ፈልግ

የሲኖዶሱ የመጨረሻ ሠነድ ረቂቅ ለጠቅላላ ጉባኤ መቅረቡ ተነገረ

የሲኖዶሱ የመረጃ ኮሚሽን ሰኞ ጥቅምት 11/2017 ዓ. ም. በሰጠው 15ኛ ጋዜጣዊ መግለጫ፥ የፍጻሜ ሠነድ ረቂቅ ለጠቅላላ ጉባኤ ቀርቦ ለሁሉም የሲኖዶስ ጉባኤ ተሳታፊዎች መታደሉን አስታውቋል። የቅድስት መንበር መገናኛ ጽሕፈት ቤት ዋና ተጠሪ እና የጉባኤው የመረጃ ኮሚሽን ፕሬዚዳንት ዶ/ር ፓውሎ ሩፊኒ በሰጡት ዕለታዊ መግለጫ “ወደ ወሳኝ የጸሎት እና የሲኖዶሳዊ ተነሳሽነት ጊዜ ላይ ደርሰናል” ብለዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ዶ/ር ፓውሎ ሩፊኒ በማከልም እሑድ ጥቅምት 10/2017 ዓ. ም. በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ በቀረበው የመስዋዕተ ቅዳሴ ሥነ-ሥርዓት ላይ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን 14 አዳዲስ ቅዱሳንን ማግኘቷን ተከትሎ የጉባኤው አባላት በሙሉ የተሰማቸውን ደስታ ገልጸው፥ ይህ ጉልህ ክስተት የታየው በሲኖዶሱ ጠቅላላ ጉባኤ ወቅት እና በዓለም አቀፍ የተልዕኮ እሑድ መሆኑን አስታውሰዋል።

ዶ/ር ፓውሎ ሩፊኒ እንደዚሁም እሑድ ጥቅምት 10/2017 ዓ. ም. ከሰዓት በኋላ የዲጂታል የወንጌል ልኡካንን በመስመር ላይ ያሰባሰበውን የጸሎት ዝግጅት በሲኖዶሱ የተግባር ሠነድ ውስጥ በዋናነት የተገለጸው የቤተ ክርስቲያን የማዳመጥ ተነሳሽነት አካል እንደሆነ ጠቅሰዋል።

ዶ/ር ሩፊኒ ለጋዜጠኞች መግለጫ ሲሰጡ
ዶ/ር ሩፊኒ ለጋዜጠኞች መግለጫ ሲሰጡ

የሲኖዶሱ የመጨረሻው ረቂቅ ሠነድ 
የሲኖዶሱ የመረጃ ኮሚሽን ጸሐፊ ዶ/ር ሺላ ፒሬስ የዕለቱን ሂደት ሲያብራሩ፥ “አሁን ጉባኤው በመጨረሻ ሳምንት ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል። ዕለቱ በቅዱስ ጴጥሮስ ባሲሊካ ውስጥ በቀረበው የቅዳሴ ጸሎት የተጀመረ ሲሆን፥ የብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ ጠቅላይ ጸሐፊ ብጹዕ ካርዲናል ማርዮ ግሬች በቅዳሴው ላይ ባሰሙት ስብከት ሲኖዶሱ የእግዚአብሔርን ቃል ለሁሉም ለማወጅ እንዳለመ አዲስ ጅምር መታየት እንዳለበት አጽንኦት ሰጥተዋል።

351 አባላት የተሳተፉበት ጠቅላላ ጉባኤ የተካሄደው አባ ቲሞቲ ራድክሊፍ ባቀረቧቸው “ነጻነት እና ኃላፊነት” በሚሉት ጭብጦች ላይ በተደረገ አስተንትኖ ሲሆን፥ በመቀጠልም የመጨረሻው ሠነድ ረቂቅ በብጹዕ ካርዲናል ዣን ክላውድ ሆሌሪች ቀርቧል።

