ፈልግ

አራተኛ የቅዱስ ሲኖዶስ ጠቅላላ ጉባኤ፥ አራተኛ የቅዱስ ሲኖዶስ ጠቅላላ ጉባኤ፥   (Vatican Media)

የቅዱስ ሲኖዶስ ጠቅላላ ጉባኤ፥ የጳጳስ እና የምእመናን ሚና በሚሉ ርዕሦች ላይ ተወያየ

ረቡዕ መስከረም 29/2017 ዓ. ም. ከሰዓት በኋላ በኢየሱሳውያን ማኅበር ጠቅላይ ቤት እና በቅዱስ አጎስጢኖስ ገዳም ውስጥ የተዘጋጁ ሁለት ስብሰባዎች በጳጳስ እና በሕዝበ እግዚአብሔር ሚና ላይ ውይይቶች ተካሂዶባቸው ነገረ-መለኮታዊ እና የሐዋርያዊ እረኝነት ግንዛቤዎችን ለተሳታፊዎች ማስጨበጡ ታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በቫቲካን ከመስከረም 22 እስከ ጥቅምት 17/2017 ዓ. ም. ድረስ እየተካሄደ ያለው የቅዱስ ሲኖዶሱ ጠቅላላ መደበኛ ጉባኤ በአሁኑ ወቅት የጉባኤው አባላትን እያሳተፉ ያሉ ርዕሦችን በኅብረት ለመመልከት ወደ ተለያዩ የስብሰባ ማዕከላት ጠርቶ ውይይቶችን በማድረግ ላይ እንደሚገኝ ታውቋል።

በዚህም መሠረት የመጀመሪያው የውይይት መድረክ ረቡዕ መስከረም 29/2017 የተካሄደ ሲሆን ሁለተኛው ጥቅምት 6/2017 ዓ. ም. ሊካሄድ ዝግጅት እየተካሄደ እንደሚገኝ ታውቋል። የጉባኤው ተሳታፊዎች በእነዚህ መድረኮች ላይ በማኅበራዊ ሚዲያ በኩል ሆነ በአካል ተገኝተው በአራት ሥነ-መለኮታዊ እና የሐዋርያዊ አገልግሎት መድረኮች መካፈል እንደሚችሉ ተገልጿል።

ለመስከረም 29/2017 የተዘጋጀ መድረክ
ረቡዕ መስከረም 29/2017 ከሰዓት በኋላ ጀምሮ እስከ ማምሻው የተካሄደው የመጀመሪያው መድረክ ሁለት ዝግጅቶች በተመሳሳይ ጊዜ የቀረቡበት እንደ ነበር ተመልክቷል። አንደኛው፥ “የእግዚአብሔር ሕዝቦች ተልዕኮ” በሚል ርዕሥ በኢየሱሳውያን ማኅበር ጠቅላይ ቤት የስብሰባ አዳራሽ ውስጥ የተስተናገደ ሲሆን ሁለተኛው፥ “የጳጳስ ሚና እና ስልጣን በሲኖዶሳዊት ቤተ ክርስቲያን” በሚል ርዕሥ በቅዱስ አጎስጢኖስ ገዳም ጳጳሳዊ ማዕከል የስብሰባ አዳራሽ የተካሄደ መድረክ እንደ ነበር ታውቋል።

በእያንዳንዱ መድረክ ላይ የነገረ-መለኮት ሊቃውንት፣ የሕገ ቀኖና ባለሙያዎች እና ብጹዓን ጳጳሳት የተገኙበት ሲሆን፥ የመጀመሪያ ክፍል ጥናታዊ ንግግሮች የቀረቡበት፣ ሁለተኛው ተሳታፊዎች ጥያቄዎችን እንዲያቀርቡ ዕድል የተሰጠበት እንደ ነበር ታውቋል።

በተለያዩ ባለሙያዎች የበለፀገ የሲኖዶስ ጉባኤ
በማሳሰቢያው መሠረት እነዚህ መድረኮች በ16ኛው የቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ መጀመሪያ ክፍለ ላይ በቀረቡ ነገረ-መለኮታዊ እና የሐዋርያዊ እረኝነት አስፈላጊነት ላይ ግንዛቤን በመስጠት በተለያዩ የቤተ ክርስቲያን የእምነት ጉዳዮች ላይ ያለውን ሥነ-መለኮታዊ፣ ሕገ-ቀኖናዊ እና ሐዋርያዊ እረኝነት ለማስቀጠል የነገረ-መለኮት እና የሕገ ቀኖና ሊቃውንት ለሲኖዶሳዊነት ትርጉም በመስጠት የበኩላቸውን አስተዋፅዖ በማድረግ ምላሽ የሰጡበት እንደ ነበር ተመልክቷል።

ጥቅምት 6/2017 ዓ. ም. ሊካሄድ የታቀደው ሁለተኛው መድረክ
መጪው ረቡዕ ጥቅምት 6/2017 ዓ. ም. ሁለት ተጨማሪ የውይይት መድረኮች ሊዘጋጁ የታቀዱ ሲሆን፥ የነገረ-መለኮት እና የሐዋርያዊ እረኝነት መድረኮች በተመሳሳይ ጊዜ እንደሚካሄዱ ተገልጿል።

የመጀመሪያው “በዓለም ዙሪያ በምትገኝ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን እና በቅድስት መንበር መካከል ያለው የጋራ ግንኙነት” በሚል ርዕሥ በኢየሱሳውያን ማኅበር ጠቅላይ ቤት የሚካሄድ ስብሰባ ሲሆን ሁለተኛው “በቅዱስ ሲኖዶስ ውስጥ የጳጳስ ሚና እና ሥልጣን” በሚል ርዕሥ በቅዱስ አጎስጢኖስ ገዳም ውስጥ የሚዘጋጀ መድረክ እንደሚሆን ታውቋል።

በእነዚህ ሁለት ዝግጅቶች ላይ ከሲኖዶሱ ተሳታፊዎች በተጨማሪ በቅድስት መንበር መግለጫ ክፍል እውቅና ያላቸው ጋዜጠኞች እና ፍላጎት ያለው ማንኛውም ሰው እንዲሳተፍ መጋበዙ ታውቋል።

 

10 October 2024, 18:38