ዲጂታል የወንጌል ልኡካን ወንጌልን በማኅበራዊ ሚዲያ አማካይነት በማወጅ ላይ እንደሚገኙ ተገለጸ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
በካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን የዲጂታል ወንጌል ልኡካን በሐዋርያው ጴጥሮስ መካነ መቃብር ዙሪያ በአካል እና በመስመር ላይ በመሰባሰብ እሑድ ከሰዓት በኋላ ተገናኝተዋል። “መንፈስ ለአብያተ ክርስቲያናት የሚናገረውን ጆሮ ያለው ይስማ” (ራዕ 2፡29) በሚል መሪ ቃል እሑድ ጥቅምት 10/2017 ዓ. ም. የተከበረው የዓለም የተልዕኮ ቀን የተዘጋጀው በቀሌምንጦስ አዳራሽ ውስጥ እንደነበር ታውቋል።
ዝግጅቱ ላይ በቅድስት መንበር የኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ኃላፊ እና የሲኖዶሱ የመረጃ ኮሚሽን ፕሬዝዳንት ዶ/ር ፓውሎ ሩፊኒ፣ በቅድስት መንበር የኮሙዩኒኬሽን ጽሕፈት ቤት ዋና ጸሐፊ ሞንሲኞር ሉሲዮ ሩዪዝ እና የቅዱስ ሲኖዶስ ጠቅላይ ጽሕፈት ቤት ምክትል ጸሐፊ ብጹዕ አቡነ ሉዊስ ማሪን ደ ሳን ማርቲን ተገኝተዋል።
በዲጂታል ተልዕኮ ውስጥ አብሮ መሆን
የኮሙዩኒኬሽን ጽሕፈት ቤት ዋና ጸሐፊ ሞንሲኞር ሉሲዮ ሩይዝ እንደገለጹት፥ ለወንጌል ልኡካን እና ለካቶሊክ ዲጂታል ተጽእኖ ፈጣሪዎች የተዘጋጀው መጪው የኢዮቤልዩ በዓል፥ ከወጣቶች የኢዮቤልዩ በዓል ጥቂት ቀደም ብሎ ማለትም ከሐምሌ 21-22/2017 ዓ. ም. እንደሚከበር ተናግረዋል። ሞንሲኞር ሉሲዮ ሩይዝ በገለጻቸው በዲጅታል ሲኖዶስ በኩል የተከናወኑ ሥራዎችን እና ከውስጡ የተገኘውን የመደማመጥ ሂደት በማድነቅ ትልቅ ለውጥ መመዝገቡንም ጠቁመዋል።
ውጥኑ ሲጠናቀቅ፥ “ቤተ ክርስቲያን ታዳምጣችኋለች” በሚል መሪ ሃሳብ የተጀመረው የሥራ ዕቅድ በዲጂታሉ ዘርፍ ዘወትር በኅብረት እየተመራ ተልዕኮውን እንደሚቀጥል ተናግረው፥ ወደ ፊት የምትጓዝ ቤተ ክርስቲያን ከሌሎች ጋር ለመገናኘት፣ ሌሎችን ለመፈወስ እና ወንጌልን ለመመስከር የሚሹ ደቀ መዛሙርትን ያቀፈች መሆኑን አስረድተዋል። ሞንሲኞር ሩዪዝ በመጨረሻም፥ “ተስፋ በሚያስፈልገው ዓለም ውስጥ የእግዚአብሔርን ደስታ የሚያሳዩ ውብ ሥራዎችን አብሮ መሥራትን እና ማለምን እንቀጥል” በማለት ንግግራቸውን አጠቃልለዋል።
የአዲሱ ዓለም የወንጌል ልኡካን
የቅዱስ ሲኖዶስ ጠቅላይ ጽሕፈት ቤት ምክትል ጸሐፊ ብጹዕ አቡነ ሉዊስ ማሪን ደ ሳን ማርቲንም በንግግራቸው፥ ኢየሱስ ክርስቶስ ተራ ምናባዊ አምሳያነት ወይም ዲጂታል ማንነት ያለው ሳይሆን ነገር ግን ሕያው የእግዚአብሔር ልጅ መሆኑን አስታውሰው፥
