“ቤተሰባችን” የኮሮና ቫይረስ ስርጭት በጣሊያን ክፍል 1.
ክቡራት እና ክቡራን የ “ቤተሰባችን” ዝግጅት ተከታታዮቻችን እንደ ምን ሰንብታችኋል። በዛሬው ሳምንታዊ የ “ቤተሰባችን” ዝግጅት በከፍተኛ ፍጥነት ወደ ዓለም ዳርቻ ስለ ተሰራጨው እና በመሰራጨት ላይ ስለሚገኝ የኮሮና ቫይረስ ያገኘነውን መረጃ እናካፍላችኋለን።
የኮሮና ቫይረስ ከቅርብ ወራት ወዲህ በከፍተኛ ፍጥነት ወደ ተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች መሰራጨት ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ እስከ ዛሬ በርካታ ሰዎችን ለሞት እየዳረገ መሆኑን የተለያዩ አገራት መንግሥታት ይፋ በማድረግ ላይ ይገኛሉ። ወረርሽኙ ከቻይና ቀጥሎ ክፉኛ ካጠቋቸው አገሮች መካከል በቅድሚያ የምትጠቀስ አገር ጣሊያን ናት። የኮሮና ቫይረስ ይህን ያህል ጣሊያንን እንዴት ሊያጠቃ ቻለ? በተለይም ደግሞ በሰሜን ጣሊያን የቫይረሱ ስርጭት ለምን ጎልቶ ታየ? የሚሉትን ጥያቄዎች ደ ኒው ዮርክ ታይምስ ያለፈው ቅዳሜ መጋቢት 12/2012 ዓ. ም. በድረ ገጹ ባሠፈረው ዘገባ እንደሚከተለው ይገልጸዋል።
የጣሊያን መንግሥት የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመቆጣጠር ከወሰዳቸው ፈጣን እርምጃዎች መካከል አንዳንዶችን ስንመለከት፣ የመጀመሪያው የኮሮና ቫይረስ ምልክት የታየባቸውን አካባቢዎችን መለየት እና በዚያ አካባቢ በቫይረሱ የመያዝ ምልክት የሚያሳዩት ሰዎችን ወደ ጊዜያዊ ማቆያ ማዕከል ማስገባት፣ ሰዎች ከአንድ ክፍለ ሃገር ወደ ሌላ ክፍለ ሀገር ወይም ከአንድ ከተማ ወደ ሌላ ከተማ የሚያደርጉትን ጉዞ መቆጣጥር የሚሉት የጣሊያን መንግሥት የቫይረሱ ምልክት ለመጀመሪያ ጊዜ በታየበት ወቅት አስቀድሞ የወሰዳቸው እርምጃዎች ናቸው። ቀጥሎም በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የዓለም ጤና ተቋም የቫይረሱን መዛመት ለመቆጣጠር እና ለመቀነስ የሚያግዙ መረጃዎችን ከአገሩ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ጋር በማስተባበር ወደ ዜጎቹ በማዳረስ ላይ ይገኛል።
ያም ሆኖ የቫይረሱ መዛመት በቀላሉ የሚቆም ሆኖ አልተገኘም። በወረርሽኙ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር ከቀን ወደ ቀን በማደግ ላይ ይገኛል። የሟች ቁጥርም እንደዚሁ። ቅዳሜ መጋቢት 12/2012 ዓ. ም. በአንድ ቀን ብቻ በቫይረሱ የሞተው ሰው ቁጥር 793 መድረሱ መላውን ዓለም ማስደንገጡ ይታወሳል። በመሆኑም የጣሊያን መንግሥት ከቀን ወደ ቀን ዜጎቹ ተግባራዊ ሊያደርጉ ይገባል ያሏቸን አዳዲስ ደንቦች ከቀን ወደ ቀን በማጽደቅ ተግባራዊነቱን እየተከታተለ ይገኛል።
