የቫቲካን ሬዲዮ ጣቢያ አዘርባጃኒኛን 56ኛ የስርጭት ቋንቋው አደረገ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
አዘርባጃንን የጎበኙ የመጀመሪያው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ 20ኛ የዕረፍት ዓመት በተከበረበት መጋቢት 24/2017 ዓ. ም. አዘርባጃኒኛን 56ኛ የስርጭት ቋንቋ አድርጎ በይፋ አስጀምሯል።
የቀድሞው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ2002 ዓ. ም. በአዘርባጃን ሐዋርያዊ ጉብኝት ባደረጉት ወቅት፥ በሀገሪቱ ውስት የሚገኙ ጥቂት ካቶሊካዊ ምዕመናን ምሳሌ ሆነው ማኅበረሰቡን እንዲመሩ ማሳሰባቸውን፥ የአዘርባጃን ሐዋርያዊ አስተዳዳሪ ብጹዕ አቡነ ቭላዲሚር ፈኬት አስታውሰው፥ በዛሬው ዓለም ሚዲያ እውነትን በማሰራጨት፣ ተስፋን በመስጠት እና የምዕመናንን እምነት በማጠናከር ረገድ ከፍተኛ ሚና እንዳለው ተናግረዋል።
ከቫቲካን መገናኛ ጽ/ቤት ጋር በመተባበር የተጀመረውን ተነሳሽነት የደገፉት ብጹዕ አቡነ ቭላዲሚር፥ በአዘርባጃን የሚገኙ አብዛኞቹ ካቶሊካዊ ምዕመናን የሌላ ቋንቋ ተናጋሪዎች አለመሆናቸን እና ስለ ዓለም አቀፋዊት ቤተ ክርስቲያናቸው ለማወቅ ሁልጊዜ አስተማማኝ ባልሆኑ ምንጮች ላይ እንደሚተማመኑ ገልጸው፥ እውቀትን ለማስፋፋት እና እምነትን ለማጠናከር ይረዳቸው ዘንድ ዕቅዱን ከቫቲካን ሬዲዮ ወይም ከቫቲካን ዜና አገልግሎት ጋር ለመጀመር መወሰናቸውን ገልጸዋል።
ብጹዕ አቡነ ቭላዲሚር አክለውም፥ “አሁን ሁሉም ሰው የቅዱስነታቸውን መልዕክት የማንበብ እና በዓለም አቀፋዊት ቤተ ክርስቲያን ውስጥ የሚከናወኑ ቁልፍ ዕድገቶችን በየራሳቸው ቋንቋ ለመከታተል ዕድል ይኖራቸዋል” ሲሉ አስገንዝበዋል። ይህ ተነሳሽነት ለብዙ አማኝ ላልሆኑ እና የሌላ እምነት ተከታዮች ለሆኑት ጠቃሚ ግብዓት እንደሚሆን ያላቸውን እርግጠኝነት ገልጸው፥ በተጨማሪም አዘርባጃኒኛ ቋንቋ በአዘርባጃን ብቻ ሳይሆን በዓለም ዙሪያ ወደ 30 ሚሊዮን በሚጠጉ ሰዎች ዘንድ እንደሚነገር ጠቁመዋል።
የቫቲካን ዜና አገልግሎት ለሁሉም አድማጮች በመንፈሳዊ እና በዕለት ተዕለት ሕይወታቸው ውስጥ ትርጉም ያለው እና አስተማማኝ አጋር እንዲሆንላቸው በማሰብ፥ ፕሮጄክቱን እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን እንድትጠብቀው” በማለት መልዕክታቸውን አጠቃለዋል።
የግንኙነት መረቦችን ማጠናከር
ከቫቲካን መገናኛዎች ዳይሬክተር ዶ/ር ፓኦሎ ሩፊኒ፥ “እያንዳንዱ ጨርቅ የተሠራው ስፍር ቁጥር በሌላቸው የተጠላለፉ ክሮች ነው፤ የእኛ የመገናኛ አውታርም እንዲሁ ነው” ብለው፥ ለብጹዕ አቡነ ቭላዲሚር እና የአዘርባጃን ሐዋርያዊ አስተዳደር ትብብር ምስጋናቸውን አቅርበው፥ ከዛሬ ጀምሮ ጣቢያችን አዘርባጃንኛን ይናገራል” ብለዋል።
አክለውም፥ በመገንባት ላይ ከሚገኙት የቤተ ክርስቲያን ሕያው መዋቅር ውስጥ ሁሉም ቋንቋዎች ከቀን ወደ ቀን ወሳኝ ሚና እንደሚጫወቱ ገልጸው፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በጥቅምት ወር 2016 ዓ. ም. ባኩን በጎበኙበት ወቅት በአዘርባጃን ውስጥ የሚገኝ ጥቂት ካቶሊካዊ ማኅበረሰብን ማመስገናቸውን እና በላይኛው ክፍል ውስጥ መንፈስ ቅዱስ በላያቸው እንዲወርድ ለመጠባበቅ ከተሰበሰቡት የመጀመሪያዎቹ ደቀ መዛሙርት ጋር ማመሳሰላቸውን አስታውሰዋል።
