ፈልግ

የአውሮፓውያኑ ገና ሰሞን አስተንትኖ የአውሮፓውያኑ ገና ሰሞን አስተንትኖ   (Vatican Media)

አባ ሮቤርቶ ፓሶሊኒ፥ የእግዚአብሔር ታላቅነት የሚታየው በሰዎች ትኅትና መሆኑን ገለጹ

በቅድስት መንበር ለከፍተኛ ጳጳሳዊ ምክር ቤቶች ስብከታቸው የሚያሰሙ ፍራንችስካዊ ካኅን አባ ሮቤርቶ ፓሶሊኒ ሦስተኛውን እና የመጨረሻውን የአውሮፓውያኑ የገና ሰሞን አስተንትኖ ስብከታቸውን አቅርበዋል። አባ ሮቤርቶ በትኅትና ጭብጥ ላይ በማስተንተን ባቀረቡት ስብከት፥ “ትኅትና ገደብን የሚጥል ሳይሆን ነገር ግን ለእርስ በርስ ግንኙነት ሥፍራን የሚያመቻች ነው” ሲሉ አስረድተዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ከመጀመሪያው ቃል የነበረው የእግዚአብሔር ልጅ መወለድ፥ ሕጻን እና ደካማ ሆኖ ወደ ዓለም መምጣትን የመረጠው የትኅትናን ጥንካሬ እና ታላቅነት ለማሳየት መሆኑን አስረድተዋል። አባ ሮቤርቶ ይህን ያስረዱት ታኅሳስ 11/2017 ዓ. ም. በጳውሎስ ስድስተኛ አዳራሽ ለተገኙት የቅድስት መንበር ከፍተኛ የጳጳሳዊ ምክር ቤት አባላት ባቀረቡት ሦስተኛው እና የመጨረሻው የገና ሰሞን ስብከት እንደሆነ ታውቋል። አባ ሮቤርቶ ፓሶሊኒ በሦስት ዙር ላቀረቧቸው ስብከቶች ጭብጥ የሚሆናቸውን ርዕሥ የመረጡት “የተስፋ በሮች” ከሚለው እና ወደ ቅዱስ ዓመት መግቢያ ከሚወስደው የብርሃነ ልደቱ ትንቢት እንደሆነ ታውቋል።

የተደበቀው የእግዚአብሔር ታላቅነት መለኪያ
አባ ፓሶሊኒ ቀደም ሲል በወሩ መጀመሪያ ላይ ያደረጓቸው ሁለት አስተንትኖዎች ማለትም “መገረም” እና “መተማመን” በሚሉት ላይ ያተኮሩ እንደ ነበር ሲታወስ፥ በሦስተኛው እና የመጨረሻ አስተንትኖአቸው የትኅትና ደረጃን ማለፍ እንደሚገባ አሳስበዋል።

ትኅትና ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ለመግባት ቁልፉ እንደሆነ የገለጹት አባ ሮቤርቶ ፓሶሊኒ፥ ትኅትና ራስን መገደብ ሳይሆን ነገር ግን ከዝምታ ጋር አብሮ እንደ እህል ፍሬ በጨለማ ከተዋጠበት ከምድር ውስጥ የሚበቅል መሆኑን አስረድተዋል። ትህትና የተደበቀ የእግዚአብሔር እውነተኛ ታላቅነት መለኪያ እንደሆነ ገልጸው፥ በሌሎች ዘንድ በትህትና እራሱን ዝቅ የደረገው እግዚአብሔር በዕድገታቸው ወቅት አብሮአቸው የሚሄድ መሆኑን አስረድተዋል።

ትኅትና የእግዚአብሔር ሥራዎች መለኪያ፣ ምርጫዎቹ እና ተስፋዎቹ የሚፈጸሙበት ቦታ እንደሆነ ገልጸው፥ የሌላው ሰው መኖር፣ መተንፈስ እና ሃሳቡን በነጻነት የመግለጽ መብት የሚያስገነዝብ ትክክለኛ ግንኙነትን የመፍጠር ፍላጎት እንደሆነ አስረድተዋል። ስለዚህ ትሁት መሆን ማለት ልዩነቶችን ሳይሸፍን ወይም ሳይሽር ሌሎች እራሳቸውን እንዲሆኑ ማስቻል እና እርስ በረስ የሚገኛኙበትን መንገዶች መክፈት ማለት እንደሆነ አስገንዝበዋል።

