“ክርስቲያን መሆን ማለት እንደገና ሰው መሆንን መማር ማለት ነው!”
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
በቅድስት መንበር የክርስቲያኖች ኅብረት ማስፋፊያ ጳጳሳዊ ምክር ቤት ፕሬዚደንት ብጹዕ ካርዲናል ኩርት ኮክ፥ የቀድሞው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቤነዲክቶስ 16ኛ ዕረፍት ሁለተኛ ዓመት ካስታወሱበት የመስዋዕተ ቅዳሴ ሥነ-ሥርዓት ቀጥለው ለቫቲካን የዜና አገልግሎት በሰጡት አስተያየት፥ “ሟቹ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቤኔዲክቶስ 16ኛ ሌሎችን ቀርበው የሚያናገሩ እና የሚያዳምጡ እጅግ ትሑት ሰው ነበሩ” ብለዋል።
“ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቤኔዲክቶስ 16ኛ ደግ ሰው ነበሩ” ያሉት ብጹዕ ካርዲናል ኩርት ኮክ፥ “ዓይኖቻቸውን ብትመለከት ብዙ የውስጥ ብርሃን እንዳላቸው ማየት ይቻላል” ብለዋል። ለእርሳቸው ክርስቲያን መሆን ሰው በመሆን ላይ የተመሠረተ በመሆኑ ሁለቱ አብረው የሚሄዱ በመሆናቸው ዘወትር እጅግ አስፈላጊ እንደ ነበሩ እና ክርስቲያን መሆን ማለት እንደገና ሰው መሆንን መማር ማለት እንደሆነ በመግለጽ፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቤኔዲክቶስ 16ኛ ጥሩ ምሳሌ ነበሩ” ሲሉ ተናግረዋል።
እግዚአብሔርን መፈለግ
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቤኔዲክቶስ 16ኛ በአንድ ወቅት እንደተናገሩት፥ ረጅም የርዕሠ ሊቃነ ጵጵስና ዓመታት እንደማይኖራቸው፣ ምንም ዓይነት ልዩ እቅድ መጀመር እንደማይችሉ ያውቁ እንደ ነበር የተናገሩት ብጹዕ ካርዲናል ኩርት ኮክ፥ ዋና ተልዕኮአቸው እምነትን ወደ ቤተ ክርስቲያን ማምጣት እንደ ነበር አስረድተዋል።
“የእግዚአብሔር ጥያቄ ማዕከላዊነት” የሥራቸው ሁሉ እምብርት እንደ ነበር የገለጹት ካርዲናል ኩርት ኮክ፥ ማንኛውንም አምላክ ወይም በሰማይ ያለው የማይናገር ግዑዝ አካል ሳይሆን ነገር ግን ለእስራኤል ሕዝብ የተናገረው እና ከሁሉም በላይ በናዝሬቱ ኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ራሱን የገለጠ እግዚአብሔር እንደ ሆነ ተናግረው፥ የእግዚአብሔር እና የኢየሱስ ክርስቶስ የማዕከላዊነት ጥያቄ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቤነዲክቶስ 16ኛ ሥራ ዋና አስኳል ሆኖ ይቀራል” ብለዋል።
የክርስቲያን ተስፋ
ካርዲናል ኩርት ኮክ ከአውሮፓውያኑ የብርሃነ ልደቱ በዓል በኋላ በሚጀምረው የጎርጎሮሳውያኑ 2025 ዓ. ም. የተስፋ ኢዮቤልዩ ዋዜማ ላይ “spe salvi” ወይም “በተስፋ ድነናል” የሚለውን የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቤኔዲክቶስ 16ኛ ሐዋርያዊ ቃለ-ምዕዳንን ጠቅሰው እንደተናገሩት፥ ሐዋርያዊ ቃለ-ምዕዳኑ “እራሱን ከቁም ነገር የማይቆጥር ሰው ብቻ ተስፋ ሊኖረው እንደሚችል ያሳየናል” ብለው፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቤኔዲክቶስ 16ኛ በአንድ ወቅት፥ “እራሳችንን የበለጠ አቅልለን ከወሰድን እንደ መላዕክት እና እንደ ወፎች መብረር እንችላለን” ማለታቸውን አስታውሰዋል።
