ካርዲናል ኮክ፥ “ር. ሊ. ጳ ቤነዲክቶስ 16ኛ እግዚአብሔር ዘላለማዊ ፍቅር እንደሆነ አስተምረውናል” አሉ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
በቅድስት መንበር የክርስቲያኖች ሕብረት ማስፋፊያ ጳጳሳዊ ምክር ቤት ፕሬዚደንት ብጹዕ ካርዲናል ኩርት ኮክ የቀድሞው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቤነዲክቶስ 16ኛ ዕረፍት ሁለተኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ በቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ማክሰኞ ታኅሳስ 22/2017 ዓ. ም. የቀረበውን ልዩ የመታሰቢያ መስዋዕተ ቅዳሴ መርተዋል።
ብፁዕ ካርዲናል ኩርት የቀድሞው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቤነዲክቶስ 16ኛ ታኅሳስ 22 ቀን 2015 ዓ. ም. ያረፉበት ሁለተኛ ዓመት በማስታወስ በሕይወት እና ትሩፋታቸው ላይ በተለይም በሥነ-መለኮት ግንዛቤያቸው እና ዕድሜ ልክ ለእግዚአብሔር ቃል መሰጠት ላይ በማስተንተን ስብከታቸውን አሰምተዋል።
የጆሴፍ ራትዚንገር (ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቤነዲክቶስ 16ኛ) የተወለዱበት እና ያረፉበት ቀናት ማለትም የተወለዱበትን የሚያስታውስ የሕማማት ሳምንት (ቅዳሜ 1919 ዓ. ም.) እና ያረፉበትን የብርሃነ ልደቱ ሰሞን የሚያስታውስ (2017 ዓ. ም.) በማስታወስ ስብከታቸውን የጀመሩት ብፁዕ ካርዲናል ኩርት፥ ሕይወታቸውን በፋሲካ ምስጢር ውስጥ በማድረግ፥ “እግዚአብሔር የጆሴፍ ራትዚንገር የሕይወት ታሪክ ማዕቀፍ በድነት ታሪክ ውስጥ መጻፉን አረጋግጧል” ሲሉ ተናግረዋል።
ር. ሊ. ጳ. ቤነዲክቶስ 16ኛ እግዚአብሔር በዛሬው ዓለም ውስጥ እንዲገኝ ያደረጉት ጥረት
“ይህ ጥልቅ ግንኙነት በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቤነዲክቶስ 16ኛ ሕይወት እና ሥራ ውስጥ መሪ ኃይል ነበር” ያሉት ካርዲናል ኮክ፥ “ይህን ምስጢር በተግባር ኖረዋል፣ በጠንካራ እምነት አውጀዋል፣ በሥነ-መለኮት ግልጽነቱ ዛሬ ለእኛ ተደራሽ አድርገውታል” ብለዋል።
“በዛሬው ወንጌል ቅዱስ ዮሐንስ የጻፈው የእግዚአብሔር ቃል “ሎጎስ” የቤኔዲክት ሥነ-መለኮት ዋና ማዕከል ሆኗል” ያሉት ብፁዕ ካርዲናል ኮክ፥ “በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል በተገለጸው በእግዚአብሔር ዘላለማዊ ፍቅር ውስጥ ያለውን የሰው ሕይወት ትርጉም አሳማኝ በሆነ መንገድ አሳይተውናል” ብለዋል።
“እግዚአብሔር ፍቅር ነው”
“በእርግጥም ለርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቤኔዲክቶስ 16ኛ የእግዚአብሔር ቃል ከፍቅር ጋር የተሳሰረ ነው” ያሉት ካርዲናል ኮክ፥ “እግዚአብሔር ፍቅር ነው” ('Deus Caritas Est') በሚለው ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳናቸው ላይ እንደገለጹትም ሕይወታቸው እና አስተምህሮአቸው ይህን የመለኮታዊ መረዳት እና ፍቅር የሰው ልጅ ሕልውና እና ዘላለማዊነት እምብርት መሆኑን የሚያንፀባርቁ እንደሆኑ አስረድተዋል።
ለር. ሊ. ጳ. ቤኔዲክት 16ኛ ሕይወት ምስጋናን ማቅረብ
“ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቤኔዲክቶስ 16ኛ ዕድሜአቸውን በሙሉ እግዚአብሔር ብዙውን ጊዜ እንደ ባዕድ በሚታወቅበት ዓለም ውስጥ የእግዚአብሔርን መገኘት ለመመስከር ያደረጉት ቁርጠኝነት እንደ ትሩፋት ውርስ ሆኖ ይቆያል” ያሉት ካርዲናል ኮክ፥ “ጌታ ሆይ! እወድሃለሁ” ያሉትን የመጨረሻ ቃላቸውን በማስታወስ እምነታቸው ለንስሐ የሚመች መሆኑን አስታውሰዋል።
“እግዚአብሔርን የትኩረት ማዕከል ማድረግ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቤነዲክቶስ 16ኛ ዋና ግብ ነበር” ያሉት ካርዲናል ኮክ፥ “እግዚአብሔር ብዙውን ጊዜ እንደ ባዕድ በሚታወቅበትና አልፎ ተርፎም ይህን መስማት በሚሳነን ዘመን ውስጥ ስለ እግዚአብሔር የምናስብበት ጊዜ እንደደረሰ አሳስበውናል” ብለዋል።
