ሊቀ ጳጳስ ጋላገር፥ የቅድስት መንበር ስምምነቶች በአፍሪካ ሰብዓዊነትን እንደሚያገለግሉ ገለጹ
“ቅድስት መንበር ከአፍሪካ መንግሥታት ጋር ያደረገችው ዲፕሎማሲ የቤተ ክርስቲያንን ነፃነት በማስጠበቅ እና በፖለቲካ ለውጦች መካከል የጋራ ጥቅምን በማስጠበቅ ላይ ያተኮረ እና ለሰብዓዊ አገልግሎት የቆመ ነው” ሲሉ ገልጸዋል። ሊቀ ጳጳሱ ይህን የተናገሩት በካሜሩን የሚገኘውን የመካከለኛው አፍሪካ ካቶሊክ ዩኒቨርሲቲ ጉብኝት አራተኛው እና የመጨረሻ ቀን ላይ እንደ ነበር ታውቋል።
በዓለም አቀፍ ዲፕሎማሲ ውስጥ የቤተ ክርስቲያን ሚና
በቅድስት መንበር የተፈረሙት ስምምነቶች የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን የረጅም ጊዜ የዲፕሎማሲ ባሕል መሠረታዊ ገጽታ እንደሆኑ ሊቀ ጳጳስ አቡነ ጋላገር ገልጸው፥ ቤተ ክርስቲያን ጥልቅ መንፈሳዊ አካል ሆና ስትቀጥል በዓለም ላይ ካሉ መንግሥታት ሁሉ እና የተባበሩት መንግሥታት ከመሰሉ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ጋር በጋራ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ውስጥ ጉልህ ተዋናይ መሆኗን አስረድተዋል።
ቅድስት መንበር ዕውቅናን በሰጧት 91 አገራት ውስጥ ዲፕሎማሲያዊ ተልዕኮዋን እየተወጣች እንደምትገኝ ታውቋል። በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ማርቲን አምስተኛ (1417-1431) ዘመን የተመሠረተውን ጳጳሳዊ ዲፕሎማሲን የቫቲካን የመንግሥታት ግንኙነት ክፍል ዋና ጸሐፊ ሊቀ ጳጳስ አቡነ ፖል ሪቻርድ ጋላገር እየመሩት እንደሚገኙ ታውቋል።
ከአፍሪካ ሀገራት ጋር ያለው የረጅም ጊዜ የበለጸገ ትብብር
በካሜሩን ያውንዴ ከሚገኘው የመካከለኛው አፍሪካ የካቶሊክ ዩኒቨርሲቲ የተሰጣቸው የክብር ዶክትሬት እንዳስደሰታቸው የገለጹት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ጋላገር፥ በቅድስት መንበር እና በካሜሩን መንግሥት መካከል በያውንዴ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ ጥር 13/2014 የጸደቀው የማዕቀፍ ስምምነት አስፈላጊነት አብራርተዋል።
በማከልም በአፍሪካ እና በቫቲካን መካከል ያለው ግንኙነት ከብዙ መቶ ዓመታት በፊት የተጀመረ መሆኑን ገልጸው፥ ከቱኒዚያ እና የቤልጂየም ቅኝ ግዛት ከነበረች ኮንጎ ጋር ቀደምት ስምምነቶች መፈረማቸውን እና በዚህም መሠረት ከረጅም ጊዜ አንስቶ ከአህጉሪቱ ጋር የበለጸገ ትብብር መጀመሩን አስረድተዋል።
በእነዚህ ግንኙነቶች ውስጥ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው የቅኝ ግዛት ዘመን ግንኙነቶች እንደ ነበሩ የገለጹትሊቀ ጳጳስ አቡነ ጋላገር፥ ከኢትዮጵያ እና ከላይቤሪያ በስተቀር ሁሉም አፍሪካ ማለት ይቻላል በአውሮፓ ኃያላን ቁጥጥር ሥር እንደ ነበሩ አስታውሰው፥ በወቅቱ ቅድስት መንበር ለምእመናን እና ለአካባቢው ካኅናት ድምፅ በመሆን በቅኝ ግዛት የተያዙ ግዛቶችን በሚመለከቱ የአካባቢዎች ስብሰባዎች ላይ ቀስ በቀስ መሳተፍ መጀመሯን አስታውሰዋል።
ከኮንጎ ጋር የተደረጉ ስምምነቶች