“መልካም ከማድረግ በፊት ትሁት መሆን ያስፈልጋ”
የእግዚአብሔርን ባህሪ በሚገባ ለመረዳት፥ በማቴ. 25:31–46 ላይ የተጻፈውን የመጨረሻው ቀን ፍርድ ምሳሌ በድጋሚ ማወቅ ያስፈልጋል” ያሉት አባ ፓሶሊኒ፥ “በትውፊት መሠረት ይህ ጥቅስ በጊዜው ፍጻሜ እግዚአብሔር በሰው ልጆች ላይ የሚፈርደው በወንድማማችነት ፍቅር መለኪያ መሆኑን ያስረዳል” ብለዋል።

ይሁን እንጂ የምሳሌው ጥልቅ ትርጉም፥ ወንጌሉ ያልተሰበከላቸውን ጨምሮ ሁሉም ሰው ወደ እግዚአብሔር መንግሥት መግባት የሚችለው በሰዎች ዘንድ ለተናቁት ለእነዚያ ድሆች፣ ችግረኞች፣ አቅመ ደካሞች በሚያደርጉት የቸርነት ሥራ እንደሆነ አባ ፓሶሊኒ ገልጸዋል።

ከዚህ በመነሳት፥ ለሌሎች መልካም ማድረግ ብቻ ሳይሆን ሌሎችም መልካም እንዲያደርጉ መፍቀድ፥ እንዲሁም ሰብዓዊነታቸውን በተሻለ መንገድ እንዲገልጹ ማስቻል የክርስቲያኖች ትልቅ እና ከፍተኛ ኃላፊነት ነው” ሲሉ ተናግረዋል።

ትኅትና ከእግዚአብሔር ጋር መስማማት እና ለእርሱ ታማኝ መሆን እንደሆነ የተናገሩት አባ ፓሶሊኒ፥ “ለሌሎች መልካምን ከማድረጋችን በፊት ራስን ትሁት ማድረግ ጥሩ እና አስፈላጊም ነው” በማለት በድጋሚ አስገንዝበዋል።

ትኅትና እንደ ስብከተ ወንጌል
“እግዚአብሔር ልጆቹ ሌሎችን እንዴት መውደድ እንደሚገባ እንዲያውቁ ብቻ ሳይሆን በሌሎች ዘንድ እንዲወደዱም ይፈልጋል” ያሉት አባ ፓሶሊኒ፥ “ይህ ማለት ሌሎች ጥሩ እና ለጋስ እንዲሆኑ ዕድል መስጠት እና ጥልቅ በሆነ የፍቅር መንገድ ሌሎች ሰብዕናቸው ሙሉ በሙሉ እንዲገልጹ የሚያስችል ነው” ሲሉ አስረድተዋል።

ባልንጀራን መውደድ ማለት ሌሎችን በየዋህነት መቅረብ ማለት ሲሆን፥ ደካማነታችንን ለመቀበል ፈቃደኛ መሆን እና ማወቅ ያለብን አስቸጋሪው ጥበብ ሌሎችን መውደድ ሳይሆን ነገር ግን ራስን በሌሎች ዘንድ ተወዳጅ ማድረግን መለማመድ እንደሆነ ተናግረዋል። “በዚህ መንገድ ትኅትና እውነተኛ የወንጌል ተግባር” ይሆናል ያሉት አባ ፓሶሊኒ፥ የአኗኗር ዘይቤ እና ጥልቅ የስብዕና መገለጫ ሌሎች የወንድማማችነት ፍቅር ምልክቶችን እንዲላበሱ ያስችላቸዋል” ብለዋል።

የአሲሲው ቅዱስ ፍራንችስኮስ ምሳሌ
ለዚህም የአሲሲውን ቅዱስ ፍራንችስኮስ እንደ አብነት የጠቀሱት አባ ፓሶሊኒ፥ ትኅትና እግዚአብሔርን ለመከተል መስፈርት እና ጥልቅ የማንነታችን አካል ነው” ብለው፥ በቅዱስ ፍራንችስኮስ እና በሱልጣን ማሊክ አል-ካሚል መካከል ያለውን ግንኙነት አብራርተዋል።

ከግንኙነታቸው በኋላ ሱልጣኑ ወደ ክርስትና ባይመለስም ነገር ግን ቅዱስ ፍራንችስኮስ በሰጠው ዕድል መልካም አቀባበል እና እንክብካቤ ማድረጉን አባ ፓሶሊኒ ገልጸው፥ “ክርስቲያኖች በበጎነት ላይ የባለቤትነት ድርሻ ባይኖራቸውም ነገር ግን ሌሎች እንዲለማመዱት መፍቀድ አለባቸው” ሲሉ አበክረው ተናግረዋል።

