ቅዱስ ሲኖዶስ በአካል ጉዳተኞች፣ በሴቶች እና በአየር ንብረት ቀውስ ላይ ውይይቶችን አካሄደ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
የሲኖዶሱ ጉባኤ ማክሰኞ ጥቅምት 5/2017 ዓ. ም. በጳውሎስ ስድስተኛ አዳራሽ ውስጥ ያካሄደው ውይይት በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ዙሪያ በሚገኙት አምዶች ስር ተጠልሎ ይኖሩ የነበረ እና ነሐሴ ወር ላይ ያረፈውን ብራዚላዊ ገጣሚ ሆሴ ካርሎስ ደ ሱሳን በማሰብ የተጀመረ እንደ ነበር ተገልጿል።
ይህን ዜና በሲኖዶሱ ጋዜጣዊ መግለጫ ወቅት ያጋሩት በቅድስት መንበር ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ኃላፊ እና የሲኖዶሱ የመረጃ ኮሚሽን ፕሬዝዳንት ዶ/ር ፓውሎ ሩፊኒ ናቸው። ዶ/ር ፓውሎ ሩፊኒ በመቀጠልም ሰኞ ከሰዓት በኋላ እና ማክሰኞ ዕለት በትናንሽ ቡድኖች ተመድበው ውይይታቸውን ያካሄዱ 347 የጉባኤው ተሳታፊዎች እንደ ነበሩ ገልጸዋል።
የመቀራረቢያ ሥፍራዎች የመገናኛ ቦታዎች ናቸው!
ይህ በእንዲህ እንዳለ የሲኖዶሱ የመረጃ ኮሚሽን ጸሐፊ ዶ/ር ሺላ ፒሬስ በቅዱስ ቤነዲክቶስ ማኅበር ገዳማዊት እህት ማርያ ኢግናሲያ አንጀሊኒ እና በብጹዕ ካርዲናል ሆሌሪች መሪነት ከተካሄደው ጸሎት እና አስተንትኖ ለተገኙት ቁልፍ ነጥቦች አፅንዖት ሰጥተዋል።
ዶ/ር ፒሬስ እህት አንጀሊኒ ያቀረቡት አስተንትኖ በቤተ ክርስቲያን ክርስቲያናዊ መሠረት ላይ ያተኮረ መሆኑን አስታውሰው፥ ቤተ ክርስቲያን እራሷን በተጨባጭ አውድ ውስጥ በማስገባት እና በቅዱስ ወንጌል የለውጥ ኃይልነት ላይ ያሰላሰለ እንደ ነበር ተናግረው፥ የሰው ልጅ መስተጋብር ወንጌልን በተጨባጭ ለመኖር እና ለመመስከር ዕድል እንደሚሰጥ ገልጸዋል።
የለውጥ ኃይል ዕይታ
ብጹዕ ካርዲናል ሆለሪች በሪፖርት የተግባር ሠነዱ በክፍል ሦስት ለ“ቦታዎች” የተሠጠውን አስፈላጊነት አስምረውበታል። ዶ/ር ፒሬስ እንዳስገነዘቡት፥ ውይይቱ በተልዕኮ አውዶች ላይ በተለይም በከተሞች እና በዋና ከተሞች ላይ ያተኮረ እና የስደት ክስተትም ዕይታ ያለው እንደ ነበር አመላክተዋል።
በኅብረት የሚጓዙ አካባቢዎች የቤተ ክርስቲያንን አንድነት ከመቅረጽ ጋር ባላቸው ግንኝነት ላይ በማሰላሰል፥ ብጹዕ ካርዲናል ሆለሪች የጉባኤው ተሳታፊዎች በምናባዊ ዓለም አቀፋዊነት እንዳይጠቁ በማስጠንቀቅ እውነተኛ የሕይወት ሁኔታዎችን እንዲያጤኑ ጋብዘው፥ ቤተ ክርስቲያን በቦታ እና በባሕል ያልተመሠረተች ካልሆነ ሊረዷት እንደማይቻል ጠቁመው የቦታ እና የባሕል ትስስር አስፈላጊነትን አጉልተው አሳይተዋል።
በጉጉት እየጠበቁ ጉዞውን ወደፊት መቀጠል
የሐዋርያዊ ቀርሜሎስ እህቶች ገዳማውያት ማኅበር የበላይ አለቃ እህት ኒርማላ አሌክስ ማርያ፥ ሲኖዶሱን “ልዩ ተሞክሮ” ሲሉ ገልፀው፥ በዓለም ዙሪያ ካሉ የቤተ ክርስቲያን ተወካዮች ጋር መገናኘት ዕድል እንደሆነ በማስረዳት የአዲሱ ተመራጭ ካርዲናል ቲሞቲ ራድክሊፍ እና የእህት ማርያ ኢግናሲያ አንጀሊኒ አስተንትኖ “አበረታች ነው” በማለት ገልጸዋል።
እህት ኒርማላ ከጉባኤው ፍጻሜ በኋላ ወደ አገራቸው ሲመለሱ ከአብያተ ክርስቲያናት ጋር መገናኘት እንደሚያስፈልግ አፅንዖት ሰጥተው፥ ነገር ግን ይህን ለማድረግ ቀድሞውንም የተስፋ ስሜት እንዳላቸው ገልጸው፥ የሲኖዶሱን ጉዞ ከጀመርን በኋላ ወደፊት እንጂ ወደ ኋላ መመለስ አንችልም ብለዋል።
በሥፍራ እና በባህል ላይ የተመሠረተች ቤተ ክርስቲያን
