ፈልግ

ቅዱነታቸው የሲኖዶስን ጉባኤ በመሳተፍ ላይ የሚገኙ የቻይና ጳጳሳትን ሲያገኟቸው ቅዱነታቸው የሲኖዶስን ጉባኤ በመሳተፍ ላይ የሚገኙ የቻይና ጳጳሳትን ሲያገኟቸው  

ቅድስት መንበር እና የቻይና መንግሥት የጳጳሳት ሹመት ጊዜያዊ ስምምነት ማራዘማቸው ተነገረ

ቅድስት መንበር እና የቻይና ሕዝባዊ ሪፐብሊክ በብጹዓን ጳጳሳት ሹመት ጊዜያዊ ስምምነት ላይ ተገቢውን ምክክር እና ግምገማ ካደረጉ በኋላ ለተጨማሪ 4 ዓመታት ተስማምተዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

የጳጳሳት ሹመት በሚመለከት ጊዜያዊ ስምምነቱ ውጤታማ በሚሆንበት መንገድ ተፈፃሚ ለማድረግ በተደረሰው ስምምነት መሠረት፥ ቅድስት መንበር እና የቻይና ሕዝባዊ ሪፐብሊክ የጳጳሳት ሹመት ጊዜው ካለፈበት ቀን ጀምሮ ለአራት ዓመታት እንዲራዘም መስማማታቸውን የቅድስት መንበር የመግለጫ ክፍል ማክሰኞ ጥቅምት 12/2017 ዓ. ም. አስታውቋል።

መግለጫው በመቀጠል፥ “ቫቲካን ከቻይና መንግሥት ጋር ያለውን እርስ በርስ የመከባበር፣ ገንቢ ውይይት እና የሁለትዮሽ ግንኙነት የበለጠ ለማጎልበት ቁርጠኛ ሆኖ መቀጠሉ በቻይና ለምትገኝ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን እና ለቻይናውያን ጥቅም ነው” በማለት ገልጿል።

ለሦስተኛ ዙር የተደረገ እድሳት
እንደ ጎርጎሮሳውያኑ መስከረም 22/2018 ዓ. ም. በቅድስት መንበር እና በቻይና ሕዝባዊት ሪፐብሊክ እና እንድሁም በቻይና በምትገኝ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ውስጥም ታሪካዊ ግንኙነት ከተጀመረበት ወዲህ ለሦስተኛ ጊዜ የተደረገ እድሳት ሲሆን፥ ይህም ሁሉም የቻይና ካቶሊክ ብጹዓን ጳጳሳት በሙሉ ተዋረድ ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ጋር እንዲገኙ የሚያስችል እንደሆነ ይታወሳል።

በጊዜያዊ ውል ላይ በሁለቱም ወገኖች የተቀመጠው አዲሱ ፊርማ ለተጨማሪ አራት ዓመታት የሚቆይ ሲሆን፥ የመጀመሪያው እድሳት ለሁለት ዓመታት የሚቆይ ሲሆን ይህም እንደ ጎርጎሮሳውያኑ ጥቅምት 22/2020 ዓ. ም. መሆኑ ይታወሳል።

አዲስ የወደፊት ሁኔታ
ጊዜያዊ ስምምነቱ ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፈቃድ ውጭ ለአሥርተ ዓመታት ሲፈጸም የቆየው የጳጳሳት ሹመት እንዲያበቃ ያደረገ ሲሆን፥ ይህም ባለፉት ስድስት ዓመታት ውስጥ ሥር ነቀል ለውጥ እንዲኖር አድርጓል። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ወደ አሥር የሚጠጉ ጳጳሳት የተሾሙ ሲሆን ቤጂንግ ከዚህ ቀደም እውቅና ያልተሰጣቸው የበርካታ ብጹዓን ጳጳሳት የሕዝብ አገልግሎት ሚናን በይፋ አውቃለች።

በቫቲካን እየተካሄደ ባለው የጠቅላላ ሲኖዶስ ጉባኤ ላይ ከቻይና የመጡ ብጹዓን ጳጳሳት መሳተፋቸው፣ በአውሮፓ እና በአሜሪካ በሚደረጉ ስብሰባዎች እንዲሁም ባለፈው ዓመት በፖርቱጋል መዲና ሊዝበን ላይ በተከበረው ዓለም አቀፍ የወጣቶች በዓል ከቻይና የመጡ በርካታ ወጣቶች መገኘታቸው እና ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በምሥራቅ አገራት ባደረጓቸው ሐዋርያዊ ጉብኝቶች ላይ ከቻይና የመጡ በርካታ ካቶሊክ ምዕመናን መገኘታቸው የአዲሱ ትብብር ማሳያ እንደሆነ ታምኗል።

 

22 October 2024, 17:38