ፈልግ

ቅዱስ ሲኖዶስ፥ ቤተ ክርስቲያን በውስጧ እና ከሌሎች ጋር ላሉ ግንኙነቶች በምትሰጠው እንክብካቤ ላይ ተወያየ

የቅዱስ ሲኖዶስ ጠቅላላ ጉባኤ ለግንኙነቶች ሊደረግ የሚገባውን እንክብካቤ በማስመልከት ዓርብ ጥቅምት 1/2017 ዓ. ም. በሰጠው አጭር መግለጫ፥ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ እንዲሁም በቤተ ክርስቲያን እና በዓለም መካከል ላሉት ግንኙነቶች ሊደረግ የሚገባውን እንክብካቤ በማስመልከት ከጠቅላላ ጉባኤው የቀረቡ አስተያየቶች ግልጽ አድርጓል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ዓርብ ጥቅምት 1/2017 ዓ. ም. መግለጫው በቅዱስ ሲኖዶስ ጠቅላላ ጉባኤ የማስታወቂያ ኮሚሽን ፕሬዝዳንት ዶ/ር ፓኦሎ ሩፊኒ እና የኮሚሽኑ ፀሐፊ ዶ/ር ሺላ ፒሬስ የቀረበ ሲሆን፥ ውይይት በተደረጉባቸው ርዕሦች ላይ ማብራሪያ እንዲሰጡ ከተጋበዙት እንግዶች መካከል በአሜሪካ የኒውዮርክ ከተማ ጳጳስ ብፁዕ ካርዲናል ጆሴፍ ቶቢን፣ የሲኖዶሱን ሂደት የሚከታተሉ የአውሮፓ አኅጉር ተወካይ ዶ/ር ጁሴፒና ዴ ሲሞን እና በአውስትራሊያ የሳንድኸርስት ጳጳስ አቡነ ሼን ማኪንሌይ ይገኙበታል።

ዶ/ር ሺላ ፒሬስ በመግለጫቸው፥ ዓርብ ጥቅምት 1/2017 ዓ. ም. ከሰዓት በኋላ የተደረገው ውይይት ማዕከላዊ ጭብጥ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ እና እንዲሁም በቤተ ክርስቲያን እና በዓለም መካከል ላሉት ግንኙነቶች የሚደረግ እንክብካቤን የተመለከተ እንደ ነበር ጠቁመዋል።

ግልጽነት፣ በትምህርት ማዘጋጀት እና ተጠያቂነት
ዶ/ር ፒሬስ በመግለጫቸው፣ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ እና እንዲሁም ቤተ ክርስቲያን እና በዓለም መካከል ላሉት ግንኙነቶች የሚደረግ እንክብካቤ፣ በመተማመን እና በወጥነት ላይ የተመሠረተ እንዲሁም ግልጽነት ያለው መሆን እንዳለበት ተናግረው፥ ብጹዕ ካርዲናል ሆሌሪች በትምህርት የተዘጋጁ ምዕመናንን ማዘጋጀትን በተመከተ አጽንዖት በሰጡት መሠረት ቤተ ክርስቲያናዊ ማስተዋል ከሌሎች የአስተዳዳር ዘይቤዎች የተለየ መሆኑን ዶ/ር ፒሬስ አስረድተዋል።

ካርዲናል ሆሌሪች በስድስተኛው ጠቅላላ ጉባኤ ወቅት ንግግር ሲያደርጉ
ካርዲናል ሆሌሪች በስድስተኛው ጠቅላላ ጉባኤ ወቅት ንግግር ሲያደርጉ

ዶ/ር ፒሬስ፥ ብጹዕ ካርዲናል ሆሌሪች በቤተ ክርስቲያን ውስጥ አሳታፊ እና የውሳኔ አሰጣጥ ሂደቶችን ማሳደግ እና የተጠያቂነት አስፈላጊነትን በማስመልከት ያቀረቡትን ጥሪን መሠረት በማድረግ እንደተናገሩት፥ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሃላፊነት ያለባቸው ሰዎች ሥራ ሊገመገም ይገባል ማለታቸውን ገልጸዋል።

በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ያሉ የለውጥ ሂደቶች
በሦስተኛው የውይይት ቅጽ መጀመሪያ ላይ አባ ቲሞቲ ራድክሊፍን ያደረጉትን አስተንትኖ በማስመልከት ዶ/ር ፒሬስ እንደተናገሩት፥ የዶሚኒካን ማኅበር መንፈሳዊ መሪ አባ ቲሞቲ፥ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ባሉት የለውጥ ሂደቶች እና በቅዱስ ወንጌል ውስጥ እንደተጠቀሰው ኢየሱስ ክርስቶስ ከከነዓናዊቷ ሴት ጋር ባደረገው ግንኙነት መካከል ያለውን ማነጻጸራቸውን ጠቁመዋል።

አባ ቲሞቲ እንደተናገሩት፥ የኢየሱስ ዝምታ ቤተ ክርስቲያን በስቃይ ውስጥ የሚገኙትን ሰዎች ጩኸት ለመስማት እና ዛሬ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ያሉ ውስብስብ ጥያቄዎችን ለመፍታት ለምታደርገው ጥረት አርአያ ሊሆን የሚችል የጥልቅ ማዳመጥ ጊዜ እንደሆነ ማስረዳታቸውን ገልጸዋል።

አባ ቲሞቲ በአስተንትኖአቸው፥ የእኩልነት እና የልዩነት ግንኙነት ጥያቄን በተለይም በተጠመቁት ምዕመናን ውስጥ ካሉ ልዩ ልዩ ጥሪዎች እና ሚናዎች አንፃር አፅንዖት ሰጥተው፥ በመጨረሻም ትኩረት እና ቀጣይነት ያለው ጸሎት አስፈላጊ እንደሆነ ገልጸው፥ ፈጣን እና ቀላል መልሶች ለማግኘት የሚቀርቡ ጥያቄዎችን መቋቋም አስፈላጊ እንደሆነ ተናግረዋል። አባ ቲሞቲ እንደተናገሩት፥ ኢየሱስ ለከነዓናዊቷ ሴት የሰጣት ምላሽ ለየት ያሉ ሰዎችንም ቢሆን ለመቀበል ያሳየውን ዕይታ እንደሚገልጽ አስረድተዋል።

አባ ቲሞቲ መንፈሳዊ የአስተንትኖ ጊዜን በመምራት ላይ
አባ ቲሞቲ መንፈሳዊ የአስተንትኖ ጊዜን በመምራት ላይ

ሲኖዶሱ በሚቀጥሉት ቀናት የሚፈጽማቸው ሥራዎች
የዶ/ር ፒሬስን አጭር መግለጫ ተከትሎ፣ በቅዱስ ሲኖዶስ ጠቅላላ ጉባኤ የማስታወቂያ ኮሚሽን ፕሬዝዳንት ዶ/ር ፓውሎ ሩፊኒ ጉባኤው በሚቀጥሉት ቀናት ውስጥ የሚያከናውናቸው ሥራዎችን በዝርዝር ገልጸዋል። ዶ/ር ሩፊኒ በተጨማሪም ሁሉም ሰው በሲኖዶስ የክርስቲያኖች አንድነት ዋዜማ ላይ በተዘጋጀው የጸሎት ሥነ-ሥርዓት ላይ እንዲሳተፍ ጋብዘዋል። የጸሎት ሥነ-ሥርዓቱ አርብ ምሽት በቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ፊት ለፊት፥ ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ ሰማዕትነትን በከፈለበት አደባባይ ላይ እንደሚፈጸም አስረድተው፥ የጸሎት ሥነ-ሥርዓቱን በዓለም ዙሪያ የሚገኙ ከ80 በላይ ካቶሊካዊ ቁምስናዎች እንደሚሳተፉት ተናግረዋል።

 

14 October 2024, 16:51