የዓለም አቀፍ ዕዳ ቀውስ የልማትና የአየር ንብረት ቀውስም ጭምር እንደሆነ ተነገረ
አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ
ባለፈው ዓመት የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት እንደዘገበው ዝቅተኛ ገቢ ካላቸው ታዳጊ ሀገራት መካከል ከግማሽ በላይ የሚሆኑት በእዳ ጫና ውስጥ መሆናቸውን ወይም ከፍተኛ ስጋት ውስጥ መግባታቸውን የገለጸ ሲሆን፥ ከ3 ቢሊዮን በላይ የሚሆኑ ሰዎች የሚኖሩት ከትምህርት ይልቅ ለዕዳ እና ለወለድ ክፍያ በርካታ ገንዘብ በሚያወጡ አገራት ውስጥ እንደሆነ ይፋ አድርጓል።
የቫቲካን ተጽዕኖ
ቫቲካን ሰኔ 2016 ዓ.ም. ለዚህ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ለሚገኘው የዓለም የዕዳ ቀውስ ላይ መፍትሄዎችን ለመፈለግ ዓላማ ያደረገ የውይይት መድረክ አዘጋጅታ ከፋይናንስ ተቋማት፣ ከአካዳሚክ ባለሙያዎች፣ ከሲቪል ማህበረሰብ ተሟጋቾች እና ከሀይማኖት አባቶች ጋር መክራለች።
በቫቲካን የቅድስት መንበር ጳጳሳዊ የማህበራዊ ሳይንስ ከፍተኛ የትምህርት ተቋም (PASS) አባል የሆኑት የቀድሞው የአርጀንቲና ሪፐብሊክ የኢኮኖሚ ሚኒስትር ማርቲን ጉዝማን ከቫቲካን ዜና ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ስብሰባው የተካሄደው ጉዳዩ በጣም ከሚያሳስባቸው ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ ጋር ቀድሞ በተደረገ ውይይት መሆኑን አስረድተዋል።
ስብሰባው ከተደረገ ከስድስት ወራት በኋላ በቫቲካን የቅድስት መንበር ጳጳሳዊ የማህበራዊ ሳይንስ ከፍተኛ የትምህርት ተቋም እና የፖሊሲ ጥናት ኢኒሺዬቲቭ (IPD) በጋራ በመሆን በመላው የደቡብ ንፍቀ ዓለም ለሚገኙ ሃገራት ዘላቂ የሆነ የእዳ ቅነሳን የሚያበረታታ “ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ማሻሻያ” ምክረ ሃሳብ አሳትመዋል።
የእዳ ወጪ
የፖሊሲ ጥናት ኢኒሺዬቲቭ መስራች የሆኑት ፕሮፌሰር ጆሴፍ ስቲግሊትዝ ከቫቲካን ዜና ጋር ባደረጉት ውይይት የኮቪድ ወረርሽኙን እና በዩክሬን የተከሰተውን ጦርነት ተከትሎ፣ አበዳሪ ሃገራት እና ድርጅቶች የሚሰጡትን ብድር ለመመለስ የሚያወጡት ወጪ እጅግ በጣም ከባድ እንደሆነ በማስረዳት፥ ሁኔታው ከዕዳ ቀውስ በላይ የሆነ የልማት እንቅፋት ነው ሲሉ ተናግረዋል።
ዓለም አቀፍ የቁጥጥር እና የመፍትሄ አሰራር ከሌለ ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት ብድር መክፈል በማይቻልበት እና አከፋፈሉ ወጥ በማይሆንበት ጊዜ ዕዳው እንዲስተካከል ከማሳሰብ ይልቅ የግል አበዳሪዎችን ለማዳን ቅድሚያ ሊሰጡ እንደሚችሉ ገልጿል።
ፕሮፌሰር ጆሴፍ እንደተናገሩት በሚሊዮን የሚቆጠሩ የተራቡ ሰዎች ባሉበት ሃገር ዕዳውን ለመክፈል ቅድሚያ የሚሰጡ መንግስታትን ተግባር “ከልጆች አፍ ምግብ ፈልቅቆ እንደ ማውጣት” ነው ሲሉ ገልጸውታል።
ከዚህም ባለፈ በጣም በርካታ በማደግ ላይ ያሉ ሀገራት የገንዘብ እና የገቢ ማሰባሰቢያ መንገዶቻቸው በጣም ውስን ስለሆነ የመጀመሪያ ደረጃ የጤና እንክብካቤ፣ ክትባቶችን እና ለህፃናት የትምህርት አገልግሎትን ለመስጠት እንደሚቸገሩም ጭምር አስረድተዋል።
ለዓለም አቀፍ ዕዳ የቀረቡ ምክረ ሃሳቦች