በጊዜያዊነት የቀረበው ረቂቁ ሚስጥራዊነትን የሚጠይቅ መሆኑን አጽንዖት ሰጥተው፥ ይህ የሆነበትም ግልጽነት ስለጎደለው ሳይሆን ነገር ግን ለውይይት ምቹ ሁኔታ እንዲኖር ለማድረግ እንደሆነ አስረድተዋል። የእያንዳንዱ የጉባኤው ተሳታፊ የትብብር ሥራ ውጤት የሆነው የረቂቁ ቅጂ ለሁሉም አባላት መታደሉ ታውቋል።

“ረቂቅ ሠነዱ በጉባኤው የተካሄዱ ውይይቶች ውጤት ብቻ ሳይሆን የበለጸገ ሂደትን ያቀፈ እና በተለያዩ የሲኖዶስ ጉዞ ምዕራፎች የተከናወኑ ሥራዎችን ሁሉ ያካተተ ነው” ሲሉ በብጹዕ ካርዲናል ዣን ክላውድ ሆሌሪች ተናግረዋል።

የሲኖዶሱ የመረጃ ኮሚሽን ጸሐፊ ዶ/ር ሺላ ፒሬስም በበኩላቸው፥ ሪፖርት አቅራቢዎች እና ባለሙያዎች የሚደርሷቸውን አስተያየቶች በጥንቃቄ ለመመልከት የተጉበት እና ከትናንሽ ቡድኖች የቀረቡ ሪፖርቶችን በጥልቀት የመረመሯቸው መሆኑን ገልጸው፥ በተለይም የነገረ-መለኮት ሊቃውንት አስተዋጽዖ ለረቂቅ ሠነዱ ዝግጅትም ሆነ ለውይይት መድረኮች ጠቃሚ እንደ ነበር አስረድተዋል።

ከሰዓት በኋላ የተደረጉ በትናንሽ ቡድኖች ውይይቶች
ብጹዕ ካርዲናል ግሬች እንደተናገሩት ሰኞ ጥቅምት 11/2017 ዓ. ም. ከሰዓት በኋላ በትናንሽ ቡድኖች የተካሄዱት ውይይቶች ተሳታፊዎች ለእውነተኛ የስጦታ ልውውጥ የተሰበሰቡበት እንደ ነበር ዶ/ር ሺላ ፒሬስ ገልጸው፥ “ተግዳሮቶችን፣ ህልሞችን፣ ውስጣዊ ለውጦችን እና ረቂቅ ሠነዱን በማንበብ የተገኙ አዳዲስ መነሳሳቶችን ለመጋራት እና ይህም ምናልባት ያልተለመደ እና አዲስ የሱባኤ መንገድ ነው” ሲሉ ብጹዕ ካርዲናል ግሬች መናገራቸው ዶ/ር ሺላ ፒሬስ ገልጸዋል።

“ውይይት ለራሷ ለቤተ ክርስቲያን መሠረት ነው!”
አጭር መግለጫ ከሰጡት መካከል የጣልያን ካቶሊክ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዚደንት ብፁዕ ካርዲናል ማቴዎ ዙፒ፥ ኅዳር 28/2017 ዓ. ም. የካርዲናነትን ማዕረግ የሚቀበሉት የሲኖዶሱ መንፈሳዊ አማካሪ አባ ቲሞቲ ፒተር ጆሴፍ ራድክሊፍ፣ የሲኖዶሱ ጠቅላይ ጽ/ቤት ምክትል ጸሐፊ እህት ናታሊ ቤኳርት እና በግሪክ የባይዛንታይን ሥርዓት የሚከተሉ ካቶሊክ ምዕምናን ሐዋርያዊ መሪ አቡነ ማኑኤል ኒን ጉኤል እንደ ነበሩ ተገልጿል።

ብፁዕ ካርዲናል ማቴዎ ዙፒ በሲኖዶሱ ሂደቶች ውስጥ የተካሄደውን የውይይት ልምድ በማስታወስ እንደተናገሩት፥ “የውይይት ልምዱ መሣሪያ ሳይሆን ለቤተ ክርስቲያን መሠረት ነው” ሲሉ ገልጸውታል። ተሳታፊዎቹ ለመነጋገር፣ ለመደማመጥ እና እርስ በርስ ለመገናኘት የተሰበሰቡባቸው ጠረጴዛዎች ዘወትር መንፈሳዊነት ባለው ሂደት እንደ ነበር አስታውሰዋል።

