ካርዲናል ዙፒ ከሊቀ ጳጳስ አቡነ አንቶኒ ጋር ተገናኝተው በሰብዓዊ ጉዳዮች ላይ ተወያዩ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
በሩሲያ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ልዩ የሰላም መልዕክተኛ ብፁዕ ካርዲናል ማቴዎ ዙፒ እና በሞስኮ ፓትርያርክ ጽሕፈት ቤት የውጪ ግንኙነት መምሪያ ፕሬዚደንት እና የቮልኮላምስክ ከተማ ሊቀ ጳጳስ አንቶኒ መካከል ማክሰኞ ጥቅምት 5/2017 ዓ. ም. የተደረገው ውይይት ከዩክሬን ጦርነት ጋር በተያያዙ ሰብዓዊ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ እንደ ነበር ተገልጿል።
ውይይቱ የተካሄደው ብጹዕ ካርዲናል ማቴዎ ዙፒ በሩሲያ ሁለተኛ ዙር ጉብኝት ባደረጉበት በሁለተኛው ቀን ሲሆን፥ ሰላምን ለማምጣት ተስፋ የተጣለበት ነው የተባለው ይህ ውይይት፥ የዩክሬን ሕጻናት ከቤተሰቦቻቸው ጋር እንዲዋሃዱ፣ ሩሲያ እና ዩክሬይን እስረኞች እንዲለዋወጡ ለማድረግ ያለመ እንደሆነ ታውቋል።
ከፓትርያርክ ኪሪል ጋር የተደረገ የሰላምታ ልውውጥ
በፓትርያርኩ ጽሕፈት ቤት የውጪ ግንኙነት መምሪያ ፕሬዚደንት እና የቮልኮላምስክ ከተማ ሊቀ ጳጳስ አቡነ አንቶኒ በሞስኮው ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ ኪሪል እና በመላው የሩስያ ሕዝብ ስም ለብጹዕ ካርዲናል ማቴዎ ዙፒ እና ለልኡካን ቡድናቸው ሰላምታ ካቀረቡላቸው በኋላ የፓትርያርኩን መግለጫ በንባብ አሰምተዋል።መግለጫው፥ ተዋዋይ ወገኖች በውይይቱ ወቅት በዩክሬን ስላለው ጦርነት እና ሌሎች የጋራ ጥቅሞችን በሚመለከቱ ሰብዓዊ ጉዳዮች ላይ መምከራቸውን አስታውቋል።
የብጹዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ ኪሪል የልዑካን ቡድን አካል የነበሩት ሊቀ ጳጳስ አቡነ አንቶኒ ለርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ መልዕክተኞች ባደረጉት ንግግር፥ ፓትርያርኩ “የቅድስት መንበር ልኡካንን ወደ ሞስኮ ስለላካችኋቸው ቅዱስነታቸው እናደንቃለን” ማለታቸውን ጠቅሰዋል።
ከኮሚሽነር ሎቮቫ-ቤሎቫ ጋር መገናኘት
ካርዲናል ዙፒ ወደ ሩሲያ ባደረጉት የመጀመሪያ ዙር ተልዕኮ በፕሬዚዳንት ፑቲን የተሾሙትን የሩሲያ ፕሬዚዳንታዊ የሕፃናት መብት ኮሚሽነር ማርያ ሎቮቫ ቤሎቫን ማግኘታቸው ሲታወስ፥ ማክሰኞ ጥቅምት 5/2017 ዓ. ም. ሁለቱ ተገናኝተው ገንቢ ውይይት ማድረጋቸውን ኮሚሽነሯ በቴሌግራም ቻናላቸው ላይ ከጻፉት መግለጫ ለማወቅ ተችሏል።
“በሩሲያ ፌዴሬሽን ውስጥ ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ልዩ የሰላም መልዕክተኛ ብፁዕ ካርዲናል ማቴዎ ዙፒ እና በሩስያ የቅድስት መንበር እንደራሴ ጽሕፈት ቤት ጋር ያለው ትብብር ከአንድ ዓመት በላይ ሲካሄድ ቆይቷል” በማለት አጽንኦት ሰጥተዋል።
በብጹዕ ካርዲናል ማቴዎ ዙፒ እና በወይዘሮ ሎቮቫ-ቤሎቫ መካከል የተደረገው ውይይት ያተኮረው በግዳጅ ወደ ሩሲያ የተወሰዱ የዩክሬን ሕጻናትን ወደ ዩክሬይን በመመለስ ላይ እንደ ነበር የተገለጸ ሲሆን፥ እንደ ዩክሬን መንግሥት ገለጻ፥ በግዳጅ ወደ ሩሲያ የተወሰዱ የዩክሬን ሕጻናትን ቁጥር ከ19,000 በላይ እንደሆኑ ይነገራል። ቅድስት መንበር በጀመረችው የሽምግልና ጥረት እስካሁን ጥቂቶቹ ከቤተሰቦቻቸው ጋር ሊገናኙ መቻላቸው ታውቋል።
ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጋር መገናኘት
ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ልዩ የሰላም መልዕክተኛ ብፁዕ ካርዲናል ማቴዎ ዙፒ ሰኞ ሞስኮ ሲደርሱ ከአገሪቱ የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌ ላቭሮቭ ጋር ተገናኝተው በዩክሬን ውስጥ በተፈጠረው ግጭት ምክንያት በሰብዓዊ ዕርዳታ አቅርቦት ላይ ስላለው ትብብር እና ሌሎች ዓለም አቀፍ ጉዳዮች ላይ መወያይታቸው ሲታወስ፥ በዕለቱ ከሚኒስቴሩ የወጣው መግለጫ፥ በሩስያ እና በቅድስት መንበር መካከል የተደረጉ ውይይቶች ገንቢ ውጤቶችን ማሳየታቸውን አጽንዖት ሰጥቷል።