ሁለቱ ተቋማት በጋራ ያቀረቡት ሰነድ የዕዳ ቀውስን ለመዋጋት ዕዳ ካለባቸው ሀገራት የሚወጡትን ሀብቶች ከማስቆም ጀምሮ የብድር ገበያን ተደራሽነት በትክክል እስከ መግለፅ ያሉ ከ10 በላይ ምክረ ሃሳቦችን በዝርዝር ያቀረበ ሲሆን፥ ከቀረቡት ሀሳቦች አንዱ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ ባለፈው ዓመት ሰኔ ወር ላይ በተደረገው ስብሰባ ዓለም አቀፍ ከወለድ ነፃ የሆነ የብድር ሥርዓትን መልሶ የማዋቀር ዘዴን መፍጠር የሚል ሃሳብ ይገኝበታል።
ከዚህም በላይ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ የፋይናንስ ተቋማት መሪዎችን “በተዋዋይ ወገኖች መካከል የሚደረጉ ውይይቶችን ለመምራት የሚያስችል ዓለም አቀፍ የሥነ ምግባር ደንቦችን እንዲከተሉ” አሳስበዋቸዋል።
ፕሮፌሰር ጆሴፍ ይህ ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የተደረገ ጥሪ እጅግ አስፈላጊ መሆኑን ገልጸው፥ ምክንያቱም ዛሬ ያለው የዕዳ ቀውስ በተለየ መልኩ ከቦንድ ጋር የተያያዙ የብድር አሰጣጦች አዲስ አሰራር በመሆናቸው እንደሆነ ጠቁመው፥ ስለሆነም ይህንን አዲስ ቀውስ ለመቅረፍ የሚቻለው “ለልማታዊ ፋይናንስ” ተስማሚ የሆነ አዲስ ዓለም አቀፍ የብድር አካሄድ መሆኑን አብራርተዋል።
ነገር ግን፣ ይህንን ዓለም አቀፍ ዘዴ ለማሳካት የሚያስፈልገው ገቢን ከማሳደግ ይልቅ በማህበራዊ ፍትህ ላይ ትኩረት ማድረግ እንደሆነ የገለጹ ሲሆን፥ የፖሊሲ ጥናት ተቋሙ መስራች ሃሳቦቻቸውን ተግባራዊ ለማድረግ ያለውን ፖለቲካዊ ተግዳሮት ሲያብራሩ በታዳጊ ሀገራት የሚታየው ሥር የሰደደ ብዝበዛ መሆኑን ጠቅሰዋል።
በቤተክርስቲያን ቅድሚያ ከሚሰጣቸው ጉዳዮች መካከል የተጠቀሰው የዕዳ ቅነሳ
የዘንድሮው የኢዮቤልዩ በዓል መሪ ቃል ተስፋ እንደመሆኑ መጠን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ በያዝነው ዓመት ድሃ አገሮች የተበደሩት ዕዳ የመሰረዝ ወይም የመቀነስ ዕድል የሚሰጥ እንደሆነ ተስፋ በማድረግ ቤተክርስቲያን ለዚህ ጉዳይ ቅድሚያ ሰጥታ እንደምትሰራ አስታውቀዋል።
በቫቲካን የቅድስት መንበር ጳጳሳዊ የማህበራዊ ሳይንስ ከፍተኛ የትምህርት ተቋም እና የፖሊሲ ጥናት ኢኒሺዬቲቭ በዚህ ዓመት ለዘላቂ ፋይናንስ ድጋፍ ያቀረቡትን ማሻሻያ ተግባራዊ ለማድረግ በጋራ እንደሚሰሩ በማሳወቅ፥ “ዓላማውም በያዝነው የኢዮቤልዩ ዓመት አውድ ውስጥ ተጨማሪ ስራ እና ተሳትፎ እንዲኖረው ነው” ሲሉ አቶ ጉዝማን አስረድተዋል።
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ ታህሳስ 23 ለሚከበረው የዓለም የሰላም ቀን በጻፉት ደብዳቤ ላይ “በደላችንን ይቅር በለን፣ ሰላምን ስጠን” የሚለውን መሪ ቃል የመረጡ ሲሆን፥ ብጹእነታቸው ሃገራት “የሰላም መንገድ” ላይ እንዲጓዙ ካቀረቧቸው ሃሳቦች አንዱ “የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታዎች” ማለትም የውጭ እና የስነ-ምህዳር ዕዳን እንደሚያካትት ተገልጿል።
ፕሮፌሰር ጆሴፍ ስቲግሊዝ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ የዕዳ ቀውስን ለመፍታት ያላቸውን ጠቃሚ ሚና በማጉላት፣ “ጠንካራ ክንድ ካለው የፖለቲካ አመራር በተቃራኒ የተለየ ሞራላዊ ሥነ-ምግባር ያለው ዓለም አቀፋዊ አመራር እጥረት” እንዳለ ከጠቀሱ በኋላ፥ “ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ እንደዚህ ዓይነት ዓለም አቀፋዊ የሥነ ምግባር ፖለቲካዊ አመራር ይሰጣሉ” በማለት አጠቃለዋል።