ብፁዕ ካርዲናል ካርሎስ፥ “ስኬቶቻችን ሳንደናቀፍ እስከ መጨረሻው እንድንጸና የሚያበረታቱን ናቸው”
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
የጉባኤውን ተካፋዮች “እንኳን በደህና መጣችሁ!” በማለት የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት ብፁዕ ካርዲናል ካርሎስ፥ የቀድሞው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ጳውሎስ ስድስተኛ “የእርሱ ቤተ ክርስቲያን” በሚል ርዕሥ በሁለተኛው የቫቲካን ጉባኤ ላይ ያስተላለፉት የመጀመሪያ ሐዋርያዊ መልዕክታቸው ቤተ ክርስቲያን አሁን የገጠማትን ፈተና ለማሸነፍ የሚያግዛት በመሆኑ ዛሬም ያገለግላል ሲሉ አስረድተዋል።
የቀድሞው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ እምነትን በተስፋ፣ በደስታ እና በውጤታማነት ለአዲሱ ትውልዶች ለማስተላለፍ በተለይም በብዙዎች ዘንድ በተስፋፋው የእኩልነት ማጣት እና የኅብረተሰብ ያለመግባባቶች መዘዝ ለሚሰቃይ ዓለም አዲሱን የወንጌል ስርጭት ማሳካት አስፈላጊ እንደሆነ ጠቁመዋል።
“የእናንተም ጭምር የሆኑት ሁለቱ ደንቦቻችን ከሦስተኛው ደንብ ጋር በመሆን ቤተ ክርስቲያን ከምትኖርበት ዓለም ጋር መመሥረት ካለባት ግንኙነት ጋር የተያያዘ ነው። ቤተ ክርስቲያን ከዘመናዊው ዓለም ጋር በምታደርገው ውይይት ችግር የገጠማት በዚህ ጊዜ ነው። ስለዚህ ሁለተኛው የቫቲካን ጉባኤ የዚህን ችግር ስፋት እና ውስብስብነት ለመወሰን እና ለመፍትሄው ተስማሚ ዘዴዎችን ለመንደፍ የተቻለውን ያደርጋል” በማለት የቀድሞው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ጳውሎስ ስድስተኛ መናገራቸውን ካርዲናል ካርሎስ አስታውሰዋል።
ብፁዕነታቸው በመክፈቻ ንግግራቸው ጉባኤው እንዲካሄድ ላደረጉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ ጉባኤውን በመሳተፍ ላይ በሚገኙት ብጹዓን ጳጳሳት፣ ካኅናት፣ ገዳማዊያን እና ገዳማውያት እንዲሁም በምእመናን ስም ልባዊ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
“በሲኖዶሳዊነት ሂደት የቤተ ክርስቲያኒቱ መነሳሳት እያደገ መምጣቱን ተገንዝበናል” ያሉት ብፁዕ ካርዲናል ካርሎስ፥ የታላቁን የእግዚአብሔር ቤተሰብ የወንድማማችነት ትስስር ለማጠናከር እና አጥጋቢ ምላሽ ለመስጠት እንዲሁም አሁን ላጋጠሙን ፈተናዎች ሲኖዶሳዊነት ትክክለኛ ዘይቤ እና ቀዳሚ መሠረት መሆኑን በሂደቱ ወቅት ተረድተናል” ብለዋል።
የወንጌል ተልዕኮውን በተመለከተ በተለይም በቤተ ክህነት የአገልግሎት ዘርፍ የማዳመጥ አስፈላጊነትን በማመን ምእመናን በተለያዩ እና አወንታዊ አመለካከቶች በኩል ያሳዩትን ተሳትፎ አድንቀው፥ ጳጳሳት፣ ካኅናት እና በሐዋርያዊ አገልግሎት ዘርፍ የተሰማሩት በሙሉ በበለጠ ስሜት ኃላፊነታችንን እንዲቀጥሉ አሳስበዋል።
በሲኖዶሱ ሂደት መካከል የሚደረጉ ጥረቶችን በማቀናጀት እውን እንዲሆኑ የሚያደርጉ አበራታች ፍሬዎች እና ፍላጎቶች መኖራቸውን ገልጸዋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ “የብጹዓን ጳጳሳት አንድነት” በሚለው ሐዋርያዊ ሠነዳቸው በአንቀጽ 5 ላይ፥ “ጳጳስ አስተማሪም ደቀ መዝሙርም ነው፤ በመንፈስ ቅዱስ ልዩ ዕርዳታ የቤተ ክርስቲያ ራስ እና እረኛ በሆነው በኢየሱስ ክርስቶስ ስም እውነትን ለምእመናኑ ሲሰብክ አስተማሪም ነው። የጥምቀት ምስጢርን ለተቀበሉት ምዕመናን ከመንፈስ ቅዱስ እንደተሰጣቸው በሳማወቅ፣ የኢየሱስ ክርስቶስን ድምፅ ለመላው ሕዝብ በማሰማት እና እምነት እንዳይሳሳት በማድረግ ደቀ መዝሙር ነው” ማለታቸውን ብፁዕ ካርዲናል ካርሎስ አስታውሰዋል።
