ፈልግ

ብጹዕ ካርዲናል ሉዊስ አንቶኒዮ ታግለ ብጹዕ ካርዲናል ሉዊስ አንቶኒዮ ታግለ 

ብጹዕ ካርዲናል ታግለ ልብን በኢዮቤልዩ በዓል ላይ ማድረግ እንደሚገባ አሳሰቡ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በቅርቡ ‘Dilexit nos’፣ ሲተረጎም “እርሱ ወዶናል” በሚል ርዕሥ ይፋ ባደረጉት ሐዋርያዊ መልዕክት ላይ ማብራሪያ የሰጡት ብጹዕ ካርዲናል ሉዊስ አንቶኒዮ ታግለ፥ የቅዱስነታቸውን ሐዋርያዊ መልዕክቶችን እና ተግባሮቻቸውን ለመረዳት የኢየሱስ ልብ ጠቃሚ መሆኑን ለቫቲካን ዜና ገልጸዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በቅድስት መንበር ለሕዝቦች የወንጌል አገልግሎት ማስፋፊያ ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት አስተባባሪ ብጹዕ ካርዲናል ሉዊስ አንቶኒዮ ታግለ ስለ አዲሱ ሐዋርያዊ መልዕክት ሲገልጹ፥ “መንፈሳዊ ማንነታችንን የሚቀርፅ እና ከሌሎች ጋር እንድንገናኝ የሚያደርገን ልባችን ነው” የሚለው መልዕክት ቅዱስነታቸው “እርሱ ወዶናል” በሚል ርዕሥ ጥቅምት 14/2017 ዓ. ም. ይፋ ያደረጉት ሐዋርያዊ መልዕክት በውስጡ ከያዛቸው ጠቃሚ ምንባቦች መካከል አንዱ እንደሆነ አስረድተዋል።

የቅዱስነታቸው አዲሱ ሐዋርያዊ መልዕክት ከዚህ በፊት ይፋ ያደረጓቸውን ሁለት ሐዋርያዊ መልዕክቶች እነርሱም “ውዳሴ ላንተ ይሁን” እና “ሁላችን ወንድማማቾች ነን” ጨምሮ ሌሎች ማኅበራዊ እና ሐዋርያዊ መልዕክቶቻቸውን ለመረዳት እጅግ ጠቃሚ ነው።

“እርሱ ወዶናል” የሚለው አዲሱ ሐዋርያዊ መልዕክት በሲኖዶሳዊነት ላይ የተካሄደውን ጠቅላላ ጉባኤ ጨምሮ ከጥቂት ሳምንታት በኋላ የሚጀምረውን የ2025 (እ.አ.አ) የኢዮቤልዩ በዓል እና ሌሎች መንፈሳዊ ክስተቶችን የበለጠ ለመረዳት ጠቃሚ ሊሆን እንደሚችል ብፁዕ ካርዲናል ሉዊስ አንቶኒዮ ታግሌ አስረድተዋል።

በቅድስት መንበር ለሕዝቦች የወንጌል አገልግሎት ማስፋፊያ ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት አስተባባሪ ብጹዕ ካርዲናል ሉዊስ አንቶኒዮ ታግለ ስለ አዲሱ ሐዋርያዊ መልዕክት እና በፊሊፒንስ በጣም ተስፋፍቶ ስለሚገኘው እና በወጣትነት ዕድሜያቸው ብዙ ስለተማሩት የኢየሱስ ቅዱስ ልብ በማስመልከት ከቫቲካን የዜና አገልግሎት ጋር ቃለ ምልልስ አድርገዋል።

“ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እኛ በጳጳሳት ሲኖዶስ ላይ ትኩረት በሰጠንበት ወቅት “እርሱ ወዶናል” የሚለውን አዲሱን ሐዋርያዊ መልዕክት ይፋ በማድረጋቸው አስገርመውናል” ያሉት ብጹዕ ካርዲናል ሉዊስ አንቶኒዮ ታግለ፥ የዚህ ሐዋርያዊ መልዕክት ይፋ መሆን ያልተጠበቀ ቢሆንም፣ በቅዱስ ልብ የተመሰለው እና ኢየሱስ ክርስቶስ ለእኛ ያለውን ፍቅር የሚገልጽ መልዕክት ይፋ ማድረጋቸው እንዳላስገረመቸው ገልጸው፥ በዚህም ማኅበረሰባዊ ይዘት ያሏቸውን ሁለት ሐዋርያዊ መልዕክቶች ማለትም “ውዳሴ ላንተ ይሁን” እና “ሁላችን ወንድማማቾች ነን” የሚሉትን የኢየሱስ ክርስቶስ ተግባራት የሚገልጽ ሥነ-መለኮታዊ መሠረትን ይበልጥ ግልጽ ለማድረግ መንገድ አዘጋጅተዋል።

