ፈልግ

በተባበሩት መንግሥታት የቫቲካን ቋሚ ታዛቢ ሊቀ ጳጳስ አቡነ ገብርኤል ካቻ በተባበሩት መንግሥታት የቫቲካን ቋሚ ታዛቢ ሊቀ ጳጳስ አቡነ ገብርኤል ካቻ  

ቅድስት መንበር የአውታረ መረብ ላይ ዘረኝነት እየጨመረ መሄዱ እንዳሳሰባት ገለጸች

በተባበሩት መንግሥታት የቫቲካን ቋሚ ታዛቢ ሊቀ ጳጳስ አቡነ ገብርኤል ካቻ ጥቅምት 28/2017 ዓ. ም. በኒውዮርክ ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ተገኝተው ባሰሙት ንግግር፥ በአውታረ መረብ በኩል እየተስፋፋ የመጣው ዘረኝነት ቅድስት መንበርን እንዳሳሰባት ተናግረዋል። ሊቀ ጳጳሱ በንግግራቸው የአውታረ መረብ ላይ ዘረኝነትን፣ በስደተኞች ላይ የሚደረግ መድልዎን እና የሃይማኖቶች አለመቻቻልን መዋጋት እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

የቫቲካን ቋሚ ታዛቢ ሊቀ ጳጳስ አቡነ ገብርኤል ካቻ ሐሙስ ኅዳር 28/2017 ዓ. ም. በኒውዮርክ በተካሄደው 79ኛው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ባደረጉት ንግግር፥ በስደተኞች ላይ በሚደረግ መድልዎ፣ በሃይማኖቶች አለመቻቻል እና በአውታረ መረብ በኩል በሚካሄድ ዘውረኝነት ላይ ቤተ ክርስቲያኗ ስጋት እንዳላት ተናግረዋል።

“ዘረኝነት በስውር መልክ እየያዘ መጥቷል!”
ሊቀ ጳጳስ አቡነ ገብርኤል ካቻ “የሰው ልጆች በሙሉ በነፃነት የተወለዱ እኩል ሰብዓዊ ክብር እና መብት ያላቸው ናቸው” የሚለውን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ድንጋጌን በመጥቀስ በጀመሩት ንግግራቸው፥ የዚህ ድንጋጌ መሠረታዊ እውነት በትክክል ቢታወቅም ነገር ግን ታሪክ እንደሚያሳየን በየጊዜው ችግር እየጠመው ይገኛል” ብለዋል።

ግልጽ የዘረኝነት አዝማሚያ መኖሩን መለየት ቀላል እንደሆነ የተናገሩት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ገብርኤል ካቻ፥ይህ አዝማሚያ በእርግጥ የተወገዘ ቢሆንም ብዙውን ጊዜ ጭፍን የዘር ጥላቻ ስውር መልክ አለው” ሲሉ አስረድተዋል።

በስደተኞች ላይ የሚደረግ አድልዎ እና የሃይማኖቶች አለመቻቻል
ይህን በተመለከተ ቅድስት መንበርን የሚያሳስቧት ሦስት ጉዳዮች እንዳሉ የገለጹት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ገብርኤል ካቻ፥ የጀመሪያው በስደተኞች እና በጥገኝነት ጠያቂዎች ላይ የሚደረግ አድልዎ እንደሆነ ተናግረው፥ “ስደት የፍርሃት እና የጭንቀት ስሜት ሊፈጥር የሚችል እና ብዙውን ጊዜ እየተባባሰ ሄዶ ለፖለቲካ ዓላማ የሚውል ነው” ሲሉ አስረድተዋል። ሆኖም “ስደተኞች እንደማንኛውም ሰው ተመሳሳይ ውስጣዊ ክብር ያላቸው እንደሆኑ መታየት አለባቸው” ሲሉ አፅንዖት ሰጥተዋል።

በሁለተኛ ደረጃ በሃይማኖቶች አለመቻቻል ምክንያት የሚፈጠር ችግር መኖሩን ያስታወሱት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ገብርኤል ካቻ፥ ግለሰቦች እና ማኅበረሰቦች እምነታቸውን በመግለጻቸው ብቻ እገዳ እና ስደት እንደሚደርስባቸው ገልጸው፥ “እነዚህ እገዳዎች የሃይማኖት ወይም የእምነት ነፃነት መሠረታዊ መርሆችን ይጎዳሉ” ብለዋል።

የአውታረ መረብ ላይ ዘረኝነት
ሊቀ ጳጳስ አቡነ ገብርኤል ካቻ በመጨረሻም፥ በአውታረ መረብ በኩል እየተስፋፋ የመጣው ዘረኝነት እናየውጭ መጤ ጥላቻ ቅድስት መንበርን እንዳሰጋት ገልጸው፥ ይህን መቅሰፍት በመዋጋት ረገድ ለሁለቱም እንደ ስልታዊ ምላሽ እና የረጅም ጊዜ መከላከያ እርምጃ ትምህርት ከሁሉም በላይ አስፈላጊ እንደሆነ አስረድተዋል።

በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የቅድስት መንበር ተወካይ የሆኑት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ገብርኤል ካቻ በኒውዮርክ በተካሄደው 79ኛው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ያደረጉትን ንግግር ሲያጠቃልሉ፥ “ለእያንዳንዱ ሰው የሚሰጥ እኩል ክብር ዘረኝነትን እና መገለልን ዐይናችን ቸል እንዳይል የሚጠይቅ ነው” ብለው፥ ይልቁንም ለስደተኞች እና ጥገኝነት ጠያቂዎች እምቅ ዕውቀት እውቅናን መስጠት እንደሚገባ ጥሪ አቅርበው፥ የእያንዳንዱን ሰው ስጦታ እና ልዩነት መቀበል እንደሚገባ በማሳሰብ ንግግራቸውን ደምድመዋል።

 

09 November 2024, 15:46