“ስለዚህ የመንጋው መጋቢ እንደመሆናችን ታላቅ እምነት ይዘን ጥረታችንን በቁርጠኝነት እና በተስፋ መቀጠል አለብን” ብለው፥ በየደረጃው የቤተ ክህነት ሥልጣንን በሚያለማምድ የቤተ ክርስቲያኒቱ አስተምህሮ መሠረት ወንድሞቻችን የሆኑ ጳጳሳትን ጨምሮ በካህናት እና በምዕመናን መካከል ያለው አንድነት እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል። በሚቀጥሉ ሳምንታትም ውስጥ በዚህ እምነት በመጓዝ የእግዚአብሔርን ቃል እና ከወንድሞቻችን እና እህቶቻችን የሚወጡ ቃላትን በማዳመጥ መንፈስ ቅዱስ በውስጣችን የሚዘራውን ዘር እርስ በርስ እንጋራለን” ብለዋል።
ወደ ሚሲዮናዊት እና ሲኖዶሳዊት ቤተ ክርስቲያን የሚደረገውን ጉዞ ጥቅም በመመልከት እና በእግዚአብሔር በረከት በመንፈስ ቅዱስ ዕርዳታ ጽኑ ተስፋ እናድርግ ብለው፥ በዚህ ምድራዊ ሕይወት ውስጥ ሙሉ የሆነ ነገር እንደሌለ ዘወትር በማስታወስ ስኬቶቻችን በጉዞአችን ወቅት እንቅፋት እንዳያደናቅፈን እና እስከ መጨረሻው ጸንተን እንድንቆይ የሚያደርጉን ማበረታቻዎች ብቻ ናቸው” ብለዋል።
በዚህ ረገድ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቤነዲክቶስ 16ኛ “የድነት ተስፋ” በሚለው ሐዋርያዊ ሠነዳቸው የተናገሩትን ማስታወስ ተገቢ እንደሆነ በመግለጽ፥ “በክርስትና እምነት መሠረት ‘መቤዠት ወይም መዳን’ እንዲሁ የተሰጠን ሳይሆን የእግዚአብሔር ቤዛነት እምነት የሚጣልበት ተስፋ በመሆኑ አድካሚ ቢሆንም አሁን ያለንበትን ሁኔታ መጋፈጥ እንችላለን፤ ወደ ግብ የሚመራ እና ይህ ግብም የክርስትናን ጉዞ ጥረት ለማስረዳት በቂ ተቀባይነት ያለው ሊሆን ስለሚችል ወደዚህ ግብ እንደምንደርስም እርግጠኞች መሆን እንችላለን” ማለታቸውን አስታውሰዋል።
ከ2014 ዓ. ም. ጀምሮ በመደረግ ላይ ባለው የሲኖዶሳዊነት ጉዞ አማካይነት ቤተ ክርስቲያኖቻችንን እንዳናድስ የሚያግዱ እውነተኛ ችግሮችን ብንመለከትም፣ በዘመናችን አስቸጋሪ ሁኔታዎች መካከል ብርሃን የሚሰጥ ወንድማማችነት እና የቤተ ክርስቲያን ድጋፍ በተለይ የምዕመናን እና የሐዋርያዊ አገልግሎት ሠራተኞቻችን ቀናተኛነት እና በተስፋ መሞላታቸውን እንደተገነዘቡ ብጹዕ ካርዲናል ካርሎስ ገልጸዋል።
በዚህ መንገድም “የብጹዓን ጳጳሳት አንድነት” በሚለው ሐዋርያዊ ሠነድ በአንቀጽ 6 ላይ የተገለጸውን ተጨባጭ ለማድረግ፥ “ቅዱስ ሲኖዶስ ከጊዜ ወደ ጊዜ የእግዚአብሔርን ሕዝብ ለመስማት የሚያስችል ልዩ መሣሪያ መሆን አለበት፤ ከሁሉ በፊት መንፈስ ቅዱስ ለሲኖዶስ አባቶች የማዳመጥ፣ እግዚአብሔርን የመስማት እና የሚፈልገው እስኪፈጸም ድረስ የሕዝቡን ጩኸት የማዳመጥ ችሎታ እንዲሰጣቸው እንለምናለን” ብለዋል።
በመጨረሻም ዛሬ በምንጀምረው የሲኖዶስ ጉባኤ፥ “ሁለት ወይም ሦስት ሆናችሁ በስሜ በሚትሰበሰቡበት በዚያ ሥፍራ እኔ በመካከላሁ እሆናለሁ” ያለውን የኢየሱስ ክርስቶስ የተስፋ ቃል መገንዘብ ወቅታዊ እና አስፈላጊ መሆኑን ገልጸው፥ “እራሳችንን ከመንፈስ ቅዱስ ለመማር እንፍቀድ! በእርሱ ለሚታመኑት እግዚአብሔር ምን ያህል መልካም እንደሆነ እንወቅ!” ብለው፥ የ16ኛው የቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ ተወካይ እና ሊቀ መንበር ብጹዕ ካርዲናል ካርሎስ አጊያር በመጨረሻም ቅድስት ሥላሴ እና የቤተ ክርስቲያን እናት እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በጉባኤው ወቅት አብረዋቸው እንዲሆኑ በመለመን የመክፈቻ ንግግራቸውን ደምድመዋል።