የኢየሱስን ፍቅር ስናገኝ በሌሎች ሰዎች ውስጥ ያለውን ወንድምነት እና እህትነት (ሁላችን ወንድማማቾች ነን) እንድናይ እና ለጋራ መኖሪያ ምድራችን (ውዳሴ ላንተ ይሁን) በማሰብ ትሁት እና ኃላፊነት የሚሰማቸው ሰዎች እንድንሆን ያስችለናል” ያሉት ብጹዕ ካርዲናል ሉዊስ አንቶኒዮ ታግለ፥ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ሐዋርያዊ ጽሑፎች እና ንግግሮች በቋሚነት በኢየሱስ ክርስቶስ ሰውነት እና ተልዕኮው ላይ ባለን እምነት ላይ የተመሠረቱ እንደሆኑ በማስረዳት፥ “እርሱ ወዶናል” የሚለውን የአዲሱ ሐዋርያዊ መልዕክት ዱካ ወይም ፍሬ ለማግኘት ማኅበረሰባዊ ይዘት ያሏቸውን ሁለቱን ሐዋርያዊ መልዕክቶችን እንደገና ማንበብ እንደሚገባ አሳስበዋል።

በፊሊፒንስ ለቅዱስ ልበ ኢየሱስ የሚሰጥ ክብር ሰፊ እንደሆነ የገለጹት ብጹዕ ካርዲናል ሉዊስ አንቶኒዮ ታግለ፥ ከኢየሱስ ቅዱስ ልብ ጋር ግንኙነት ያላቸው የኢየሱሳውያን እና የጸሎት ሐዋርያነት ማኅበራትን ጨምሮ ሌሎች በርካታ ገዳማውያን እና ገዳማውያት በሀገረ ስብከቶች፣ በቁምስናዎች፣ በትምህርት ቤቶች እና በቤተሰቦች ውስጥ ለቅዱስ ልበ ኢየሱስ ክብር እንዲሰጥ ለሚያደርጉት ጥረት ምስጋናቸውን አቅርበውላቸዋል።

በወሩ የመጀመሪያ ዓርብ እና በዋዜማው ከሚደረጉ ጸሎቶች በተጨማሪ የቅዱስ ልብ ምስል በየቤቱ እንዲኖር ማድረግ የተለመደ እንደሆነ ገልጸው፥ የኢየሱስ ልብ ቤተሰቦችን እና ሕዝባቸውን እንዲገዛ እና እንዲያስተዳድር ምሕረቱን እና ፍቅሩን እንደሚለምኑ ተናግረው፥ ይህ ጸሎት የፍትህ እጦት፣ ስግብግብነት፣ ሙስና እና ግዴለሽነት ልባቸው ካቆሰለባቸው ሰዎች የሚመጣ እንደሆነ አስረድተዋል።

ለኢየሱስ ቅዱስ ልብ ክብር መሰጠት ልባችን እርሱን እንዲመስ እና እንዲለውጥ ዘወትር ኢየሱስን መለመን እንዳለብን የሚያሳስብ መሆኑን የገለጹት ብጹዕ ካርዲናል ሉዊስ አንቶኒዮ ታግለ፥ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ ከ1937 ጀምሮ እስከ ዛሬም ድረስ በማኒላ የተካሄደውን ዓለም አቀፍ የቅዱስ ቁርባን ጉባኤን ጨምሮ በአንዳንድ አጋጣሚዎች ኦፊሴላዊ መዝሙር እንዘሚዘመር አስረድተዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ “እርሱ ወዶናል” በሚለው አዲሱ ሐዋርያዊ መልዕክታቸው ውስጥ፥ እንደ ባሕል ተስፋፍቶ ከኢየሱስ ክርስቶስ ልብ ውስጥ ከሚፈልቅ ፍቅር፣ እውነት እና ርኅራኄ ጋር እንዳንገናኝ የሚያደርጉንን ክስተቶች እና መንስኤዎች ገልጸውልናል ያሉት ብጹዕነታቸው፥ ለሕሊና ምርምርራ ዋና መንገድ እንዲሆን ቅዱስ አባታችን የሰጡትን መግለጫ ማንበብ እንደሚገባል አሳስበው፥ ከውስጣችን እና ከእውነተኛ ማንነታችን ጋር ያለን ግንኙነት ቀስ በቀስ እየጠፋ መሆኑን ልባችንን ለማስገንዘብ የመጀመሪያው እርምጃ እንደሆነ አስረድተዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የእግዚአብሔር አገልጋይ ለነበሩት የቤተ ክርስቲያን ልጆች በይፋ የሚሰጡት የቅድስና ማዕረግ ቅዱሳን ስለ ኢየሱስ ልብ ያላቸውን የማይመረመር ፍቅር ሕይወታቸውን እና ተልእኮአቸውን እንዴት እንደለወጠው ምስክርነትን የሚሰጡ በመሆናቸው ነው ብለው፥ ልብን ማደስ የምንችለው በፅንሰ-ሃሳብ ወይም በረቂቅ ነገር ሳይሆን እውነተኛ ሕይወት በኢየሱስ አፍቃሪ ልብ ውስጥ የሚገኝ መሆኑን በማወቅ እንደሆነ አስረድተዋል።