“የመጨረሻው ሠነድ ‘የመንግሥቱን ምስሎች’ የያዘ ነው!”
የሲኖዶሱ መንፈሳዊ አማካሪ አባ ቲሞቲ ፒተር ጆሴፍ ራድክሊፍ፣ ቤተ ክርስቲያኒቱ በአሁኑ ጊዜ እያካሄደች ያለው የመታደስ ጉዞ በመጨረሻው ሠነድ ላይ የሚቀርብ ጉዞ እንደሆነ በመግለጽ፥ ረቂቅ ሠነዱ ውሳኔ የተሰጠበት ወይም ግንባር ቀደም ርዕሥ ተደርጎ መወሰድ እንደሌለበት አሳስበዋል።

ኅብረተሰቡ እየተበታተነ በሚገኝበት እና ዓለም አስቸጋሪ የጦርነት ጊዜን እያሳለፈች በምትገኝበት በዚህ ወቅት ቤተ ክርስቲያን የክርስቶስ የሰላም ምልክት የመሆን እና ከክርስቶስ ጋር በኅብረት እንድትኖር የሚያደርጋት የተለየ ጥሪ ያላት መሆኑን ገልጸዋል።

በዚህ ሲኖዶስ አማካይነት ቤተ ክርስቲያንን በአዲስ መንገድ የምናስባት ጊዜ እየመጣ እንደሆነ እና ኢየሱስ ክርስቶስ መንግሥቱን ለማወጅ ምሳሌዎችን እንደተጠቀመ ሁሉ የመጨረሻው ሠነዱም ያንን ለማሳየት ልዩ ልዩ ምስሎችን የሚያቀርብ እንደሆነ አባ ቲሞቲ ፒተር ጆሴፍ ተናግረዋል።

በቫቲካን ፕሬስ ጽ/ቤት መግለጫ ሲስጥ
በቫቲካን ፕሬስ ጽ/ቤት መግለጫ ሲስጥ

ሲኖዳሳዊነት እና የክርስቲያኖች አንድነት
የሲኖዶሱ ጠቅላይ ጽ/ቤት ምክትል ጸሐፊ እህት ናታሊ ቤኳርት በሌሎች አብያተ ክርስቲያናት ልኡካን በኩል የሚታየውን ወንድማማችነት መንፈስ በማስመለከት እንደተናገሩት፥ ሲኖዶሱ ቤተ ክርስቲያን የመሆን አዲስ ምስል እንደሚሰጥ፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በጉባኤው ተሳታፊዎች መካከል ተቀምጠው ሲያዳምጡ እና በክርስቲያኖች አንድነት የጸሎት ሥነ-ሥርዓት ላይ የተገኙትን በመጥቀስ እና የቅዱስ ጴጥሮስን ሰማዕትነት በማሰብ የጉባኤው ተሳታፊዎች በአንድነት ሲጸልዩ እንደ ነበር ተናግረዋል።

በማከልም ይህ ሲኖዶስ ለክርስቲያኖች ግንኙነት እና አንድነት አዲስ ምዕራፍ የከፈተ፣ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቀዳሚነት እና በብጹዓን ጳጳሳት እና በመላው የእግዚአብሔር ሕዝቦች መካከል ያለውን ትብብር ለመረዳት የሚያግዝ ዘዴን የሚያስተዋውቅ እንደሆነ ተናግረዋል።

በግሪክ የሚገኙ የምሥራቅ ቤተ ክርስቲያን ካቶሊክ ምዕመናን
ከመቶ ዓመት በፊት የተቋቋመ እና በግሪክ የባይዛንታይን ሥርዓት የሚከተሉ ጥቂት የካቶሊክ ማኅበረሰብ ሐዋርያዊ መሪ የሆኑት አቡነ ማኑኤል ኒን ጉኤል እንደተናገሩት፥ ሲኖዶሱ ጠለቅ ያለ ግንዛቤ እንዲኖር ዕድል የሰጠ መሆኑን አስረድተዋል።

