ቅድስት መንበር፥ ግዴለሽነት ፍትሕን ከማጓደል ተግባራት አንዱ መሆኑን ገለጸች
የዚህ ዝግጅት አራቢ ዮሐንስ መኮንን-ቫቲካን
የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ ካርዲናል ፒዬትሮ ፓሮሊን በአዘርባጃን ባኩ ከተማ ከኅዳር 2-13/2017 ዓ. ም. በመካሄድ ላይ በሚገኘው 29ኛ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ ባደረጉት ንግግር፥ “በእኛ ዘንድ ያለው ሳይንሳዊ መረጃ ተጨማሪ መዘግየትን የማይፈቅድ እና ፍጥረትን ከጉዳት መጠበቅ በጊዜያችን ካሉት አንገብጋቢ ጉዳዮች አንዱ እንደሆነ ግልጽ ያደርጋል” ካሉ በኋላ፥ “ይህም ሰላምን ከማስጠበቅ ጋር በቅርበት የተቆራኘ መሆኑን መገንዘብ ይገባል ብለዋል።
የግለሰብ እና የቡድን ራስ ወዳድነት
በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት 29ኛው የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ ላይ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስን በመወከል የተገኙት ካርዲናል ፒዬትሮ ፓሮሊን በንግግራቸው፥ ጉባኤው የብዙ ወገን ተቋማት ብስጭቶችን እና እንቅፋት የመሆን አደገኛ ዝንባሌዎችን በቁም ነገር ወስዶ ምላሽ እንደሚሰጥ ያላቸውን እምነት ገልጸው፥ ካልሆነ ግን የግለሰቦችም ሆነ የባለ ስልጣናት ራስ ወዳድነት አለመተማመንን እና መከፋፈልን እያስፋፋ እንደሆነ ገልጸዋል።
ካርዲናል ፓሮሊን እርስ በርስ የሚያቀራርበን “ግሎባላይዜሽን” በመካከላችን ወንድማማችነትን እና እህትማማችነትን ሊያሳድግ እንዳልቻለ ገልጸው፥ “የኢኮኖሚ ልማትም ቢሆን የሃብት አለመመጣጠንን እንዳልቀነሰ አስረድተው፥ “በተቃራኒው ለደካሞች ጥበቃን ከማድረግ ይልቅ ለትርፍ እና ለልዩ ጥቅም ቅድሚያን በመስጠት የአካባቢ ችግሮች ከጊዜ ወደ ጊዜ እንዲባባሱ አስተዋጽኦ አድርጓል” ሲሉ ተናግረዋል። “ይህን አካሄድ መቀልበስ ያስፈልጋል!” ያሉት ካርዲናል ፓሮሊን፥ ሕይወትን እና የሰው ልጅ ክብር የመጠበቅ ባሕልን ለመፍጠር የአኗኗር ዘይቤዎች የሚያስከትሏቸው ጎጂ ውጤቶች ሁሉንም ሰው እንደሚጎዱ ማወቅ ያስፈልጋል” ብለዋል።
የሥነ-ምሕዳር ቀውስ እና የውጭ ዕዳ ጫና የሚያስከትሏቸው አደጋዎች
ካርዲናል ፓሮሊን አያይዘውም፥ በኢኮኖሚ ዕዳ ጫና ውስጥ የሚገኙ የበርካታ አገሮች ልማት እና የመላመድ አቅምን የሚያጠናክሩ መፍትሄዎችን ለማግኘት ጥረት መደረግ እንዳለበት አሳስበዋል። "በአየር ንብረት ፋይናንስ ላይ በሚወያዩበት ጊዜ የሥነ-ምሕዳር ቀውስ እና የውጭ ዕዳ ጫና የአንድ ሳንቲም ሁለት ገፅታዎች መሆናቸውን ማስታወስ ያስፈልጋል” ሲሉ አሳስበዋል።
ከዚህ አንጻር ካርዲናል ፓሮሊን የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስን ጥሪ በመድገም፥ የበለጸጉ አገራት “ዕዳቸውን መክፈል የማይችሉ አገራትን ይቅር እንዲሉ” ጠይቀው፥ “ይህም ከልግስና ጥያቄ በላይ የፍትህ ጉዳይ ነው” በማለት ያስተላለፉትን የቅዱስነታቸውን መልዕክት አስታውሰዋል።
ካርዲናል ፓሮሊን በመቀጠልም፥ ፍትሃዊ እና ዘላቂ ልማትን የሚደግፍ አዲስ ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ሥርዓት እንዲፈጠር ተማጽነው፥ በተለይም ተጋላጭ ወደሆኑ አገራት እና የፖለቲካ ፍላጎት ወደ ሁሉን አቀፍ ዕድገት እንዲያመራ ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት 29ኛ የአየር ንብረት ቀውስ ጉባኤ ጥሪ አቅርበዋል።
ፊታችንን ወደ ሌላ አቅጣጫ ማዞር አንችልም
ካርዲናል ፓሮሊን በዚህ ጥረታቸው የቅድስት መንበርን ቁርጠኝነት በድጋሚ በመግለጽ፥ በተለይም በሁሉ አቀፍ ሥነ-ምህዳር፣ በትምህርት እና በአካባቢ ጥበቃ እንደ ሰው በማንኛውም ደረጃ ግንዛቤን በማሳደግ ረገድ ፊታችንን ወደ ሌላ አቅጣጫ ማዞር የማይቻል መሆኑን በመግለጽ “ግዴለሽነት ከፍትሕ ማጓደል ተግባራት መካከል አንዱ ነው” ሲሉ አስገንዝበዋል።
የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ ካርዲናል ፒዬትሮ ፓሮሊን ንግግራቸውን ሲያጠቃልሉ፥ በጉባኤው የተገኙት፥ “ምን ማድረግ እችላለሁ? እንዴት ማበርከት እችላለሁ?” በማለት ራሳቸውን እንዲጠይቁ ተማጽነው፥ ግዴለሽነት ጊዜ የሚሰጠው እንዳልሆነ በማስረዳት “እጅን ታጥቦ በርቀት መቆም አንችልም፤ ይህ የዘመናችን እውነተኛ ፈተና ነው” ስሉ ስገንዝበዋል።