ፈልግ

በስልጠና ወቅት በፀረ-አይሮፕላን ሚሳኤል ላይ የሚደረግ ልምምድ በስልጠና ወቅት በፀረ-አይሮፕላን ሚሳኤል ላይ የሚደረግ ልምምድ  ርዕሰ አንቀጽ

“በጦርነት መቀለድ እና በሰው ሞት መነገድ”

የቫቲካን መገናኛዎች ርዕሠ አንቀጽ ዝግጅት ክፍል ዳይሬክተር አቶ አንድሬያ ቶርኔሊ ስቶክሆልም የሚገኝ ዓለም አቀፍ የሰላም ምርምር ኢንስቲትዩት በቅርቡ በጦር መሣሪያ ሽያጭ ላይ ያለውን ከፍተኛ ጭማሪ በዝርዝር የሚገልጸውን እና ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ጦርነትን አስመልክተው በሚሰጧቸው የማያቋርጡ ማስጠንቀቂያዎች ላይ አስተያየት ሰጥቷል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

“ስለ ሰላም እያወሩ በጦርነት ስለ መዝለቅ ግብዝነት እጠቁማለሁ” ስለ ሰላም ብዙ በሚነገርባቸው አገሮች ውስጥ ከፍተኛ ገንዘብ የሚወጣው በጦር መሣሪያ ምርት ላይ ነው። ይህ ግብዝነት የወንድማማችነት እና የሰላም ግንባታን ዘወትር ወደ ውድቀት ይመራል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የቢግል ቻናል ውዝግብን ለማስቆም በአርጀንቲና እና በቺሊ መካከል የተደረገውን የሰላም ስምምነት 40ኛ ዓመት ባከበሩበት ዕለት ኅዳር 16/2017 ዓ. ም. ንግግር አድርገዋል።

የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ንግግር በቅርቡ በስቶክሆልም ዓለም አቀፍ የሰላም ምርምር ተቋም በተለቀቀው መረጃ ላይ ተጨማሪ ማረጋገጫ አግኝቷል። የጦር መሣሪያ ኢንዱስትሪ በማደግ ላይ ይገኛል። ገቢው ባለፈው ዓመት በ 4.2% በመጨመር ወደ $ 632 ቢሊዮን የደረሰ ሲሆን ይህም እንደ ጎርጎሮሳውያን ከ 2015ቱ በ19% ጨምሯል።

በሚያሳዝን ሁኔታ ከዚህ ጭማሪ ጋር የተቆራኙት ሌሎች አሃዛዊ መረጃዎች የሚታወቁ ናቸው። እነርሱም በጦር ሠራዊት እና በሲቪሉ ላይ የሚደርስ የሞት እና የአካል ጉዳት፣ የወደሙ ከተሞች፣ የተፈናቀሉ ሰዎች፣ የወደፊት እጣ ፈንታ የተሰረቀበት ወጣቶች ትውልድ  እና የአካባቢ ውድመቶች ናቸው።

የሮም ጳጳስ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ “በጦርነት መጫወት” የሚለውን አስደናቂ ማጣቀሻ ተጠቅመዋል። ጦርነትን በአእምሮ ውስጥ እንደ “ጨዋታ” ዓይነት አድርገው ሲመለከቱት፣ በፖለቲካም ይሁን በወታደራዊ ዘርፍ የግጭቶችን መንስኤ ለመፍታት የነበረው ፍላጎት መጥፋቱን  የሚያሳይ ምልክት ነው።

እንዲህ ያለው አመለካከት የጦርነትን መንስኤ ለመረዳት እና ለመፍትሔ አቅጣጫ ለማበጀት ፈቃደኛ አለመሆንን ያመላክታል። የሰላም እሴት፣ የውይይት አስፈላጊነት እና አለመግባባቶችን ለመፍታት የሚያግዝ የድርድር ሚና የተረሳ መሆኑን ያሳያል።

ከዚህም በላይ ጨዋታዎች በአብዛኛው ውድድርን ያካትታሉ። በቴኒስ ግጥሚያ ወይም በቼዝ ጨዋታ አሸናፊን እና ተሸናፊን መለየት ፍጹም ተቀባይነት ያለው ነው። ነገር ግን "በጦርነት መጫወት" አገርን በማካተት የሰው ልጅ ወንድማማችነትን እና የዓለም አቀፍ ሕግ ጽንሰ-ሃሳብን ይቃረናል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከጦርነት ትርፍ ለማግኘት የመሻት ግብዝነትን በማጋለጥ ለፖለቲካ መሪዎች እና ለሌሎች ሰዎች ሕሊና አስቸኳይ ጥሪ አቅርበዋል።

ቅዱስነታቸው አቅመ ደካማ በሆኑ ሰዎች ስም የሚደረግ ንግድ እና በዚህም ምክንያት የሰውን ልጅ በሙሉ የሚጎዳ እንዲሁም በሰላም ስም የሚደረግ ንግድ ሁሉ ሊቆም እንደሚገባ ጠይቀዋል።  ጥያቄያቸው በተለይም በዚህ የአውሮፓውያኑ የስብከተ ገና ሰሞን መግቢያ ወቅት የመላዋ ቤተ ክርስቲያንን ብርቱ ጸሎት የሚጠይቅ ጥልቅ መንፈሳዊ ጥሪ ነው።

የቅዱስነታቸው መንፈሳዊ ጥሪ መጪውን ጊዜ እና አዲሱን ትውልድ ያገናዘበ የወደፊት ራዕይን በመያዝ ዓለም አቀፍ የፖለቲካ ሕይወትን በቁም ነገር ለመምራት የሚያስችሉ ሃሳቦችን፣ ቃላትን እና ተግባራትን ለማነሳሳት የሰላም አለቃ ወደ ሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ ዘንድ የቀረበ ጥሪ ነው።

ከአራት አሥርት ዓመታት በፊት ቫቲካን ባደረገችው የሽምግልና ጥረት በአርጄንቲና እና በቺሊ መካከል የተፈጠረውን ውዝግብ ያስወገደው የሰላም ስምምነት፥ ዓለማችን በአስቸኳይ የሚያስፈልገው እና ለዚህም እውቅና መስጠት  ኃያላኑ ከሚያካሂዱት “የጦርነት ጨዋታዎች” የበላይ መሆን አለበት።

እግዚአብሔር አምላክ የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ውይይቶችን መመሪያው፣ ሕግንም ኃይሉ በማድረግ ችግሮችን በንግግር መፍታት እንዲችል ብርታትን ይስጠው” በማለት የቫቲካን መገናኛዎች ርዕሠ አንቀጽ ዝግጅት ክፍል ዳይሬክተር አቶ አንድሬያ ቶርኔሊ ርዕሠ አንቀጹን ደምድሟል።

04 December 2024, 14:40