ካርዲናል ፓሮሊን ወደ ዩክሬን ተጉዘው ሊቪቭን፣ ኦዴሳን እና ኪየቭን በጎበኙበት ወቅት ካርዲናል ፓሮሊን ወደ ዩክሬን ተጉዘው ሊቪቭን፣ ኦዴሳን እና ኪየቭን በጎበኙበት ወቅት  

ካርዲናል ፓሮሊን፥ ለማስቆም የማይቻል በሚመስል ጦርነት መሸነፍ የለብንም ማለታቸው ተገለጸ

የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ ካርዲናል ፒዬትሮ ፓሮሊን ከጀመረ 1000 ቀናት ያስቆጠረውን የዩክሬን ሙሉ ወረራ በማስመልከት ከቅድስት መንበር መገናኛዎች ርዕሠ አንቀጽ ዝግጅት ክፍል ሃላፊ አንድሬያ ቶርኔሊ ጋር ቃለ ምልልስ አድርገዋል። ካርዲናል ፓሮሊን በቃለ ምልልሳቸው፥ በዩክሬን ሕዝብ ላይ እየደረሰ ያለውን መከራ በማውገዝ እልቂቱን ለማስቆም የተጠናከረ ዲፕሎማሲያዊ ጥረት እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

“ለጦርነት አይቀሬነት ራሳችንን ማስገዛት አንችልም!” ያሉት የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ ካርዲናል ፒዬትሮ ፓሮሊን ከቫቲካን ሚዲያ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ፥ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በየዓመቱ የሚውለው ኅዳር 19 አሳዛኝ ቀን “በሁሉም ሰው ዘንድ በተለይም እየቀጠለ ያለውን እልቂት ሊያስቆሙ በሚችሉት ሰዎች ሁሉ ላይ የኃላፊነት ስሜት ሊያነቃቃ ይችላል” ብለዋል። ካርዲናል ፓሮሊን ባለፈው ዓመት ሐምሌ ወር ዩክሬን ተጉዘው ሊቪቭ፣ ኦዴሳ እና ኪየቭ ጎብኝተው መመለሳቸው ይታወሳል።

“በየዕለቱ ወደ እኛ የሚደርሰውን የበለጠ ሞት እና የጥፋት ዜናን መልመድ ወይም ደንታ ቢስ መሆን ስለማንችል በከባድ ሐዘን ውስጥ እንገኛለን” ያሉት ካርዲናል ፓሮሊን፥ ዩክሬን ጥቃት ተፈጽሞባት በስቃይ ውስጥ የለች አገር፣ ትውልዶች ወጣቶች እና ሽማግሌዎች፣ ከትምህርታቸው፣ ከሥራ ገበታቸው እና ከቤተሰቦቻቸው ተነጥቀው ወደ ጦር ግንባር በመላክ መስዋዕትነትን እየከፈለ ያለ ሕዝብ እንደሆነ ገልጸው፥ ዘመዶቻቸው በቦምብ ወይም በሰው አልባ አውሮፕላኖች ጥቃት ሲሞቱ የሚያዩ እና በጦርነቱ ምክንያት ቤታቸውን ያጡ ወይም በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ለመኖር የተገደዱ ሰዎች የሚደርስባቸውን መከራ አስታውሰዋል።

ካርዲናል ፓሮሊን “ዩክሬንን ለመርዳት ምን እናድርግ?” ተብለው ለተጠየቁት ጥያቄ ሲመልሱ፥ “በመጀመሪያ ደረጃ፥ እንደ ክርስቲያን መጸለይ እንደሚቻል፥ እግዚአብሔር የጦር አዛዦችን ልብ እንዲለውጥ መለመን እንደሚገባ በማሳሰብ በተለይ ከብዙ ዘመናት በፊት ጥምቀትን በተቀበሉ አገሮች ውስጥ የምትከበረውን የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን አማላጅነት መለመን አለብን” ብለዋል።

