የቫቲካን መገናኛዎች ሃላፊ ዶ/ር ፓውሎ ሩፊኒ፥ “ዓለምን ለማስተማር ጊዜው አሁን ነው” ሲሉ ተናገሩ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
የቫቲካን መገናኛዎች ጽሕፈት ቤት ሃላፊ ዶ/ር ፓውሎ ሩፊኒ፥ “በዓለማችን የማኅበራዊ መገናኛ አብዮት እየተካሄደ ባለበት ወቅት የካቶሊክ መገናኛ ባለሞያዎች በማኅበረሰብ እና በጋራ መድረኮች ውስጥ ትብብርን ለመፍጠር ለሚደረገው ጥረት ምላሽ ለመስጠት ዝግጁ ናቸው ወይ?” ሲሉ ጠይቀዋል።
ዶ/ር ፓውሎ ሩፊኒ በሕንድ ባንጋሎር ግዛት ከኅዳር 14-15/2017 ዓ. ም. ለተካሄደው የመጀመሪያው ብሔራዊ የካቶሊክ ሚዲያ ጉባኤ ባስተላለፉት መልዕክት፥ “በዘመናችን ውስጥ በመገናኛው ዓለም አብዮት እየተካሄደ ነው” ሲሉ ተናግረዋል።
“ጊዜ የእኛ ነው!”
የእርምጃውን አጣዳፊነት በማንጸባረቅ ባስተላለፉት መልዕክት፥ “ዘመናችን በምንሠራቸው ሥራዎች እና መሥራት በማንችላቸው ሥራዎች ዓለምን የምንቀርጽበት ነው” ሲሉ አስረድተዋል። “በሰው ሠራሽ አስተውሎት ዘመን ዲጂታል የመገናኛ መሣሪያን መጠቀም” በሚል ርዕሥ የተዘጋጀው ጉባኤ የማኅበራዊ ሚዲያ እና ሰው ሠራሽ አስተውሎት በገዳማውያን ሕይወት ላይ የሚያሳድረውን ተፅእኖ ለመዳሰስ እና ሃላፊነታቸውን እና ሥነ-ምግባራዊ አጠቃቀማቸውን በማስተዋወቅ ላይ እንደሆነ ታውቋል።
“ዲጂታል የመገናኛ መሣሪያዎችን መጠቀም ብቻ አይደለም" ያሉት ዶ/ር ፓውሎ ሩፊኒ፥ እውነትን በመናገር እና ከሌሎች ጋር በመጋራት ዓለምን የመቅረጽ ኃላፊነት ያለባቸው ሰዎች ባይኖሩ ኖሮ ‘ማጋራት’ የሚለው ቁልፍ ቃል አይኖርም ነበር” ብለው፥ ልዩ ልዩ ታሪኮችን የሚለዋወጡበት እና ግንኙነቶችን የሚያዳብሩበት ሰው ሠራሽ አስተውሎት እጅግ ጠቃሚም ጎጂም ሊሆን እንደሚችል አስረድተዋል። ሰው ሠራሽ አስተውሎት በግለሰቦች መካከል ያለውን ግንኙነት ሊያጠናክር ወይም ብቸኝነትን በማሳደግ እውነተኛ የሃሳብ ልውውጥ እንዳይኖረን ያደርጋል” ብለዋል።
ሰው ሠራሽ አስተውሎትን የመጠቀም ሃላፊነት
ሰው ሠራሽ አስተውሎት እኩልነትን በማጎልበት ጥቅም ላይ ሊውል እንደሚችል የገለጹት ዶ/ር ፓውሎ ሩፊኒ፥ “በመረጃ የበላይነት ላይ በተመሠረቱ አዳዲስ የብዝበዛ ዓይነቶች ሳይሆን ነገር ግን በ“አልጎሪዝም” ባለቤትነት ከማያልቀው የሕይወት ልምዶች መረጃን ማግኘት እንደሚቻል አስረድተዋል። “ዋናው ጉዳይ ስለ ሰዎች መጨነቅ እንጂ ስለ መሣሪያዎች ማሰብ አይደለም” ያሉት ሃላፊው፥ “በሰዎች መካከል ያለው ግንኙነት የቀመር ስሌት አይደለም” ብለዋል።
“ለዚህ ፈተና ዝግጁዎች ነን ወይ?” ያሉት ዶ/ር ፓውሎ ሩፊኒ፥ “በእያንዳንዱ ሰው ውስጥ ያለውን መልካም ነገር ወደ ውጭ ለማውጣት የመገናኛ ዘዴዎች ያላቸውን ችሎታ ሁላችንም እናውቀዋለን” ብለው፥ በሰዎች መካከል ያለው ግንኙነት የተሻለ ዓለም ለመገንባት መሣሪያ ሊሆን እንደሚችል ካልሆነም አለመግባባቶችን፣ ቂሞችን እና ጠላትነትን ሊፈጥር እንደሚችል ተናግረዋል።
በብዝሃነት መካከል ያለ አንድነት
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ሰዎች ተስፋ እንዳይቆርጡ በማሳሰብ በሁሉም ሰብዓዊ ቤተሰብ መካከል ዘወትር ትብብር እንዲጎለብት በማለት የሰጡትን የማበረታቻ መልዕክት ያስታወሱት ዶ/ር ፓውሎ ሩፊኒ፥ “በወዳጅነት ላይ የተመሠረተ ግንኙነትን በመፍጠር ክፍፍልን በመዋጋት ላይ ቁርጠኝነት እንዲኖር ጥሪ አቅርበዋል።
የቫቲካን መገናኛዎች ጽሕፈት ቤት ሃላፊ ዶ/ር ፓውሎ ሩፊኒ መልዕክታቸውን ሲያጠቃልሉ፥ የዲጂታል መገናኛዎች ከዚህ በፊት ባልነበረ መልኩ እርስ በርስ እንድንገናኝ ያስቻሉን መሆናቸውን ገልጸው፥ አባላቱ ከጉባኤው በኋላ ኅብረተሰብን፣ የጋራ መድረክን እና ትብብርን ለመፍጠር የሚያስችሉ አዋጭ መንገዶችን እንደሚያገኙ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።