል።
“በወታደራዊ መሣሪያዎች እና በሰው ልጅ ሕይወት መካከል ያለውን ልዩነት የመለየት ጥብቅ ግዴታ ቢኖርም በሰላማዊው ሕዝብ ላይ ጉዳት ሳይደርስ የሚካሄድ ግጭት የለም” ብለዋል።
ሕዝብ በሚበዛባቸው አካባቢዎች ፈንጂዎችን መጠቀም
ሊቀ ጳጳስ አቡነ ባሌስትሬሮ አክለውም፥ ሕዝብ በሚበዛባቸው አካባቢዎች ፈንጂዎችን መጠቀም፣ ማፈናቀል እና ለሲቪል ሕዝብ አስፈላጊ በሆኑ ከተሞች፣ ትምህርት ቤቶች፣ ሆስፒታሎች፣ የአምልኮ ሥፍራዎች እና መሠረተ ልማቶች ላይ ከፍተኛ ውድመት ማስከተል ቅድስት መንበርን በጥልቅ እንዳሰጋት ገልጸዋል።
ዓለም አቀፍ ሰብዓዊ ሕግን ማክበር የሚቻል ብቻ ሳይሆን አስገዳጅም መሆኑን የተናገሩት አቡነ ባሌስትሬሮ፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳስ ፍራንችስኮስ፥ “በጦርነት መካከል እንኳ ቢሆን እያንዳንዱ የሰው ልጅ የተቀደሰ ነው” ማለታቸውን አስታውሰዋል።
“ግጭቶችን ማስቀረት እንደማይቻል አድርገን መቁጠር ወይም በጦርነት ወቅት ሁሉን ዓይነት ክፋት መፈጸም ይፈቀዳል ብሎ ማሰብ አንችልም” ብለዋል።
በዓለም አቀፍ የሰብዓዊነት ሕግ ላይ የሕዝብ ግንዛቤን ማሳደግ
አሁን ካለው አስጨናቂ የዓለም ሁኔታ አንጻር ዓለም አቀፍ የሰብዓዊነት ሕግ እና ሥነ-ምግባራዊ መሠረቱን ለማዳረስ ያለመ የትምህርት ሂደት እንደሚያስፈልግ ገልጸው፥ በእነዚህ ጉዳዮች ላይ የሕዝብ ግንዛቤን ለማሳደግ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ድጋፍ ለማድረግ ቃል መግባቷን ሊቀ ጳጳስ አቡነ ባሌስትሬሮ ተናግረዋል።
በግጭቶች ውስጥ ሰው ሠራሽ አስተውሎት የጦር መሣሪያ መጠቀምን ማስቆም ያስፈልጋል
በቴክኖሎጂ እድገት እና በሰው ሠራሽ አስተውሎት መሣሪያ በመታገዝ የጦር መሣሪያን መታጠቅ በጦርነት ሂደት ውስጥ ማዕከላዊ እየሆነ በመጣበት በዚህ ወቅት በዓለም አቀፍ ሰብዓዊ ሕግ ላይ የሕዝብ ግንዛቤን ማሳደግ ከሁሉም በላይ አስፈላጊ መሆኑን አቡነ ባሌስትሬሮ አስረድተዋል።
በዚህ ረገድ ቅድስት መንበር የ “ዲጂታል” እና የ “ሳይበር” ቴክኖሎጅዎችን ኃላፊነት በተሞላበት መንገድ መጠቀም እንደሚገባ የቅድስት መንበር ተወካይ ገልጸው፥ እነዚህ ዘመናዊ መሣሪያዎች ለሰላማዊ ዓላማ፣ ለትብብር እና ለጋራ ብልጽግና መዋል እንደሚገቡ አሳስበዋል።
“የሰው ልጅ ማዕከላዊነትን፣ ክብርን እና መሠረታዊ መርሆችን መጠበቅ እንዲሁም የሕይወትን ከፍተኛ እሴት መከላከል በጋራ ንቃተ ህሊና ውስጥ በጥብቅ መቀመጥ አለበት” ሲሉ አሳስበዋል።
የቅድስት መንበር ቁርጠኝነት
ለግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ የበኩሏን አስተዋጽኦ ለማበርከት ቅድስት መንበር በመጪዎቹ አራት ዓመታት ውስጥ ሦስት ሥራዎችን ለማከናወን ቃል መግባቷን ገልጸው እነርሱም፥ ለሠራዊቱ መንፈሳዊ አገልግሎት የሚሰጡ ካቶሊካዊ ካኅናትን በዓለም አቀፍ የሰብዓዊ ሕግ ዘርፍ ማሰልጠን፣ ሥነ-ምግባራዊ መሠረቱን በተለይም ሰላማዊ ዜጎችን እና ሃይማኖታዊ ሥፍራዎችን ከጉዳት መጠበቅ፣ መከባበርን እና በሃይማኖቶች መካከል የሚደረግ ውይይትን ማዳበር ይህም የሰው ልጅ ክብር እንዲጠበቅ ለዓለም አቀፍ የሰብዓዊነት ሕግ መረጃ የሚሆኑ እሴቶችን ለማሳደግ አስተዋፅኦ የሚያደርግ መሆኑን አስረድተዋል።
“ለሰው ልጅ ጦርነት ምን ጊዜም ሽንፈት ነው” በማለት በድጋሚ የተናገሩት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ባሌስትሬሮ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ “ሰላምን ለመገንባት የጦር መሣሪያ ምርትን፣ ሽብርተኝነትን እና ጦርነትን ማስፋፋት ሳይሆን ነገር ግን ርኅራኄ፣ ፍትህ እና ውይይት ያስፈልጋል!” በማለት ያቀረቡትን አቤቱታ በማደስ ንግግራቸውን አጠቃለዋል።
በጄኔቫ የተካሄደ ጉባኤ የውይይት ጭብጦች
ከጥቅምት 18-21/2017 ዓ. ም. የተካሄደው 34ኛው የቀይ መስቀል እና ቀይ ጨረቃ ዓለም አቀፍ ጉባኤ የጄኔቫን ስምምነት የፈረሙ 196 መንግሥታትን የሚወክሉ 191 ብሔራዊ ቀይ መስቀል እና ቀይ ጨረቃ ማኅበራት ተወካዮችን ማሳተፉ ታውቋል።
“ሰብዓዊነትን ማጠናከር” በሚል መሪ ርዕሥ የተካሄደው ጉባኤ አጀንዳ በተለይ ዓለም አቀፍ ሰብዓዊ ሕግን ማክበር፣ የሲቪሎች እና ሰብዓዊ አገልግሎት ጥበቃን ማሳደግ፣ በየአገራቱ የሚመሩ ዘላቂ የሰብዓዊ አገልግሎት እርምጃዎችን ማራመድ፣ የአየር ንብረት ለውጥ ፈታኝ ሁኔታን መከታተል፣ መዘጋጀት እንዲሁም የአደጋ ጊዜ ሕጎች አስፈላጊነት እና በጦርነት ውስጥ የዲጂታል ቴክኖሎጂዎች ተጽእኖ በሚሉት ርዕሠ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ እንደ ነበር ተመልክቷል።