በሁለተኛ ደረጃ፥ ለሚሰቃዩት፣ እንክብካቤ ለሚያስፈልጋቸው ሰዎች አብሮነታችን በተጨባጭ መግለጽ እንደሚገባ ተናግረው፥ በብርድ ለሚሰውቃዩት እና ምንም ነገር ለሌላቸው ሰዎች ራስን አሳልፎ መስጠት እንደሚቻል በማስታወስ በዩክሬን ያለች ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ለሕዝቡ ብዙ እየሠራች እንደሚትገኝ እና በጦርነት ውስጥ የሚገኝ ሕዝብ ችግር በመካፈል ላይ እንደምትገኝ አስረድተዋል።

በሦስተኛ ደረጃ፥ እንደ ማኅበረሰብ፣ እንደ ሕዝብ ሰላምን በመጠየቅ ድምጻችንን ማሰማት እንችላለን፤የሰላም ተነሳሽነት እንዲሰማ እና እንዲታሰብበት መወትወት እንችላለን” ብለዋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ አሁንም እያወገዙት ያለውን ጦርነት እና የጦር መሣሪያ ውድድርን ውድቅ ማድረግን መግለጽ እንደሚቻል ተናግረው፥ “እየተከሰቱ ባሉ ሁኔታዎች ውስጥ የዕርዳታ እጦት ስሜት መረዳት የሚቻል ቢሆንም እንደ አንድ ሰብዓዊ ቤተሰብ አንድ ላይ ሆነን ብዙ መሥራት እንችላለን” ብለዋል።

ካርዲናል ፓሮሊን “ቢያንስ ዛሬ የጦር መሣሪያ ድምጽን ለማስቆም ምን ማድረግ ያስፈልጋል?” ተብለው ለተጠየቁት ጥያቄ ሲመልሱ፥ “የጦር መሣሪያ ድምጽ ይቁም!” ማለት ተገቢ እንደሆነ ገልጸው፥ ምክንያቱም ፍትሃዊ በሆነ ሰላም ላይ መደራደር ጊዜ የሚወስድ ሲሆን፥ ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት ሁሉ የሚጋሩት እርቅ፥ በዋናነት ግጭቱን የቀሰቀሰችው እና ጥቃቱን ማቆም ያለባት ሩሲያ ፍላጎቱ ካላት በጥቂት ሰዓታት ውስጥ የጦር መሣሪያ ድምጽን ማቆም እንደምትችል አስረድተዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ብዙውን ጊዜ እንደሚናገሩት፥ በጦርነት ላይ ሳይሆን በሰላም ላይ ለመወራረድ ፈቃደኛ የሆኑ ግለሰቦች ለዩክሬን ብቻ ሳይሆን ለመላው አውሮፓ እና ለዓለም አስከፊ ውጤት የሚያስከተለውን ግጭት በማስቆም የተሰጣቸውን ከፍተኛ ኃላፊነት የሚገነዘቡ ግለሰቦች እንደሚያስፈልጉ ተናግረዋል።

“ይህ ጦርነት ወደ ኑክሌር ግጭት እና ወደ ጥልቁ እንድንወርድ ሊጎተትን ይችላል” ያሉት ካርዲናል ፓሮሊን፥ ቅድስት መንበር የምትችለውን ሁሉ ለማድረግ እየጣረች መሆኗን ገልጸው፥ “ለሁሉም ወገን ክፍት የሆነ የውይይት መድረክ ቢኖርም ነገር ግን ታሪክ ወደ ኋላ የተመለሰ ይመስላል” ብለዋል። “ዲፕሎማሲያዊ ጥረቶች፣ ትዕግስት የታከለባቸው ውይይቶች እና ድርድሮች ጊዜ ያለፈባቸው ቅርሶች ሆነው የጠፉ ይመስላሉ” ያሉት ካርዲናል ፓሮሊን፥ በጦርነቱ የሚጎዱት እና ከፍተኛ ዋጋን የሚከፍሉት ንጹሃን ዜጎች ናቸው” ብለው፥ ጦርነት የልጆችን እና የወጣቶችን የወደፊት ዕጣ ፈንታ እንደሚሰርቅ፣ መለያየትን በመፍጠር ጥላቻን እንደሚያባብስ አስረድተዋል።

