ፈልግ

አዲስ የወጣቶች ጉዳይ አማካሪ ቡድን የ5 ዓመት ሥራውን በቫቲካን ጀመረ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ አዲስ ዓለም አቀፍ የወጣቶች ጉዳይ አማካሪ በመሆን ሥራቸውን የጀመሩ ሃያ ወጣቶችን በቫቲካን ተቀብለው የማበረታቻ ምክራቸውን ለግሠዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

“በሕይወት ጉዞአችን አንዳንድ ጊዜ የምንፈልገውን መመሪያ የማናገኝ ቢመስለንም እንኳን “ክርስቶስ ሕያው ነው!” የሚለውን ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳን በማንበብ ብቻ የአካሄዳችንን አቅጣጫ እናገኛለን” ሲል በቅድስት መንበር የምእመናን እና የቤተሰብ ሕይወት መምሪያ ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ሥር የሚገኝ አዲስ የዓለም አቀፍ ወጣቶች አማካሪ ቡድን “IYAB” አባል የሆነው ዚምባቡያዊ ወጣት ሰለስቲኖ ሙፕፊጎ ተናግሯል።

በ 2010 ዓ. ም. በተካሄደው የወጣቶች ሲኖዶስ ማግሥት ይፋ የወጣው ሐዋርያዊ ሠነድ፥ ወጣቶች ጽ/ቤታቸውን ለመደገፍ የጀመሩትን ተነሳሽነት እንዲመራው በማለት በቅድስት መንበር የምእመናን እና የቤተሰብ ሕይወት መምሪያ ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤትን ጠይቋል።

በ2015 ዓ. ም. ሥራውን የወሰደው የመጀመሪያው የዓለም አቀፍ ወጣቶች ጉዳይ አማካሪ ቡድን የአምስት ዓመት የአገልግሎት ዘመኑን ካጠናቀቀ በኋላ ይህ የሁለተኛ ዙር አማካሪ ቡድን እንደሆነ ታውቋል።

እንደ ክርስቲያን ወጣቶች የሕይወት መንገድ ማግኘት
በሮም በተካሄደው የመጀመሪያ ስብሰባ ማጠቃለያ ላይ ከቫቲካን የዜና አገልግሎት ጋር ቆይታ ያደረገው ወጣት ሰለስቲኖ፥ በ 2010 ዓ. ም. በተካሄደው የወጣቶች ሲኖዶስ ማግሥት “ክርስቶስ ሕያው ነው!” በሚል አርዕስት ይፋ የሆነውን ሐዋርያዊ ሠነድ በማስታወስ ለርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ምስጋናውን አቅርቧል።

በሮም ያካሄዱት ስብሰባ አዲስ የተዋቀረው አማካሪ ቡድኑ በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት ውስጥ ውጤታማ ለመሆን የሚያግዝ ወዳጅነት ለመመሥረት ማስቻሉን ተናግሯል። በስብሰባው ወቅት በሕልሞቻችን እና ልምዶቻችን ላይ በማትኮር፥ እንዴት አንድ ላይ ማምጣት እንደምንችል እና በኅብረት ልንሠራበት በምንችልበት ተልዕኮ ላይ አተኩረናል” ሲል ገልጿል።

ወጣት ሰለስቲኖ በዚምባቡዌ ከሚገኙት ወጣቶች ጋር ለአራት ዓመታት ያበረከተው የወጣቶች ሐዋርያዊ አገልግሎት ተግባር ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እና በቅድስት መንበር የምእመናን እና የቤተሰብ ሕይወት መምሪያ ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ወጣቶችን በሚመለከቱ ጉዳዮች ላይ ለሚያቀርቧቸው ምክረ ሃሳቦች ድጋፍ ሊሆን እንደሚችል ያለውን ተስፋ ገልጿል።

በሃያ ወጣቶች ተዋቅሮ ጥቅምት ወር ላይ የተሾመው ይህ ሁለተኛው የዓለም አቀፍ ወጣቶች አማካሪ ቡድን “IYAB” ከተለያዩ የዓለም ክፍሎች የተውጣጣ ሲሆን ብዙዎቹ የቡድኑ አባላት ከዓለም አቀፍ እንቅስቃሴዎች፣ ማኅበራት እና ማኅበረሰቦች የተወጣጡ መሆናቸው ታውቋል።

በዕለት ተዕለት ሕይወት እና ኅብረተሰብ ውስጥ እግዚአብሔርን ማግኘት
የአማካሪ ቡድኑ አባል ደቡብ ኮሪያዊት ወጣት ጂዩን ሊ፥ ቡድኑ የሲኖዶሳዊነት ዘዴን የሚጠቀም መሆኑን በማስረዳት ለቫቲካን የዜና አገልግሎት እንደተናገረችው፥ የአማካሪ ቡድኑ ሥራ ከራስ ሕይወት ተሞክሮዎች የሚመነጭ እና ያንን ተሞክሮ በቅድስት መንበር ውስጥ ለሚገኝ የምእመናን እና የቤተሰብ ሕይወት መምሪያ ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ማካፈል ነው” ብላ፥ ከልዩ ልዩ ሃያ አገራት የተገኙ ልምዶቻችንን ለመቃኘት በመንፈስ ቅዱስ መሪነት የመጓዝ ዘዴን እንጠቀማለን” ስትል አስረድታለች።

ደቡብ ኮሪያ ውስጥ የሚገኝ የአናሳ ካቶሊክ እምነት ተከታይ ምዕመናን አባል መሆኗን የገለጸችው ወጣት ጂዩን ሊ የራሷን ተሞክሮ ስትናገር፥ “እግዚአብሔር ለእኔ የት ነው ያለው? በሕይወቴ ውስጥ እንዴት ይሳተፋል? ” በማለት ራሷን በንቃት እንድትጠይቅ ማድረጉን ተናግራለች።

የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ቡድን አባል በመሆን ከሌሎች ወጣቶች ጋር ባላት ግንኙነት እና አገልግሎት መልስ ማግኘቷን የምትገልጸው ወጣት ጂዩን ሊ፥ በእነዚህ ልምምዶች መካከል እግዚአብሔር በግለሰብ፣ በቡድን እና እንደ ማኅበረሰብም በሰዎች ውስጥ እንዴት እንደሚሠራ መገንዘብ መቻሏን አስረድታለች።

ደፋር ወጣቶች እንዲሆኑ የሚያግዝ የር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ማበረታቻ
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ ከዓለም አቀፍ የወጣቶች ጉዳይ አማካሪ ቡድን ጋር ዓርብ ታኅሳስ 4/2017 ዓ. ም. ጠዋት በቫቲካን ተገናኝተው፥ የቀጣዩን አምስት ዓመት ሥራውን ሲጀምር ብርታትን የሚሰጥ ምክር ለግሠዋል።

“ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ጋር ከመገናኘታችን በፊት ፈርተን ነበር” በማለት ሳትሸሽግ የተናገረችው ወጣት ጂዩን ሊ፥ “ቅዱስነታቸው በቫቲካን መልካም ቀባበል ካደረጉልን በኋላ በሰጡን ማበረታቻ ከፍተኛ ጉልበት አግኝተናል” ስትል ለቫቲካን የዜና አገልግሎት አስረድታለች።

 

16 December 2024, 16:42