የዲጂታል ወንጌል ልኡካን “መንፈስ ለአብያተ ክርስቲያናት የሚናገረውን ጆሮ ያለው ይስማ” የሚለውን የዘንድሮ የዓለም የተልዕኮ እሑድ መሪ ሃሳብ እንዲቀበሉ በማሳሰብ፥ የራሳቸውን ምቾት ትተው ክርስቲያናዊ ደስታን ለመመስከር እና ሁሉንም ወደ ግብዣው ለመጋበዝ የተጠሩ መሆናቸውን ተናግረዋል። የወንጌል ተልዕኳቸው ከእንቅፋቶች እና ታሪካዊ ስኅተቶች ጋር የተሳሰረ እንጂ ፈጽሞ ጎራዎችን ለመፍጠር የሚፈልግ መሆን እንደሌለበትም አሳስበዋል።
የዲጂታል ተጽእኖ ፈጣሪዎች ምስክርነት
በዝግጅቱ ወቅት በርካታ ወጣት ተፅእኖ ፈጣሪዎች በተለያዩ ቋንቋዎች ጸሎታቸውን ያቀረቡ ሲሁን፥ ከሊባኖስ የመጡ መንታ ወጣቶች በዲጂታል የወንጌል ተልዕኮ አገልግሎት ሕይወታቸው እንዴት እንደተነካ ለተሳታፊዎች አስረድተዋል። አሁን በመካከለኛው ምሥራቅ በመስመር ላይ አገልግሎት የክርስትናን ውበት ለሌሎች ለመካፈል ቆርጠው መነሳታቸውን ገልጸዋል።ተሳታፊዎቹ ወንድማማችነትን፣ መደማመጥን፣ ደስታን፣ ስቃይን፣ ጥማትን፣ እና እግዚአብሔርን መፈለግ ጨምሮ በወንጌል ተልዕኮዋቸው ላይ ያተኮሩ ጥቂት መልዕክቶችን እንዲጽፉ ተጋብዘዋል።
በትህትና የሚፈጸም የወንጌል ተልዕኮ
በዝግጅቱ ላይ የተገኙት በቅድስት መንበር የኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ኃላፊ እና የሲኖዶሱ የመረጃ ኮሚሽን ፕሬዝዳንት ዶ/ር ፓውሎ ሩፊኒ፥ በዲጂታል መድረኮች ላይ የሚያገለግሉ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን የወንጌል ልኡካን ተነሳሽነታቸውን ከቅዱስ ጳውሎስ ሕይወት እንዲያገኙ ጋብዘዋል። በዘመናዊው ኅብረተሰብ ላይ እየደረሰ ላለው ጉዳት ኃላፊነትን በመውሰድ ለመፈወስም የበኩላቸውን እንዲወጡ በማሳሰብ፥ “ከትሕትና ጋር የዘመናችን ጨው እና እርሾ ለመሆን እግዚአብሔር ይርዳን” ብለዋል።
የአሕዛብ ሐዋርያ የሆነው ቅዱስ ጳውሎስ በሕዝቡ መካከል ሆኖ ከፖለቲካ አስተዳዳሪነት፣ ከቢሮ ኃላፊነት ወይም ከብልህ የዕቅድ አውጪነት በተቃራኒ፥ ሁሉም ነገር ለሁሉም ሰው እንዲሆን ማድረጉን ተናግረው፥ሐዋርያው እግዚአብሔርን በትህትና እና በእንባ ማገልገሉን አስታውሰዋል።
ወጣት የወንጌል ልኡካን የግል ፍላጎቶችን ወደ ጎን በመተው፣ የስልጣን ጥማትን በመቃወም፣ ከልዩነት እና ከመከፋፈል ይልቅ በኅብረት ተመሳሳይ መንገድን እንዲከተሉ ጋብዘዋል። ሞንሲኞር ሩዪዝ በመጨረሻም፥ “እስከ ምድር ዳርቻ ድረስ ሂዱ!” የሚለውን የወንጌላዊነት መርህ በመጥቀስ የዲጂታል ሲኖዶስ ዝግጅትን በጸሎት ደምድመዋል።