የቤልጂየም ቅኝ ግዛት ከነበረች ኮንጎ ጋር ሁለት ስምምነቶች መደረጋቸውን የጠቀሱት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ጋላገር፥ አንደኛው በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፒዮስ 10ኛ ዘመን እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በግንቦት 26/1906 እና ሁለተኛው በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፒዩስ 12ኛ ዘመን እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በታኅሣሥ 8/1953 እንደነበር አስታውሰዋል።
የመጀመሪያው ስምምነት ዓላማ ትምህርት ቤቶችን እና የሙያ ማሰልጠኛ ማዕከላትን በማቋቋም የመንግሥትን የትምህርት ማስፋፊያ ጥረቶችን በመደገፍ የካቶሊክ እምነትን ማስፋፋት እንደ ነበር፥ ሁለተኛው ስምምነት በኮንጎ የሚገኙ ካቶሊካዊ ድርጅቶችን ከአዳዲስ ሁኔታዎች ጋር ለማላመድ፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ በመጣው የካቶሊክ ምዕመናን ቁጥር እና በአገሪቱ ካቶሊክ ካኅናት የሚታወቅ እና ለነጻነት የሚጥር ዘመናዊ መንግሥት ከመፍጠር ጎን ለጎን መሆኑን አስረድተዋል።
በአህጉሪቱ የነበሩ የመጀመሪያ ተልዕኮዎች
በቅኝ ግዛት ዘመን ማብቂያ ላይ ቅድስት መንበር በአፍሪካ ያላት ዲፕሎማሲያዊ እንቅስቃሴ መፋጠኑን የገለጹት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ጋላገር እንደ ጎርጎሮሳውያኑ ከ1960 ዓ. ም. ጀምሮ እንደ ሌጎስ (ናይጄሪያ)፣ ናይሮቢ (ኬንያ) እና አንታናናሪቮ (ማዳጋስካር) በመሳሰሉ ከተሞች አዳዲስ ሐዋርያዊ ልዑካን ሲላኩ ሌሎች ልዑካን ወደ ሐዋርያዊ እንደራሴነት ማደጋቸውን አስረድተዋል።
በፈረንሳይኛ ተናጋሪ የአፍሪካ አገራት የመጀመሪያው የቅድስት መንበር ሐዋርያዊ እንደራሴ ጽሕፈት ቤት በዳካር (ሴኔጋል) እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ1961 የተከፈተ ሲሆን ይህም በአህጉሪቱ ውስጥ በካይሮ (ግብፅ)፣ በአዲስ አበባ (ኢትዮጵያ) እና በሞንሮቪያ (ላይቤሪያ) ቀጥሎ አራተኛው እንደሆነ ታውቋል።
በአሁኑ ወቅት መካከለኛው አፍሪካ በሚባሉት በሁሉም አካባቢዎች ላይ ስልጣን ያለው እና በካሜሩን ያውንዴ የሚገኘው የሐዋርያዊ ተልዕኮ ጽሕፈት ቤት እንደ ጎርጎጎሮሳውያኑ በሚያዝያ 3/1965 የተመሠረተ ሲሆን፥ ሆኖም ቅድስት መንበር ከአፍሪካዊቷ አገር ጋቦን ጋር የመጀመሪያውን የማዕቀፍ ስምምነት ያፀደቀችው እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ1997 እንደ ነበር ይታወሳል።
የሃይማኖት ነፃነት እና የጋራ ጥቅም
ዛሬ ከ54 የአፍሪካ አገራት 51 ዱ ከቅድስት መንበር ጋር የተረጋጋ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እንዳላቸው ሲታወቅ፥ እነዚህ ግንኙነቶች የሃይማኖት ነፃነትን ያለ ልዩነት ለማስከበር እና የጋራ ጥቅምን ለማስጠበቅ በማቀድ በሁለተኛው የቫቲካን ጉባኤ መርሆዎች እንደሚመሩ ታውቋል። "ደስታ እና ተስፋ” (Gaudium et Spes) የተሰኘው ሐዋርያዊ ድንጋጌ ይህን ድንጋጌ “ቡድኖች እና ግለሰቦች ፍላጎታቸውን በተሟላ ሁኔታ እና በቀላሉ እንዲያገኙ የሚያስችል የማኅበራዊ ሁኔታዎች ስብስብ” ሲል ይገልጸዋል።
ሊቀ ጳጳስ አቡነ ጋላገር፥ ቅድስት መንበር ከመንግሥታት ጋር ስምምነቶችን በምትፈርምበት ጊዜ ቤተ ክርስቲያኒቱ እንደ ቀድሞው ጊዜ ልዩ መብቶችን ሳትፈልግ ነገር ግን ለካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን እና ለሕዝቦቿ የሃይማኖት ነፃነት ጥቅም ብቻ እንደምትናገር አጽንኦት ሰጥተዋል።