አርቆ አስተዋይ፣ ራዕይ ያላቸው፣ በትህትና ደፋር ተግባራትን መፈጸም የሚችሉ፣ ስለ ሕዝባቸው ጥቅም የሚያስቡ የሀገር መሪዎችን እጅግ እንፈልጋለን” ያሉት ካርዲናል ፓሮሊን፥ ከአርባ ዓመታት በፊት በሮም፣ በአርጀንቲና እና በቺሊ መካከል በተፈረመ የሰላም ስምምነት መሠረት የቢግል ቻናል ውዝግብን ለመፍታት ቅድስት መንበር የተጫወተችውን ሚና በማስታወስ፥ ስምምነቱ ከመደረጉ ከጥቂት ዓመታት በፊት ሁለቱ ሀገራት ጦር ሠራዊታዊቶቻቸን በማሰባሰብ በጦርነት አፋፍ ላይ የነበሩ ቢሆንም ውጥረት ሙሉ በሙሉ ቆሞ እግዚአብሔር ይመስገን ስፍር ቁጥር የሌለው የሰው ሕይወት ከሞት መትረፍ ችሏል” ብለው፥ ይህ መንፈስ ዛሬ በአውሮፓ እምብርት ውስጥ እንደገና ሊገለጥ ያልቻለው ለምንድነው?” ሲሉ ጠይቀዋል።

“ዛሬ ለድርድር ቦታ እንዳለ ያምናሉ?” ተብለው የተጠየቁት ካርዲናል ፓሮሊን፥ ምልክቶቹ አወንታዊ ባይሆኑም፣ ድርድር ሁል ጊዜ የሚቻል እና ለሰው ልጅ ሕይወት ቅድስና ዋጋ ሊሰጠው ይገባል” ብለው፥ መደራደር የድክመት ሳይሆን የድፍረት ምልክት እንደሆነ አስረድተዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በቅርቡ ወደ ሉክሰምበርግ እና ቤልጂየም ባደረጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት ወቅት የተናገሩትን በመጥቀስ፥ “ሐቀኛ ድርድር እና ክብር የሚሰጠው ስምምነት የሕዝቦችን ዕጣ ፈንታ በእጃቸው የያዙት ሰዎች ሊከተሉት የሚገባ ዋና መንገድ ነው” ማለታቸውን አስታውሰዋል። መወያየት የሚቻለው በተዋዋይ ወገኖች መካከል ቢያንስ መተማመን ሲኖር እንደሆነ ተናግረው፥ ይህም ከሁሉም ሰው በኩል ጥሩ እምነትን እንደሚጠይቅ፣ በትንሹም ቢሆን መተማመን ከሌለ እና ድርጊቶች ቅንነት የጎደላቸው ከሆነ ሁሉም ነገር በቆመበት እንደሚቀር አስረድተዋል።

በዩክሬን፣ በቅድስት ሀገር እና በብዙ የዓለማችን ክፍሎች ፍልሚያ እና ሞት ቀጥሏል” ያሉት ካርዲናል ፓሮሊን፥ ለጦርነት አይቀሬነት ራስን ማስገዛት እንደማይቻል ተናግረው፥ በዩክሬን ላይ ወታደራዊ ጥቃት የተፈጸመበት ይህ አሳዛኝ ሺህኛው ቀን በሁሉም ሰው ላይ በተለይም እልቂቱን ማስቆም በሚችሉት ሁሉ ላይ የኃላፊነት ስሜትን እንደሚቀሰቅስ ተስፋ እንደሚያደርጉ ገልጸዋል።

 

19 November 2024, 16:36