“ራሳችንን በቁም ነገር ስንመለከት ብዙ ጊዜ ከምድር ጋር እንጣበቃለን” ያሉት ካርዲናል ኩርት ኮክ፥ ተስፋ ሊኖረን የሚችለው ሕይወታችንን ወደ እግዚአብሔር ካቀናን ብቻ እንደሆነ እና ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቤነዲክቶስ 16ኛ የቅዱስ ዓመት ዋና ትርጉም ምን እንደሆነ ያሳዩን ለዚህ ነው” ብለዋል። ይህ በር የሚታይ የኢየሱስ ክርስቶስ ምሳሌ እንደሆነ እና ወደ ቅድስና መድረስ የምንችለው በእርሱ ብቻ እንደሆነ፥ “ይህ ቅዱስ ዓመት ሰዎች በጥምቀት ቃል የገቡትን ቅድስና ማግኘት እንደሚያስችል ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል።
ክርስቲያን እና አባት
የራትዚንገር የምሑራን ቡድን አባል የሆኑት ፕሮፌሰር ራልፍ ዌይማን ለቫቲካን የዜና አገልግሎት እንደተናገሩት፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቤነዲክቶስ 16ኛ እንደ ግለሰብ እና እንደ ካኅን ፈጠሩትን ተጽዕኖ ሲገልጹ፥ “ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቤነዲክቶስ 16ኛ ከሁሉ በፊት ለእኔ ክርስቲያን ነበሩ፤ ይህን መናገር በጣም ቀላል ነው፤ ክርስቲያን ማለት ኢየሱስ ክርስቶስን የለበሰ ሰው ማለት ነው፤ ር. ሊ. ጳ. ቤኔዲክቶስ 16ኛ የቆሙት ለዚህ ነው። በእውነት ክርስቶስን በመከተል ምስክርነትን ሰጥተዋል። ያ በልቤ ውስጥ ጥልቅ ስሜት በመፍጠሩ አመሰግናለሁ። ለእኔ እንደ አባት ነበሩ፤ ከሁሉም በላይ አብረውን የሆኑ ክርስቲያን አባት ነበሩ” ሲል ተናግሯል።
ሊቀ ጳጳስ ጆርጅ ጋንስዌይን በመንፈስ በሮም በመሆን
የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቤነዲክቶስ 16ኛ የረዥም ጊዜ የግል ጸሐፊ የነበሩት ሊቀ ጳጳስ ጆርጅ ጋንስዌይን ዘንድሮ በሮም በተደረገው የመታሰቢያ መስዋዕተ ቅዳሴ ላይ መገኘት ባይችሉም ካለፈው የአውሮፓውያኑ የበጋ ወራት ጀምሮ በቪልኒየስ የሚገኘውን የባልቲክ ግዛቶች ውስጥ እያገለገሉ በአዲስ ዓመት ዋዜማ ላይ በሐሳብ ሮም ውስጥ እንደ ነበሩ ገልጸዋል።
“ዘንድሮ የብርሃን ልደቱን በዓል ያለ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቤኔዲክቶስ 16ኛ ያሳለፍኩበት ሁለተኛ ዓመት ነው” ሲሉ ለቫቲካን የዜና አገልግሎት የተናገሩት ጋንስዌይን፥ “በመልካ-ምድራዊ አቀማመጥ ከቤት ወይም ከሮም በራቅኩ ቁጥር ውስጣዊ ቅርበቴ እየጨመረ ይሄዳል” ብለዋል። “በእርግጥ ሐዘን ይሰማኛል፤ ነገር ግን ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቤኔዲክቶስ 16ኛ ጋር በመሆን ከጎናቸው ሆኜ ማሳለፍ ለቻልኩባቸው ጊዜያት ሁሉ ውስጣዊ ተስፋ እና ምስጋና ይሰማኛል” ብለዋል። “በዚህ ረገድ የብርሃነ ልደቱ በዓል ከሌሎች ዓመታት በጣም የተለየ ቢሆንም ብርሃነ ልደት ምን ጊዜም ቢሆን ብርሃነ ልደት ነው፤ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቤኔዲክቶስ 16ኛ ዕርዳታ እንደተሰጠኝም አውቃለሁ” ብለዋል።
በተጨማሪም በዚህ ቅዱስ ዓመት ልዩ ትርጉም ያለውን የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቤነዲክቶስ 16ኛ “spe salvi” ወይም “በተስፋ ድነናል” የሚለውን ሐዋርያዊ ቃለ-ምዕዳን አስታውሰው፥ ይህ ቃለ-ምዕዳን የሰውን ተስፋ በዋነኝነት ወደ እግዚአብሔር የሚመራ እንደሆነ እና ይህን ተስፋ ያጸናው ራሱ እግዚአብሔር እንደሆነ አስረድተዋል።
የዚህ ተስፋ መሠረት እና ግብ እግዚአብሔር ነው” ያሉት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ጆርጅ ጋንስዌይን፥ ለእኔ “በተስፋ ድነናል” የሚለውን ሐዋርያዊ ቃለ-ምዕዳን ብዙ ጊዜ የሕይወቴ መመሪያ እና ግብ በመሆን ችግሮቼን እንድሻገር የሚያደርገኝ የሕይወቴ ግብ እና በእግዚአብሔር ላይ የተመሠረተውን ተስፋ እንድመለከት የሚረዳኝ ነው” ብለዋል።