ብፁዕ ካርዲናል ኮክ ስብከታቸውን ሲያጠቃልሉ፣ ምእመናን ለርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቤነዲክቶስ 16ኛ ሕይወት ምስጋናቸውን በኅብረት እንዲያቀርቡ፥ በታማኝነት ያወጁትን ዘላለማዊ እውነት መፈለግ እንዲቀጥሉ ጋብዘው፥ እግዚአብሔር በኢየሱስ ክርስቶስ አማካይነት እውን እንደሆነ እና እርሱን ለሚወዱት የዘላለም ሕይወት ሽልማት እንደሆነም አስረድተዋል።
የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቤነዲክቶስ 16ኛ ዕረፍት
በ95 ዓመታቸው ያረፉት የቀድሞው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት በነዲክቶስ 16ኛ እንደ ጎርጎሮሳውያን በ2013 ለርዕሠ ሊቃነ ጵጵስና ከመመረጣቸው በፊት ታዋቂ የነገረ-መለኮት ምሑር እንደ ነበሩ ሲታወቅ፥ የሮም ጳጳስነት አገልግሎታቸውን ከለቀቁ በኋላ ቫቲካን ውስጥ በሚገኘው የ “ማተር ኤክሌሲያ” ገዳም ውስጥ መኖርን መርጠዋል።
“የእግዚአብሔር የወይኑ ሥፍራ ትሁት ሠራተኛ” የነበሩ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቤነዲክቶስ 16ኛ የተለያዩ ሥራዎችን ከሚያስታውሱ በዓለም ዙሪያ ከሚገኙ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤዎች፣ የሃይማኖት መሪዎች፣ የአገራት እና የመንግሥታት መሪዎች ሥፍር ቁጥር የሌላቸው የሐዘን መግለጫዎች ደርሰዋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቤነዲክቶስ 16ኛ ያረፉበትን ዕለት ለማስታወስ በቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ውስጥ በቀረበው መስዋዕተ ቅዳሴ ላይ ባሰሙት ስብከት፥ “የተከበሩ ሰው መሆናቸውን ስናስታውሰው ልባችን ተነክቶአል፤ እርሳቸውን ለቤተ ክርስቲያን እና ለመላው ዓለም ስለሰጠን እግዚአብሔር እናመሰግነዋለን፤ ላደረጉት መልካም ነገሮች ሁሉ እና ከሁሉም በላይ ስለ እምነት እና የጸሎት ምስክርነት፣ በተለይም በእነዚህ መጨረሻዎቹ ጊዜያት ለቤተ ክርስቲያን ጥቅም ሲሉ ያቀረቡትን መስዋዕትነት፣ የአማላጅነታቸውን ዋጋ እና ኃይል የሚያውቀው እግዚአብሔር ብቻ ነው” ሲሉ ገልጸዋል።
የመጨረሻ ስንብት
የዕረፍታቸው ዜና ከተነገረ በኋላ በብዙ ሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በቅድሚያ ቅርብ የሆኑ ሰዎች ቫቲካን ውስጥ በሚገኘው “ማተር ኤክሌሲያ” ገዳም ውስጥ፣ ከዚያም አስክሬናቸው ወደ ቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ሲዛወር ከ200,000 በላይ ምእመናን ለርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት በነዲክቶስ 16ኛ የመጨረሻ ስንብት አድርገዋል።
ታኅሳስ 27 በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ በተዘጋጀው የቀብር ሥነ-ሥርዓት ላይ 50 ሺህ የሚያህሉ ሰዎች ተገኝተዋል። ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ጋር ወደ 130 የሚጠጉ ካርዲናሎች፣ 400 ጳጳሳት እና ወደ 3,700 የሚጠጉ ካህናት በኅብረት ሆነው መስዋዕተ ቅዳሴን አሳርገዋል። ከቅድስት መንበር መግለጫ ክፍል እውቅና የተሰጣቸው 1,600 ጋዜጠኞች የቀብር ሥነ-ሥርዓቱን ለመዘገብ የተገኙ ሲሆን 200 የመገናኛ ብዙኃን ሥነ-ሥርዓቱን በቀጥታ አሰራጭተዋል።
የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቤነዲክቶስ 16ኛ አስከሬን የቀድሞው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ በተቀበሩበት በባዚሊካው የምድር ውስጥ መካነ መቃብር የተቀበረ ሲሆን፥ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ2011 ዓ. ም. ወደ ባዚሊካው እስኪወሰድ ድረስ እዚያው መቆየቱ ታውቋል።