ዶ/ር ሩፊኒ በመቀጠልም “አዘርባጃንኛን በብዙ የቫቲካን ዜና አገልግሎት ቋንቋዎች ማካተት በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ማንም ሰው ከሌላው የሚበልጥ ወይም የሚያንስ አለመሆኑን የምናሳይበት መንገድ ነው” ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በአንድ ወቅት እንደተናገሩት፥ ኅብረትን በሙላት ለመኖር ሁለት ነገሮች እንደሚያስፈልጉ፥ በላይኛው ክፍል ውስጥ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም እና በጎነት መገኘቱ፥ ሌላው በመንፈስ ቅዱስ አምሳል የፈሰሰው የወንድማዊነት ፍቅር እንደሆነ መናገራቸውን ዶ/ር ፓውሎ ሩፊኒ አስታውሰዋል።
ዛሬም ቢሆን እርስ በርሳችን መነጋገር፣ በፍቅር ቋንቋ መግባባት፣ በጎ ፈቃድ ያለውን ማኅበረሰብ መገንባት እና በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የምንካፈለውን አንድነት ከሁሉ የላቀው የመገናኛ ዘዴያችን ማድረግ፥ እንደ በባቢሎን ግንብ ግራ መጋባት በሚያሰጋው ዓለም ውስጥ ተልዕኮአችን ማድረግ አስፈላጊ ነው” ሲሉ አስገንዝበዋል።
ለውይይት የሚያግዝ የመገናኛ ድልድይ
ከቫቲካን መገናኛዎች ዳይሬክተር ዶ/ር ፓኦሎ ሩፊኒ ንግግር ጎን ለጎን የቫቲካን መገናኛዎች ርዕሠ አንቀጽ አርትዖት ክፍል ሃላፊ አንድሬያ ቶርኔሊ በበኩላቸው፥ “በአዘርባጃን የሚገኘው የቫቲካን ዜና አገልግሎት ዓላማ የቅዱስነታቸውን መልዕክት ለብዙ ሰዎች ማድረስ መንገድ ብቻ ሳይሆን በሃይማኖቶች መካከል ውይይት ለመፍጠር ጠቃሚ እርምጃ ነው” ሲሉ አስረድተዋል። በጦርነትና በዓመፅ በተናወጠ ዓለም ውስጥ የቅዱስ ጴጥሮስ ተተኪ የተናገሯቸውን ቃላት፥ ጥላቻን እና መከፋፈልን በማሸነፍ የእርስ በርስ ግንኙነትን፣ የጋራ መግባባትን እና ወንድማማችነትን ማሳደግ ለሚፈልጉት ሁሉ ድልድይ እንደሚሆንላቸው አስረድተዋል።
የቫቲካን ሬዲዮ ምክትል ዳይሬክተር እና የዜና ክፍል ኃላፊ የሆኑት አቶ ማሲሚላኖ ሜኒኬቲ በበኩላቸው፥ “አዲስ የስርጭት ቋንቋን ማካተት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ወደ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት፣ ወደ ዓለም አቀፋዊት ቤተ ክርስቲያን እና ከቅድስት መንበር የወጡ ዜናዎችን ለማግኘት የሚያስችል ወሳኝ እርምጃ ነው” በማለት አስፈላጊነቱ ላይ አጽንኦት ሰጥተዋል።
“ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ዓለም አቀፍ ግንኙነቶችን ለመገንባት እና አዳዲስ የመረጃ እና የወንጌል ስርጭት አገልግሎትን ለመደገፍ በየአገራቱ ከሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት ጋር ያለንን አጋርነት በማጠናከር ላይ እንገኛለን” ሲሉ ገልጸው፥ “ራዕያችን እውቀትን እና ግብዓቶችን በማጣመር የጋራ አውታረ መረቦችን መፍጠር ነው” ሲሉ አስረድተዋል።
ይህ በአንድ በኩል የተባበረ የግንኙነት መረብ እንደሚፈጥር፥ በሌላ በኩል ደግሞ የየአካባቢዎችን የፈጠራ ችሎታን እንደሚያሳድግ እና በተለያዩ ማኅበረሰቦች ውስጥ ዕድገትን እንደሚያበረታታ አስረድተው፥ ህልማቸው በመላው ዓለም የሚገኙ ካቶሊካዊ ማኅበረሰቦች ሙሉ በሙሉ የተገናኙበትን መድረክ መፍጠር እንደሆነ፣ ይህም ጽሑፎችን፣ ምስሎችን እና የድምጽ መልዕክቶችን ብቻ ሳይሆን የቤተ ክርስቲያኗን የሕይወት ተሞክሮ የትም ሆነው ለማግኘት እንደሚያስችላቸው አስረድተዋል።