ከካሜሩን ጋር የተደረጉ ስምምነቶች
ሊቀ ጳጳሱ አቡነ ጋላገር፥ ከያውንዴው ካቶሊካዊ ተቋም ጋር የተደረገውን ስምምነት ጨምሮ ከካሜሩን መንግሥት ጋር የተፈራረሙትን ስምምነቶች በማስመልከት ሲናገር፥ የመጀመሪያው ስምምነት እንደ ጎርጎሮሳውያኑ ሐምሌ 5/1989 በካሜሩን ጳጳሳዊ ዩኒቨርሲቲ እንዲቋቋም ማስቻሉን፥ እና ይህም በወቅቱ አንድ የመንግሥት ዩኒቨርሲቲ ብቻ በነበረበት እና የግል ዩኒቨርሲቲዎች በሌሉት ሀገር ውስጥ ለከፍተኛ ትምህርት አስተዋፅዖ ማድረጉን አስረድተዋል።
እንደ ጎርጎሮሳውያኑ ነሐሴ 17/1995 የተደረገው ሁለተኛው ስምምነት፥ ተቋሙ በካሜሩን የሲቪል ተቋማት እውቅና ያላቸውን ዲግሪዎች እንዲሰጥ ማስቻሉን ገልጸው፥ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ2014 የጸደቀው የማዕቀፍ ስምምነት በሁለቱ ደረጃዎች የተደረጉትን የአጭር እና የረጅም ጊዜ ስምምነቶች አስፈላጊነትን የሚያጠናክር መሆኑን አብራርተዋል።
በካሜሩን ለቤተ ክርስቲያን እንቅስቃሴዎች አስፈላጊ የሆነው የአጭር ጊዜ ማዕቀፍ፥ ተዋዋይ ወገኖች ለሃይማኖት ነፃነት ያላቸውን ቁርጠኝነት እንደሚያረጋግጥ ገልጸው፥ ከረዥም ጊዜ ማዕቀፍ አንጻር ሲታይ ከካሜሩን መንግሥት ጋር ያለው ግንኙነት እና ትብብር ለቤተ ክኅነት ግልጽ መርሆዎችን እና የሕግ ድንጋጌዎችን እንደሚያቀርብ አስረድተዋል።
በስምምነቱ ውስጥ ከተገለጹ አስፈላጊ ርዕሦች መካከል፥ ለተለያዩ የሕግ አካላት እውቅናን መስጠት፣ የአሠራር ሂደታቸውን ቀላል ማድረግ፣ ቤተ ክርስቲያን ማሻሻያዎችን እና ለውጦችን በማድረግ ራሷን እንድትችል እና የጳጳሳት ሹመቶችን ማካሄድ፣ ከቦታ ቦታ ማዛወር እና የሥራ መልቀቂያዎችን መስጠት የሚሉት እንደሚገኙባቸው አስረድተዋል። በተጨማሪም ስምምነቱ ቤተ ክርስቲያን በካሜሩን ሕግ መሠረት ሕጋዊ ሰውነት ያላቸውን ተቋማት በመፍጠር የጋራ ልማትን እና ጥቅምን እንድታገለግል የሚያስችላት መሆኑን ሊቀ ጳጳሳ አቡነ ጋላገር አስረድተዋል።
የአካባቢው ማኅበረሰቦች የሚያገኟቸው ጥቅሞች
ሊቀ ጳጳስ ጋልገር ንግግራቸውን ሲያጠቃልሉ፥ የቅድስት መንበር ዲፕሎማሲ ከሁሉም ዓይነት አቅመ ደካማነት ጋር ቤተ ክርስቲያንን እና ሰብዓዊነትን በማገልገል ላይ እንደሚገኝ ገልጸው፥ ሊፈጠሩ ከሚችሉ ፖለቲካዊ ለውጦች ጋር የቤተ ክርስቲያን ነፃነቶችን ለመጠበቅ እና ለአካባቢው ማኅበረሰቦች ሰብዓዊ ክብር ያለውን ሐዋርያዊ ቃል ኪዳን እውን ለማድረግ እንደ ወሳኝ ግብዓት ሆኖ እንደሚያገልግል አስረድተው፥እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በመስከረመ 18/2023 በተካሄደው 78ኛው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ሁሉም መንግሥታት የአገልጋይነት መንፈስን እንደገና ማግኘት እንዳለባቸው አሳስበዋል።
ይህን ማሳሰቢያቸውን ያስታወሱት ሊቀ ጳጳሱ አቡነ ጋላገር፥ ከካሜሩን ጋር የተደረገውን የማዕቀፍ ስምምነት 10ኛ ዓመት ለማክበር ዝግጅት እየተደረገ ባለበት በዚህ ጊዜ፣ ስምምነቱ ለካሜሩንና በተለይም ተጋላጭ ለሆኑ ክርስቲያኖች እና ዜጎች ደኅንነት የበለጠ ፍሬ እንደሚያፈራ ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል።