በአውሮፓውያኑ የብርሃነ ልደቱ ዋዜማ በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ዝግጅቶች እንደሚቀርቡ ተነገረ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
በዝግጅቱ ላይ ብፁዕ ካርዲናል ማውሮ ጋምቤቲ፣ አባ ኢብራሂም ፋልታስ እና አባ ኤንዞ ፎርቱናቶ ምስክርነታቸውን እንደያቀርቡ ሲጠበቅ በተጨማሪም በዜማ ኮንሴርቱ ላይ እንደ ቦሴሊ፣ ባሊዮኒ እና አሌቪ የመሳሰሉ ታዋቂ ድምጻውያን የሚሳተፉ ሲሆን፥ እውቁ ተወዛዋዥ ሮቤርቶ ቦሌም እንደሚገኝ ታውቋል።
በአውሮፓውያኑ የብርሃነ ልደቱ በዓል ዋዜማ እና የኢዮቤልዩ ልዩ ምሽት ማለትም ማክሰኞ ታኅሳስ 15/2017 ዓ. ም. የተዘጋጀውን መስዋዕተ ቅዳሴን እና ቅዱስ በር የመክፈት ሥነ-ሥርዓትን ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እንደሚመሩት ታውቋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ከሚመሩ የኢዮቤልዩ ዓመት መግቢያ ሥነ-ሥርዓት ቀጥሎ የዜማ ኮንሴት፣ ባሕልን እና ወጎችን አጣምሮ የያው ዝግጅት እንደሚካሄድ ታውቋል። በኤሌኖራ ዳንኤሌ የተዘጋጀው መርሃ ግብሩ ከቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ተመልካቾችን ወደ ቅዱስ ምሽት ድባብ የሚሸኙት እንደ አንድሪያ ቦሴሊ፣ ክላውዲዮ ባሊዮኔ፣ ጆቫኒ አሌቪ፣ በቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ የቅድስት ጁሊያ ቤተ ጸሎት መዘምራን የመሳሰሉ ልዩ አርቲስቶች ዝግጅቶቻቸውን እንደሚያቀርቡ ይጠበቃል። በቫዮሊን ተጫዋጭ አናስታሲያ ፔትሪሻክ አጃቢነት የሚቀርብ የሮቤርቶ ቦሌ ውዝዋዜ ወደ ቅዱስ በር የመቅረብ ምሳሌን የሚገልጽ ይሆናል።
ልዩ ልዩ ምስክርነቶች
የኢዮቤልዩ ዓመት የመጀመሪያ ዝግጅት የሆነውን “የብርሃነ ልደቱ ማስታወሻ” በ“ራይ” የጣሊያን ቴሌቪዥን አማካይነት የሚያስተዋውቁት የቅዱስ ጴጥሮስ ጳጳሳዊ ባዚሊካ ሊቀ ካህናት እና የቅዱስነታቸው ረዳት ካርዲናል ማውሮ ጋምቤቲ ሲሆኑ፥ በቤተልሔም ውስጥ ከሚገኘው የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት ሥፍራ ጋር በመገናኘት ንግግር የሚያደርጉት የቅድስት አገር ረዳት ተንከባካቢ አባ ኢብራሂም ፋልታስ እንደሚሆኑ ታውቋል።
የምስጋና እና የተስፋ ጊዜ
“የብርሃነ ልደቱ በዓል ሁሉንም ሰው በአስተንትኖ፣ በምስጋና እና በተስፋ አንድ የሚያደርግ ሁሉ አቀፍ በዓል ነው። እንደ ዘንድሮ የዓለም ሕዝብ በብርሃነ ልደቱ ምሽት ዓይኑን በቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ላይ አሳርፎ አያውቅም” በማለት የባዚሊካው ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክተር የሆኑት አባ ኤንዞ ፎርቱናቶ አስታውቀዋል። የቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ የቅዱስ በር የመክፈቻ ሥነ-ሥርዓት ላይ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለቤተ ክርስቲያን የሚሰጡት ደስታ ቀጣይነት እንዲኖረው የሚያደርግ ነው” ሲሉ ገልጸዋል።
ለሥነ ጥበብ ሰዎች ሴቶች እና ወንዶች ምስጋናቸውን ያቀረቡት አባ ኤንዞ በማከልም “በእነዚህ ሰዎች ተሰጥኦዎች አማካይነት በዓለም አቀፋዊ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ አስፈላጊ ክስተት መደሰት ችለናል” ብለው፥ “ይህ ክስተት በሰው ልጅ ላይ ትኩረት የምንሰጥበት ጊዜ እና ቤተ ክርስቲያን ለሁሉም ሰው በተለይም ለአቅመ ደካሞች፣ ለተናቁት እና ለድሆች መሐሪ እና እንግዳ ተቀባይ እናት ነች” ሲሉ ተናግረዋል።
ዘንድሮው “ራይ” በተሰኘ የጣሊያን ቴሌቪዥን ለሦስተኛ ጊዜ የሚቀርበው የብርሃነ ልደቱ በዓል የዋዜማ ሥነ-ሥርዓት በዋና መሪው ማርቼሎ ካናሜያ የተዘጋጀ፣ በፓውላ ሚሌቲች የተጻፈ እና በማርኮ ካፓሶ በሚመራ የስርጭት ፕሮግራም ላይ የተካተተ እንደሆነ ታውቋል።