ፈልግ

ሊቀ ጳጳስ ገብርኤሌ ካቺያ ሊቀ ጳጳስ ገብርኤሌ ካቺያ 

አንድነትና መረዳዳት የማኅበራዊ ልማት ቁልፍ ተግባራት ናቸው ተባለ

በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የቫቲካን ቋሚ ታዛቢ የሆኑት ብጹእ አቡነ ጋብሪኤሌ ካቺያ የግለሰቦችን ክብር ያስጠበቀ፣ ድህነትን በማጥፋት እና ቤተሰብን ማጠናከር ላይ የሚሰራ፣ በአንድነት እና በመረዳዳት መርሆዎች ላይ ያተኮረ የበለጠ ሁሉን አቀፍ የማህበራዊ ልማት ጥረቶች እንዲደረጉ ጥሪ አቀረቡ።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

ብጹእ አቡነ ጋብሪኤሌ ካቺያ አርብ ዕለት በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ ወቅት ማህበራዊ ልማትን አስመልክቶ በተደረገ ውይይት ላይ ባደረጉት ንግግር “የሁለንተናዊ የሰው ልጅ እድገት መሰረታዊ ምሰሶ የሆነው” ይህ ግብ አካታች ካልሆነ እና ድህነትን ለማጥፋት ጥረት ካልተደረገ ሊሳካ እንደማይችል አጥብቀው ተናግረዋል።

የድህነት መንስኤዎችን መፍታት
ነገር ግን የሽንገላ የአካታችነት ንግግሮች የተጠቃሚውን ማህበረሰብ “ባህል” በእጅጉ የሚቃረን መሆኑን ጠቁመው፣ “ግለሰቦች ‘ጥቅም አልባ’ ሆነው እንዲሰማቸው በማድረግ ሰብአዊነትን ያሳጣል” ካሉ በኋላ፥ “ለኢፍትሃዊነትና ለእኩልነት መጓደል ቀጣይነት ባለው መልኩ አስተዋፅዖ ያደርጋል” በማለት አሉታዊ ጎኑን አስረድተዋል።

በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የቫቲካን ቋሚ ታዛቢው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስን በመጥቀስ፣ “መደጋገፍ እና ተሳትፎ ሁለቱ የውጤታማ አካታችነት ምሶሶዎች ናቸው” በማለት የድህነትን መንስኤዎች ለማጥፋት የበለጠ ፈጠራ በተሞላበት መንገድ መስራት እንደሚገባ እና ዘላቂ መፍትሄ መስጠት እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል።

ብጹእነታችው አክለውም “ይህንን በማድረግ ለጋራ ጥቅም ሲባል ድሆች እንደ ተረጂ ሳይሆን እንደ አጋር መታየት አለባቸው” ካሉ በኋላ “በድህነት ውስጥ የሚኖሩ ሰዎችን አስቸኳይ ፍላጎቶች ማሟላት አስፈላጊ ነው፥ ይህ ግን ዘላቂ መፍትሄ አይደለም” በማለት አሳስበዋል።

ተደራሽ እና ጥራት ያለው ትምህርት ለሁሉም ማሳደግ
የድህነት ተፅእኖ ቁሳዊ ብቻ ሳይሆን መንፈሳዊም መሆኑን የገለጹት ሊቀ ጳጳስ ካቺያ፣ የትምህርት ጥራትና ተደራሽነት መብት ለሁሉም ማዳረስ እና የማህበራዊ እድገት መንገድ ማረጋገጥ አስፈላጊ መሆኑን አስምረውበታል።

ቤተሰቦችን መደገፍ
ብጹእነታቸው በመቀጠልም ቤተሰብ በማህበራዊ ልማት ውስጥ የሚጫወተውን ወሳኝ ሚና ገልጸው፥ ቤተሰቦችን በተለይም እንደ ድህነት ወይም ግጭት ባሉ አስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ ያሉ ቤተሰቦች ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸው ካስታወሱ በኋላ፥ የቤተሰብን ምስረታ የሚያጠናክሩ እና እንደ ሥራ አጥነት፣ የቤት እጥረት እና የቤት ውስጥ ግጭት ያሉ ችግሮችን የሚፈቱ ህዝባዊ ፖሊሲዎች እንደሚያስፈልጉ አሳስበዋል።

የቫቲካኑ ተወካይ በተጨማሪም ለቤተሰቦች የሥራ ዕድልን የሚያስገኝ እና የቤተሰብን ሕይወት ለማሻሻል የሚረዱ እርምጃዎች እንዲወሰዱም ጠይቀዋል።

ብጹእ አቡነ ካቺያ እነዚህ በከፍተኛ ጥናት የሚወጡ ፖሊሲዎች እና ፕሮግራሞች ጠንካራ ቤተሰቦችን ለማስፋፋት እና የሥራ እና የቤተሰብ ህይወትን በማሻሻል ረገድ የትምህርት እና የስራ አስተዋፅዖን ጨምሮ፥ ድህነት በቤተሰብ ምስረታ እና መበታተን ላይ የሚያሳድረውን ተፅእኖ እንደሚቀንሱ አብራርተዋል።

ሊቀ ጳጳስ ካቺያ በመጨረሻም፣ ከመሪዎች ጀምሮ በችግር ውስጥ እስከሚገኙ ሰዎች፣ ሁሉም የሰው ልጆች እንደ ክብራቸው መኖር እንደሚችሉ ለማረጋገጥ በአብሮነት እና በመደጋገፍ መንፈስ በሁሉም ደረጃዎች የሚደረጉ ጥረቶች አስፈላጊ መሆናቸውን በማሳሰብ፥ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን በተግባር በርካታ ሥራዎችን እየሰሩ በሚገኙ የተለያዩ ድርጅቶቿ አማካይነት የሰው ልጅን ሁለንተናዊ እድገት ለማስፋፋት ያላትን ቁርጠኝነት በድጋሚ አረጋግጠዋል።
 

07 October 2024, 13:39