በሌሎች ላይ ሳይፈርዱ እውነተኛ መሆን
መሠረታዊ በሆነው የመጨረሻው ፍርድ ምሳሌ ላይ ያስተነተኑት አባ ፓሶሊኒ፥ ይህም በሰዎች ላይ መፍረድ እንደማይገባ የሚያስታውስ መሆኑን ገልጸው፥ በሌሎች ላይ መፍረድ ድርሻችን እንዳሆነ እና በሌሎች ላይ መፍረድን የምናቆም ከሆነ አስፈላጊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ብቻ ማትኮር የሚቻል መሆኑን እና
የበለጠ እውነተኞች በመሆን በሥራችንም መመስገን እንደሚቻል እና “ምስጋና በነጻ የሚሰጥ እንጂ በገንዘብ የሚገዛ አይደለም” ሲሉ አስገንዝበዋል።

ሙሉ የሆነ ስጦታ
“ወደ ዕድለኝነት የሚያዘነብሉ ሁኔታዎችን እና ተስፋዎችን በማስወገድ የሰው ልጅ ብቸኛውን እና እውነተኛውን መንገድ ማለትም ሙሉ ደስታን መቀበል ይችላል” ያሉት አባ ፓሶሊኒ፥ ይህም ውሮታን ከመክፈል ወይም በውድድር ተስፋ ከሚነዱ ሥራዎች መላቀቅን እንደሚያካትት አስረድተው፥ “ይህን ካደረግን በኋላ ብቻ ሌሎችም ለእኛ እንዲያደርጉልን በመፍቀድ ከንቱነትን በማሸነፍ ራሳችንን ጥልቅ እና ተጨባጭ ለሆነ ደስታ ክፍት ማድረግ እንችላለን” ሲሉ ተናግረዋል።

የመልካምነት ዋጋ
ወደ እግዚአብሔር መንግሥት የሚያስገባን እውነተኛ ቁልፍ “የማይገለጽ በጎነት ነው” ያሉት አባ ፓሶሊኒ፥ ይህ በጎነት እኛ ሳናውቀው ያደረግነውን ነገር ግን ሌሎች የሚገነዘቡት ነው” ሲሉ አስረድተዋል።

አባ ፓሶሊኒ ስብከታቸውን ሲያጠቃልሉ፥ “በዘመኑ ፍጻሜ በጣም የሚያስደንቀው ነገር፥ እግዚአብሔር ከእኛ የሚጠብቀው ሌላ ሳይሆን በፍቅር እርሱን እንድንመስል ከፍተኛ ፍላጎት እንዳለው ማውቅን ነው” ሲሉ ገልጸዋል። “ውሎ አድሮ የሚያስጨንቀው የጥሩ ወይም የመጥፎ ሥራዎች ብዛት ሳይሆን ነገር ግን በእነርሱ አማካይነት ሙሉ በሙሉ እራሳችንን መሆናችን ነው” ብለዋል።  

ተስፋን ለመስጠት ትኅትናን ማካተት
አባ ሮቤርቶ ፓሶሊኒ የአውሮፓውያኑ የገና እና የኢዮቤልዩ በዓል በተቃረበበት በዚህ ወቅት፥ ሁሉም ሰው የወንጌልን ተስፋ ለሌሎች ለማካፈል ትኅትናን እንዲመርጥ ጋብዘው፥ በተለይም ጠላት ወይም ግዴለሽ በሚመስል ዓለም ውስጥ ደካማ የሆኑ ልጆቹ መሐሪ እና ዘወትር ተወዳጅ ከሆነው እግዚአብሔር ጋር ለመገናኘት መጠባበቅ እጅግ አስፈላጊ መሆኑን አበክረው ገልጸዋል።

በቅድስት መንበር ለከፍተኛ ጳጳሳዊ ምክር ቤቶች ስብከታቸው የሚያሰሙ ፍራንችስካዊ ካኅን አባ ሮቤርቶ ፓሶሊኒ፥ የኢዮቤልዩ ቅዱስ በርን በታላቅ ቅንነት መሻገር፣ ቤተ ክርስቲያን ለዘመናት ካከናወነችው መልካም ተግባር ጋር እውነተኛ ተስፋን እንደሚያመጣ፣ የእግዚአብሔር ጸጋ የሰውን ልጆች ትጉ የወንጌል አብሳሪዎች እንዲያደርጋቸው በመጠየቅ፥ “አዲስ ሰማይን እና አዲስ ምድርን በተስፋ መጠባበቅ” የሚለውን የቅዱስ ዓመት ጸሎት በመድገም ስብከታቸውን ደምድመዋል።

 

21 December 2024, 15:32