የካቶሊክ ማኅበረሰብ በዚያች አገር የተመሠረተው የግሪኮ-ቱርክ ጦርነትን ተከትሎ ብዙ የግሪክ ስደተኞች አቴንስ በደረሱበት ወቅት እንደነበር ሲታወስ፥ ሐዋርያዊ አስተዳደሩ ሁለት ቁምስናዎችን ያቀፈ፥ አንደኛው በአቴንስ የሚገኘው ካቴድራል ሲሆን ሁለተኛው በሰሜን 500 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በተሰሎንቄ አቅራቢያ የሚገኝ እንደሆነ ታውቋል።

ብፁዕ ካርዲናል ፈርናንዴዝ የሰጡት ማብራሪያ

በቅድስት መንበር የእምነት አስተምህሮ ጳጳሳዊ ጽ/ቤት ተጠሪ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ ካርዲናል ፈርናንዴዝ ጥቅምት 11/2017 ዓ. ም. በሲኖዶሱ ጠቅላላ ጉባኤ ወቅት በሰጡት ማብራሪያ፥ የሴቶችን ዲቁና በተመለከተ ምላሽ ለመስጠት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እስካሁን ዝግጁ እንዳልሆኑ አጽንኦት ሰጥተዋል። ሆኖም በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የሴቶች ሚናዎች ላይ የተደረገው ውይይት ቁልፍ ትኩረት የተሰጠበት እንደ ነበር አስረድተዋል።

አባ ቲሞቲ ፒተር ጆሴፍ ራድክሊፍ፥ ሰዎች በሹመት ላይ ብቻ ማትኮር እንደሌለባቸው ነገር ግን በታሪክ ውስጥ ሴቶች ከፍተኛ የቤተ ክርስቲያን ዶክተርነት ቦታ የነበራቸው መሆኑን አሳስበዋል። ሁሉም ነገር ወደ ሹመት ደረጃ ከወረደ ለሥልጣን አስተሳሰብ ያጋልጠናል ብለዋል።

የሲኖዶሱ ጠቅላይ ጽ/ቤት ምክትል ጸሐፊ እህት ናታሊ ቤኳርት እነዚህን ነጥቦች በማጠናከር ሴቶች ቀደም ሲል በቤተ ክርስቲያ ውስጥ እንደ የካቶሊክ ዩኒቨርሲቲዎች ፕሬዚዳንቶች፣ በካሪታስ የካቶሊክ ዕርዳታ ሰጭ ድርጅቶች ውስጥ የመሪነት ሥልጣን እንዳላቸው ወይም በብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤዎች ውስጥ የክፍል ኃላፊዎች እና ከፍተኛ ቦታዎችን ይዘው መቆየታቸውን አጽንኦት ሰጥተዋል።

የሴቶችን የአመራር ሚናን ለማስተዋወቅ ብዙ መንገዶች እንዳሉ የገለጹት ጸሐፊ እህት ናታሊ ቤኳርት፥ በርካታ ጳጳሳት በአሁኑ ወቅት ሴቶችን በሀገረ ስብከታቸው ውስጥ በመሾም በአስተዳደር ውስጥ ሚና እንዲኖራቸው በማድረግ ላይ እንደሚገኙ አስረድተዋል።

አክለውም ቤተ ክርስቲያን የኅብረተሰብ አካል በመሆኗ ማኅበራዊ እና ባሕላዊ እንቅፋቶች አሁንም እንዳሉ በመጥቀስ፥ ለምሳሌ፣ ከአንግሊካን ጳጳስ ጋር በተነጋገሩበት ወቅት፥ ምንም እንኳን ሴቶች ለቤተ ክርስቲያን አገልግሎት በተቀቡበት ጊዜም እንኳ ብዙውን ጊዜ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የወንድ አስተዋጽዖ ከሴቶች የበለጠ ክብደት እንደሚሰጠው መናገራቸውን በማስታወስ፥ እውነተኛ የአስተሳሰብ ለውጥ እንደሚያስፈልግ እና ይህም ጊዜ እንደሚወስድ ገልጸው፥ አስተሳሰቦችን የምንወርሰው ከቤተ ክርስቲያን ብቻ ሳይሆን ከምንኖርበት ማኅበረሰብም ጭምር ነው ብለዋል።

ሙሉ ጋዜጣዊ መግለጫ

 

22 October 2024, 17:18