ካርዲናል ፓሮሊን በዩክሬይን አውዳሚ ጦርነት ከመባባሱ በፊት መቆም እንዳለበት አሳሰቡ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ ካርዲናል ፒዬትሮ ፓሮሊን ዓለም አቀፉ የጦር ወንጀለኞች ፍርድ ቤት የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንጃሚን ኔታንያሁን በጋዛ በመካሄድ ላይ በሚገኘው ጦርነት የጦር ወንጀለኛ ብሎ የእስር ማዘዣ በማውጣቱ ውሳኔ ላይ ምንም ዓይነት መግለጫ ባይሰጡም በዩክሬን ጦርነት የረዥም ርቀት ሚሳኤሎችን መዘርጋት እና ሰፋፊ የዓለም ግጭቶች ስጋት ጨምሮ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የተከሰቱት ሁኔታዎች ቅድስት መንበርን በጥልቅ እንዳስጋት ገልጸዋል።
የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ ካርዲናል ፒዬትሮ ፓሮሊን፥ እስራኤል በጋዛ ባካሄደችው ጦርነት የሟቾች ቁጥር ከ44,000 በላይ መሆኑ “የዘር ማጥፋት” ተብሎ ሊፈረጅ ይችላል” በሚለው ላይ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የሰጡትን አስተያየት በማስመልከት ዓርብ ኅዳር 13/2017 ዓ. ም. በሮም በተካሄደው የመጽሐፍ ምረቃ ሥነ-ሥርዓት ላይ ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ ሰጥተዋል።
ካርዲናል ፒዬትሮ ፓሮሊን፥ ለጥያቄው በሰጡት ምላሽ፥ “ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የቅድስት መንበርን አቋም ገልጸዋል” ብለው፥ የዘር ማጥፋት ጽንሰ-ሐሳብን ለመወሰን ቴክኒካዊ መስፈርቶች ስላሉ ጉዳዩ በጥልቀት ሊጠና እንደሚገባ ተናግረዋል።
ዩክሬይንን በተመለከተ ያለው ስጋት
ካርዲናል ፒዬትሮ ፓሮሊን በእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንጃሚን ኔታንያሁን ላይ የተላለፈውን የእስር ማዘዣ ውሳኔ ቢሰሙም የቅድስት መንበር አቋም ጦርነቱ እንዲቆም የሚል መሆኑን በድጋሚ ገልጸዋል። በዩክሬን ካለው ሁኔታ ጋር በተያያዘ የብሪታንያ እና የአሜሪካ-ሠራሽ ሚሳኤሎችን ወደ ሩሲያ ግዛት ለመተኮስ መወሰኑ ሊያስከትል የሚችለው መዘዝ እና ፑቲን ዓለም አቀፋዊ ግጭት እናይከሰት ያስተላለፉት ማስጠንቀቂያ ሁለቱም ተመሳሳይ ጭንቀት መፍጠራቸውን ገልጸዋል።
“የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስን ሃሳቦች እና ስጋቶች አስተጋባለሁ” ያሉት ካርዲናል ፒዬትሮ ፓሮሊን፥ በሩስያ እና በዩክሬይን መካከል የሚካሄደው ጦርነት ተባብሶ ከቁጥጥር ውጭ ሊሆን ስለሚችል በጊዜ ሊቆም እንደሚገባ አሳስበው፥ አለበለዚያ ግን ማንም ሊገምተው የማይችለው ውጤት ሊያከትል እንደሚችል አስጠንቅቀዋል።
እስረኞችን መለዋወጥ እና ሕፃናትን ወደ አገራቸው መመለስ
በግጭቱ አስከፊነት ላይ ያሰላሰሉት ካርዲናል ፒዬትሮ ፓሮሊን፥ በዚህ የጦርነት ወቅት ከዚህ የከፋ ታይቷል ብሎ ማመን ይከብዳል” ብለው፥ አክለውም “አሁን ያለው ሁኔታ በጣም አሳሳቢ ነው” ሲሉ ገልጸዋል።
ቅድስት መንበር ለእስረኞች ልውውጥ መንገዶችን ለማመቻቸት እና በግዳጅ ወደ ሩሲያ የተወሰዱ የዩክሬን ሕጻናት ደኅንነትን ለማስጠበቅ ጥረት ማድረግ መቀጠሏን ካርዲናል ፓሮሊን አረጋግጠዋል። ይህን በተመለከተ ምንም አዲስ ነገር ባይኖርም ቫቲካን በጥረቶቿ ለመጽናት ያላትን ቁርጠኝነት በድጋሚ አረጋግጠው፥ ሰብዓዊ ጉዳዮች ውሎ አድሮ ወደ ድርድር የሚወስዱ እርምጃዎች መሆናቸውንም ተናግረዋል።
በጋዛ ላይ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ አስተያየት
“በጋዛ የሟቾች ቁጥር ከ44,000 በላይ በመሆኑ ይህ ክስተት የዘር ማጥፋት ባሕሪያትን ሊይዝ ይችላል” በማለት ባለሙያዎች ያቀረቡትን በመጥቀስ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ስለ ሰጡት አስተያየት ሲናገሩ፥
“ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ በዓለም አቀፍ ሕግ በተገለጹት ቴክኒካዊ መመዘኛዎች ላይ በመመርኮዝ በጥንቃቄ ማጥናት ያስፈልጋል” በማለት ደጋግመው መናገራቸው የቅድስት መንበርን አቋም የሚያንፀባርቅ መሆኑን ካርዲናል ፓሮሊን ተናግረው፥ እነዚህን በመሰሉ ከባድ ጉዳዮች ላይ መደምደሚያ ከማድረግ በፊት ጥብቅ ምርመራን ማድረግ የቫቲካን አቋም መሆኑንም አስረድተዋል።
በፀረ-ሴማዊነት ላይ ያለው የጸና አቋም
ቫቲካን ፀረ-ሴማዊነትን የሚያወግዝ የማያወላውል አቋም አላት ሲሉ በድጋሚ ያረጋገጡት የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ ካርዲናል ፒዬትሮ ፓሮሊን፥ “የቅድስት መንበር አቋም ግልጽ ነው” ብለው፥ “ፀረ ሴማዊነትን ሁልጊዜ አውግዘናል አሁንም እንቀጥላለን፣ በማያሻማ ውድቅ ለማድረግ ሁኔታዎችን በማመቻቸት በሁሉም መልኩ እንታገላለን” ብለዋል።