በብራዚል የመናውስ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ ካርዲናል እስታይነር ማክሰኞ ዕለት በቀረበው ጋዜጣዊ መግለጫ ወቅት እንደተናገሩት፥ በተለይም ከሲኖዶሱ የሚወጡ አዳዲስ መንገዶች የሲኖዶሳዊነትን ተግባራዊ ትርጉም እንዴት እንደሚገልጹ ተናግረው፥ ይህ ሂደት ብራዚል ውስጥ አስቀድሞም ቢሆን ሲካሄድ እንደቆየ ገልጸው፥ በርካታ ሴቶች እና ቋሚ ዲያቆናት በአማዞን ደኖች ወስጥ የሚገኙ ማኅበረሰቦችን በንቃት በመምራት ላይ መሆናቸውን አስረድተዋል። ብፁዕ ካርዲናል እስታይነር በማከልም “በመካሄድ ላይ ካለው ጉባኤ የምቀስመው ልምድ በአገራችን በምትገኝ ቤተ ክርስቲያናችን ያለውን ሲኖዶሳዊነት የበለጠ እንድንረዳ ይረዳናል” ሲሉ ተናግረዋል። “ቦታን ወይም አካባቢን መሠረት ላደረገች ቤተ ክርስቲያን የባሕሎች እና የሃይማኖቶች ብዝሃነት ቁልፍ ናቸው” ሲሉ አጽንኦት ሰጥተዋል።
በብራዚል ውስጥ የሚታይ የአካባቢ ቀውስ
የሲኖዶሱ ተሳታፊዎች ብራዚል ውስጥ የተከሰተው ድንገተኛ የአካባቢ አደጋ በተለይም በአማዞን አካባቢዎች ለአንድ ወር የዘለቀው ድርቅ ወንዞች እንዳይፈሱ ማድረጉን እና በርካታ ማኅበረሰቦች እዲለያዩ ማድረጉን ተመልክተዋል።
ብፁዕ ካርዲናል እስታይነር ከአማዞን ባሻገር ባሉ አካባቢዎች የውሃ እጥረት ያጋጠማቸው በመሆኑ ሁኔታውን አሳሳቢ ደረጃ ላይ ማድረሱን ገልጸው፥ ከገደብ በላይ ዓሣ ማጥመድ እና የሜርኩሪ ብክለት በክልሉ ሥነ-ምህዳር ላይ የሚያስከትሉት ውጤቶች አሳዛኝ እንደሆኑ አስረድተዋል።
ምንም እንኳን ሲኖዶሱ የአካባቢ ጉዳዮችን በግልፅ ባይናገር፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከዚህ በፊት ከተካሄደው የብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ በኋላ ይፋ የሆነው “ኬሪዳ አማዞንያ” የሚለው ሠነድ የመኖሪያ አካባቢ የሲኖዶሳዊነት ዋና አካል እንደሆነ ለመረዳት የሚያስችል ማዕቀፍ እንደሚሰጥ ብፁዕ ካርዲናል እስታይነር አሳስበዋል። “ልምዶችን እየኖርንበት ያለው ሲኖዶስ የቤተ ክርስቲያን ተልዕኮአችን አካል በመሆኑ ካለቀ በኋላም ቢሆን ይህን ጉዞ መቀጠል አለብን” ብለዋል።
ዓለም አቀፋዊት ቤተ ክርስቲያንን ማሰብ
የቱሪኑ ሊቀ ጳጳስ ተመራጩ ካርዲናል ሬፖል የሲኖዶሱ ሂደት ለሀገረ ስብከታቸው ያለውን ፋይዳ ሲናገሩ፥ የተሳታፊዎቹ መንፈሳዊ ጥልቀት እና በመካከላቸው እያደገ ያለው የወዳጅነት ስሜት በእርሳቸው ላይ ጠንካራ ስሜት መፍጠሩን ተናግረው፥ ሲኖዶሱ ከተለያዩ ባሕሎች የተውጣጡ ድምፆችን በማካተት ወንጌልን በማስፋፋት ረገድ የቤተ ክርስቲያንን ሁለንተናዊ ተፈጥሮ በንጸባርቅ አጽንኦት መስጠቱን ገልጸዋል።
በቅድስት መንበር ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ኃላፊ እና የሲኖዶሱ የመረጃ ኮሚሽን ፕሬዝዳንት ዶ/ር ፓውሎ ሩፊኒ ከጋዜጠኞች ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች በሰጡት ምላሽ፥ የአካል ጉዳተኞችን ማካተትን አስመልክተው እንድተናገሩት፥ ይህ ርዕሥ በአንዳንድ የውይይት ቡድኖች ውስጥ እንደተነሳ እና ለሁሉን ሰው ልብ የነካ መሆኑን አምነዋል።
ቢያንስ እርሳቸው በተገኙበት ቡድን ውስጥም ውይይት የተደረገበት ርዕሥ እንደ ነበር ገልጸው፥ “በሚቀጥሉት ቀናት በጠቅላላ ጉባኤ ውስጥ ይብራራ እንደሆነ እናያለን” ብለዋል። በእርግጠኝነት ጉዳዩ የሁሉንም ሰው ልብ የነካ እና የበለጠ ሊሠራበት እንደሚችል ተናግረው፥ “ስለ ድሆች እና ስለ ተገለሉት ስናወራ ስለ አካል ጉዳተኞች ጭምር እናወራለን” ብለዋል።