ፈልግ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ የ2025 የዓለም የሰላም ቀንን በማስመልከት ባስተላለፉት መልዕክት ዙሪያ ጋዜጣዊ መግለጫ ሲሰጥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ የ2025 የዓለም የሰላም ቀንን በማስመልከት ባስተላለፉት መልዕክት ዙሪያ ጋዜጣዊ መግለጫ ሲሰጥ 

የር. ሊ. ጳጳሳቱ የሰላም ቀን መልዕክት ልባችንን እና አእምሮአችንን ለመለወጥ የሚያስችለን ግብዣ ነው ተባለ

ታህሳስ 23 የሚከበረውን 58ኛው የዓለም የሰላም ቀንን አስመልክቶ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ ያስተላለፉትን መልእክት አስመልክቶ የቅድስት መንበር ጋዜጣዊ መግለጫ ጽህፈት ቤት መግለጫ ሰጥቷል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ በአውሮፓዊያኑ አዲስ ዓመት መግቢያ ላይ የሚከበረውን የዓለም የሰላም ቀን አስመልክተው “ዕዳችንን ይቅር በለን፡ ሰላምህን ስጠን” በሚል ርዕስ ያስተላለፉት መልእክት ታህሳስ 3 ቀን 2017 ዓ.ም. ሐሙስ ጧት በቫቲካን ጋዜጣዊ መግለጫ ጽህፈት ቤት ቀርቧል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳቱ በመልዕክታቸው “የተስፋው ነጋዲያን” በሚል መሪ ቃል የሚከበረውን የ2025 የኢዮቤልዩ ዓመትን በመጥቀስ፣ የኢዮቤልዩ ጥልቅ ትርጉም የተጨቆኑትን ነፃ ለማውጣት ዓለም አቀፍ የኃጢአትና የዕዳ ስርየት የሚገኝበት ልዩ ዓመት መሆኑን አጉልተው አሳይተዋል።

በጋዜጣዊ መግለጫው ላይ ንግግር ያደረጉት በቅድስት መንበር የሰው ልጅ ሁለንተናዊ ዕድገት አገልግሎት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ሃላፊ ብፁዕ ካርዲናል ሚካኤል ቸርኒ፣ የካቶሊክ ሞቢሊዚንግ ኔትዎርክ ዋና ዳይሬክተር ክሪሳኔ ቫይላንኮርት መርፊ እና የቀድሞ ፈንጂ አምራች አሁን ላይ ደግሞ በተለይም በግጭት ምክንያት ህይወታቸው ለአደጋ ለተጋለጡ ሰዎች እርዳታ ለሚያቀርበው ‘ኢንተርሶስ’ ከተሰኘው ግብረሰናይ ድርጅት ጋር እየሰሩ የሚገኙት ቪቶ ፎንታና እንደሆኑ ለማወቅ ተችሏል።

ይቅርታ፣ መታደስ፣ ዓለም አቀፋዊ ኃላፊነት
ብፁዕ ካርዲናል ቸርኒ በመልዕክቱ እና በኢዮቤልዩ ዓመት መካከል ያለውን ሃሳብ ሲገልጹ፥ መልዕክቱ የ ‘ኃጢአት’ እና ‘ዕዳ’ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ትርጉሞችን በማጣመር ይቅርታን፣ መታደስን እና ዓለም አቀፋዊ ኃላፊነትን እንደሚጠይቅ አስረድተዋል።

በዚህም አንፃር በዓለም ላይ ያሉ ኢፍትሐዊ ድርጊቶችን እና ክፋትን ለመቋቋም በጌታች ኢየሱስ ክርስቶስ ላይ ያለንን እምነት እንድናጠናክር ይጋብዘናል ብለዋል። ለሌሎች በተለይም ለድሆች እና ለምድራችን ባለን ፍቅር እና ሃላፊነት በመመራት ልብ እና አእምሮን ለመለወጥ ቃል መግባትን፣ አንድነትን እና እንክብካቤን የሚያጎለብት የለውጥ አመለካከትን በመቀበል የጦር መሳሪያ ቅነሳ ላይ በትጋት መስራትን፣ የውጭ ዕዳን መሰረዝን፣ እንዲሁም የሞት ቅጣት ማስወገድን እና የረሃብ አደጋ መዋጋትን የመሳሰሉ ዓለም አቀፍ እርምጃዎችን መውሰድን እንደሚያካትት አብራርተዋል።