“እርሱ ወዶናል” የሚለው አዲሱ የቅዱስነታቸው ሐዋርያዊ መልዕክት ሲኖዶሳዊት እና ሚስዮናዊት መሆን የምትፈልግ ቤተ ክርስቲያንን የሚያስተምራት ብዙ ነገር እንዳለው የገለጹት ብጹዕ ካርዲናል ሉዊስ አንቶኒዮ ታግለ፥ በቅርቡ በተጠናቀቀው የብፁዓን ጳጳሳት ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ሲኖዶሳዊነት ስለ እርስ በርስ ግንኙነት፣ ከእግዚአብሔር ጋር፣ ቤተ ክርስቲያንን ከሚያዋቅሩ የተጠመቁ ምዕመናን ጋር፣ ከመላው የሰው ልጅ እና ከፍጥረት ጋር የሚያገናኝ መሆኑ ተደጋግሞ መነገሩን ገልጸዋል።

በሚስዮናዊ ሲኖዶሳዊነት ውስጥ የቤተ ክርስቲያን መታደስ ሊሳካ የሚችለው ፍቅር ከሆነው ቅድስት ስላሴ ጋር በእምነት፣ በመታዘዝ እና በትህትና ስንገናኝ ብቻ እንደሆነ ተናግረው፥ ሚስዮናዊ ሲኖዶሳዊነት በመንፈሳዊ አባቶች እና በምእመናን መካከል እንዲሁም በየአገራቱ በሚገኙ ቤተ ክርስቲያናት መካከል የልብ ለልብ ግንኙነት እንዲኖር የሚጠይቅ፣ የሰዎች ልብ በሌሎች ላይ ካለው ጭፍን ጥላቻ እና ራስን ከፍ ከማድረግ ስሜት የጸዳ መሆኑን ማዳመጥ እንደሚችል ገልጸው፥ የሰዎች ግንኙነት በመለኮታዊ ጸጋ የጸዳ ካልሆነ፣ በመንፈስ ቅዱስ እና በመለኮታዊ የፍቅር ነበልባል የሚቃጠል ልብ ከሌለ ሚስዮናዊ ሲኖዶሳዊነት ወደ ቢሮክራሲነት እና ወደ ሃሳብነት ብቻ ሊወርድ እንደሚችል አስረድተዋል።

“እርሱ ወዶናል” በሚለው አዲሱ የቅዱስነታቸው ሐዋርያዊ መልዕክት እና በመጪው የኢዮቤልዩ በዓል የተስፋ ጉዞ መካከል ግንኙነት እንዳለ ይታየኛል ያሉት ብጹዕ ካርዲናል ሉዊስ አንቶኒዮ ታግለ፥ የኢየሱስ ክርስቶትስ ቅዱስ ልብ በሚስዮናዊነት ላይ ያተኮረ እንደሆነ ገልጸው፥ የኢየሱስ ቅዱስ ልብ የተትረፈረፈ መለኮታዊ ፍቅርን ለሰው ልብ እና ለፍጥረታት የሚያመጣ ሚስዮናዊ ልብ እንደሆነ አስረድተዋል።

የኢየሱስ ቅዱስ ልብ መሐሪ ፍቅር ለተሰበረ ዓለም በተለይም በሕይወታቸው ውስጥ ምንም ዓይነት መቤዠት ለማይችሉት ተስፋን እንደሚሰጥ ገልጸው፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በልባችን ውስጥ የኢየሱስን ፍቅር ተቀብለን እንድንፈውስ እና የእርሱ ፍቅር ወደ ሌሎች ሰዎች እና ወደ ማኅበረሰብ መፍሰስን እንዳንከለክል ማሳሰባቸውን ገልጸዋል።

“እርሱ ወዶናል” የሚለው ሐዋርያዊ መልዕክት እያንዳንዳችን የኢየሱስን ፍቅር ለሌሎች የምንካፈል መንፈሳዊ ተጓዦች እንድንሆን የሚያዘጋጀን እና ለመጭው የኢዮቤልዩ በዓል ጠቃሚ የሆነ መንፈሳዊ እና ሚሲዮናዊ ግብዓት ሲሆን ይህ ፍቅር ሁሉንም ልብ ከፍርሃት፣ ከኩራት፣ ከራስ ወዳድነት፣ ከቸልተኝነት፣ ከበቀል እና ከተስፋ መቁረጥ ነፃ የሚያወጣ እንደሆነ ገልጸው፥ እርሱ የሚወደን በመሆኑ ተስፋ አለን በማለት ከቫቲካን ዜና አገልግሎት ጋር የነበራቸውን ቆይታ አጠቃለዋል።

 

06 November 2024, 16:05