በቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ውስጥ የሚገኘው የሚካኤል አንጄሎ የእመቤታችን ሐውልት እድሳት ተጠናቀቀ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
የመጭው የኢዮቤልዩ ክብረ በዓል ዝግጅት አካል የሆነውን የሐውልቱን የእድሳት ሥራን በበላይነት የሚከታተለው የቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ አስተዳደር ጽሕፈት ቤት ሲሆን፥ ከዚህ በፊት እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ 1973 ተገጥሞለት የነበረው መስተዋት አንድ ግለሰብ በፈጸመው ጥቃት ጉዳት ደርሶበት እንደ ነበር ይታወሳል።
መስተዋት የመተካት ሥራ ከስድስት ወር ያልበለጠ ጊዜ የወሰደ ሲሆን፥ ዓላማውም ጸሎታቸው ወደ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ለማድረስ ወደ ቫቲካን የሚመጡ መንፈሳዊ ነጋዲያን እና ለጎብኝዎች በተቻለ መጠን ጥሩ ዕይታ እንዲኖረው ለማድረግ ያለመ እንደሆነ ታውቋል።
የቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ አስተዳደር ፕሬዝዳንት ብፁዕ ካርዲናል ማውሮ ጋምቤቲ በመልዕክታቸው፥ በዛሬው ውስብስብ በሆነ ዓለም አቀፍ ጂኦፖለቲካዊ አውድ ውስጥ የእግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስን የምታቀርበውን የተባረከች እናታችን ቅድስት ማርያምን ምእመናን እንደገና እንዲያጤኗት ለማስቻል እንደሆነ ገልጸው፥ ከመስቀል የወረደው ኢየሱስ ክርስቶስ በትንሳኤው ሃይል በልባችን ውስጥ እርቅ በመፍጠር የወንድማማችነት እና የሰላም መንገዶችን ለመገንባት እንደሚያስችል አስረድተዋል።
ሐውልቱን ለማደስ የተደረጉት ማሻሻያዎች
ከሃምሳ ዓመታት በኋላ የተካሄደው መስታወት የመተካት ሥራ በተፈጥሮው ለመዋቅራዊ ስጋቶች እና ውበት ምክንያቶች አስፈላጊ መሆኑን የባዚሊካው የቴክኒክ ቢሮ ኃላፊ ኢንጂነር አልቤርቶ ካፒታኑቺ አስረድተዋል። ፕሮጀክቱ ይበልጥ ግልጽ የሆኑ መስተዋቶችን መግጠም ብቻ ሳይሆን በሜካኒካል የላቀ ጥቅም ያለው እንደሆነም አስረድተዋል።
ለበጎ አድራጊዎች የቀረበ ምስጋና
ፕሮጀክቱን ለመጀመር የሚያስችንል የገንዘብ ድጋፍ የተገኘው ከጣሊያን ፒዬሞንት ክልል ከመጡ የሥራ ፈጣሪዎች እና ባለሙያዎች ቡድን በተገኘ ልገሳ ሲሆን ከለጋሾቹ መካከልም ጥቂቶቹ በጣሊያን ውስጥ የሚገኙ የግል ባንኮች፣ የግንባታ ተቋራጭች፣ አታሚ ድርጅቶች ይገኙበታል።
አዲስ ብርሃን የማስገባት ሥራ
ወደ እመቤታችን ሐውልት በቂ ብርሃን ማስገባት የእድሳቱ ሥራ ቁልፍ አካል ሲሆን ለመላው ቤተ መቅደስ ዘመናዊ የብርሃን ሥርዓት በመዘርጋት በአዳዲስ ቴክኖሎጂዎች ሙሉ የእድሳት ሥራ የተካሄደ ሲሆን፥ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ 2017 የመብራት ሥርዓቱን ነድፎ ተግባራዊ ያደረገው ጉዚኒ የተሰኘ የጣሊያን ኩባንያ እንደ ነበር ይታወሳል።
ተጨማሪ የእድሳት ሥራ
የቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ አስተዳደር በባዚሊካው ውስጥ የሚገኝ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ቤተ መቅደስን ጨምሮ ሌሎች ክፍሎችን በትልቅ ባለ ቀለም መስታወቶች በመሸፈን ተከታታይ የማጠናከሪያ እና የእድሳት ሥራዎችን ማከናወኑ ታውቋል።
በባዚሊካው ውስጥ የምትገኝ የእመቤታችን ጸሎት ቤት
የእመቤታችን ቤተ መቅደስ አጠቃላይ የጌጣጌጥ ሥራ ማዕከላዊ ጭብጥ የመስቀልን ክብር እና የኢየሱስ ክርስቶስ የማዳን ኃይልን የሚገልጽ እንደ ሆነ የተመለከተ ሲሆን፥ ሚካኤል አንጀሎ ይህን የጥበብ ሥራ በ23 ዓመት ዕድሜው እንደ ጎርጎሮሳውያኑ ከ1498 እስከ 1499 ድረስ ሠርቶ እንደ ጨረሰው ይነገራል።
የሚካኤል አንጄሎ የእመቤታችን ሐውልት
በወጣትነት ዕድሜዋ የሞተው ልጇን ታቅፋ በእርጋታ የምትጨነቅ እና የምታዝን እናቱ የሚያሳይ የእምነ በረድ ሥራን ሚካኤል አንጄሎ በ 23 ዓመት ዕድሜው እንደ ጎርጎሮሳውያኑ ከ 1498-1499 ሠርቶ መጀመሪያ ያቀረበው ለካርዲናል ዣን ደ ቢልሄረስ-ላግራውላስ መቃብር እንደ ነበር ይታወሳል።
ሐውልቱ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ ታኅሳስ 3/1749 ለምእመናን ዕይታ እንዲያመች በእምነ በረድ በተሠራ ቅዱስ መስቀሉ ፊት እንዲቀመጥ የተደረገ ሲሆን፥ ከ1964-1965 በነበሩ የተወሰኑ ወራት መካከል ከዚህ በፊት ታይቶ የማያውቅ የውቅያኖስ ጉዞ በማድረግ ለዓለም አቀፍ ትርኢት ወደ ኒውዮርክ መወሰዱ ይታወሳል።
ሐውልቱ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በግንቦት 21/1972 በድንግል ማርያም ግራ በኩል እና ፊት ላይ የተፈጸመው ጥቃት ያደረሰውን ጉዳት ተከትሎ በባለሙያዎች ከታደሰ በኋላ አሁን በተተካው ትልቅ መስታወት ተጠብቆ ቆይቷል።