ካርዲናል ቸርኒ እንዳብራሩት ይቅርታን፣ ፍትህን፣ እና አንድነትን ያካተቱት እነዚህ እርምጃዎች በችግር በተሞላ ዓለም ውስጥ የተስፋ እና የሰላም መንገዶች መሆናቸውን አፅንዖት ሰጥተው ገልጸዋል።

የህይወት ባህልን መገንባት
በዩናይትድ ስቴትስ የሞት ቅጣት እንዲወገድ የሚሟገተው የካቶሊክ ሞቢሊዚንግ ኔትዎርክ ዋና ዳይሬክተር የሆኑት ወይዘሮ ክሪሳኔ ቫይላንኮርት መርፊ እንደተናገሩት የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳቱ መልዕክት ይቅርታ የሰላም መሠረት መሆኑን አጉልቶ ያሳያል ብለዋል።

ከዚህም ባለፈ ግለሰቦች እና ማህበረሰቦች የኃጢያትን አሰራር እንዲቃወሙ እና በተለይ በተሃድሶአዊ ፍትህ በኩል ድነትን እንዲያበረታቱ በመልዕክታቸው ማሳሰባቸውን አስታውሰዋል።

ወይዘሮ ክሪሳኔ አክለው እንደገለጹት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ በመልዕክታቸው በዋናነት ተግባራዊ እርምጃ እንዲጀመር ጥሪ ማቅረባቸውን ገልጸው፥ ይቅርታን እንድንቀበል እና እንደ የሞት ቅጣት ያሉ የጥቃት መዋቅሮችን እንድናፈርስ፣ በምህረት እና በፍትህ ላይ የተመሰረተ የህይወት ባህል እና ሰላም እንዲገነባ ግብዣ ያቀርባል ብለዋል።

የጦር መሳሪያ ንግድ
‘ኢንተርሶስ’ ከተሰኘው ግብረሰናይ ድርጅት ጋር እየሰሩ የሚገኙት የቀድሞ ፈንጂ አምራች ጣሊያናዊው አቶ ቪቶ አልፊየሪ ፎንታና በበኩላቸው፣ የጦር መሳሪያ ንግድ በአቋራጭ ትርፍ ለማግኘት በማሰብ እንዴት እንደሚዳብር በመጥቀስ፣ የረዥም ጊዜ ጉዳቶችን ችላ በማለት ግጭቶችን በማቀጣጠል እና በማስፋፋት ትርፍ መሰብሰብ ላይ ብቻ እንደሚያተኩር አስረድተዋል።

አቶ ቪቶ ፎንታና የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳቱ አስተምህሮ ጦርነት፣ ውሸት እና ኢፍትሃዊነት ማህበረሰቦችን እንዴት እንደሚያፈራርሱ እና ጥቂቶችን ተጠቃሚ ብሎም ጉልበተኛ እንደሚያደርጉ በመጥቀስ፥ እንዲሁም በጦርነት የተጎዱ ሰዎች የበጎ አድራጎት ሳይሆን ፍትህ እንደሚያስፈልጋቸው በግልጽ ያስረዳሉ ብለዋል።

ባለሙያው አክለውም ጉዳቱን ለመጠገን እና የመልሶ ማቋቋም ሥራዎችን ለመደገፍ የሞራል ሃላፊነት የሚሸከሙት ከግጭት ትርፍ የሚያገኙ ሰዎች መሆናቸውን ብጹእነታቸው ደጋግመው ሲያነሱት የነበረውን ፅንሰ-ሀሳብ በመድገም አሳስበዋል።

አቶ ቪቶ በመጨረሻም በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ አስተምህሮ ላይ በመመርኮዝ፥ እውነተኛ ሰላም እንዲመጣ ከተፈለገ የዓለም ማህበረሰብ በጦርነት ለተጎዱ ማህበረሰቦች እውቅና መስጠት እንዳለበት እና እርቅን፣ ፍትህን እና አብሮ መኖርን ለማስፈን በቁርጠኝነት መስራት እንደሚያስፈልግ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።
 

13 December 2024, 14:13