የቫይረሱን መዛመት ለመቀነስ ሲባል መሥሪያ ቤቶች እና ድርጅቶች ተዘግተዋል። የትምህርት ተቋማት፣ የስፖርት ማዕከላት፣ የአምልኮ ሥፍራዎች፣ ባጠቃላይ ሰው በብዛት የሚገኙባቸው ቦታዎች እንዲዘጉ ተደርገዋል። ቤተሰብ በመሰባሰብ ጊዜያቸውን እቤት ውስጥ እንዲሳልፉ ታዘዋል። የጣሊያን ሪፓብሊክ መንግሥት ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ጁሰፔ ኮንተ የወረርሽኙን አስከፊነት በማጉላት ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወዲህ አገራቸውን ከባድ ማኅበራዊ ቀውስ ሲያጋጥማት ይህ የመጀመሪያ ነው ብለው መንግሥታቸው የሚችለውን ሁሉ ለማድረግ ዝግጁ ነው በማለት ዜጎችን አጽናንተዋል።
የኮሮና ቫይረስ ዓለምን ለማዳረስ በፍጥነት እየገሰገሰ ባለበት ባሁኑ ጊዜ ጣሊያን ቶሎ ብላ የወሰደቻቸው ቆራጥ እርምጃዎች ለአውሮጳ አገሮች እና ለተቀረውም የዓለማችን ክፍሎች እንደ ጥሩ ምሳሌ እየተጠቀሰ ይገኛል። ጣሊያን የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመግታት ከሁሉ አስቀድሞ የአውራጃ ከተሞቿን ለየች። ቀጥላ የክፍለ ሀገር ከተሞቿን ለየች። ቀጥላም ዜጎቿ ወደ ሌሎች አገሮች እንዳይጓዙ በማለት የጉዞ እቀባ አደረገች። በጣሊያን ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ምክትል ዋና ጸሐፊ የሆኑት ወ/ሮ ሳንድራ ዛምፓ እንደገለጹት ጣሊያን በኮሮና ወረርሽኝ ዙሪያ ያሰባሰበችውን ጠቃሚ መረጃ መሠረት በማድረግ የቫይረሱን ስርጭት ለመቀነስ የምትችለውን ጥረት ሁሉ በማድረግ ላይ መሆኗን ገልጸዋል።
የጣሊያን መንግሥት የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመቆጣጠር የወሰደው ከባድ ውሳኔ እና ቆራጥ እርምጃ፣ የዜጎችን መብት ይጋፋል በማለት ከተቀሩት የአውሮፓ አገሮች ቅሬታ አሳድሯል። ቢሆንም ባለስልጣናቱ ቫይረሱ ዛሬ በምንገኝበት የሰለጠነ ዓለም ይከሰታል ተብሎ የተጠበቀ ባለመሆኑ መንግሥት ከአገሪቱ ሳይንቲስቶች የሚቀርቡ ምክሮችን በመቀበል የዜጎችን ሕይወት ለማትረፍ በፍጥነት መነሳቱን እንደ ቀዳሚ አማራጭ ቆጥሮታል።
የጣሊያን መንግሥት የወሰዳቸው አንዳንድ እርምጃዎች ቀላል አልነበሩም። ዘጎቿን ሥራን እንዲያቆሙ በማዘዝ፣ በሰሜናዊው የአገሪቱ ክፍሎች የሚገኙ በርካታ የማምረቻ ኢንዱስትሪዎች እንዲዘጉ ማድረግ በማሕበራዊ ሕይወት ላይ ከሚያስከትለው አደጋ በተጨማሪ በኤኮኖሚው ላይ የሚያስከትለው ቀውስ ከፍተኛ እንደሆነ መገመት ይቻላል።
ክቡራት እና ክቡራን የ “ቤተሰባችን” ዝግጅት ተከታታዮቻችን በዚህ ጽሑፍ በጣሊያን አገር የርኮሮና ቫይረስ ስርጭትን በማስመልከት ያቀረብነውን ጽሑፍ የመጀመሪያ ክፍል በዚህ አንፈጽማለን። በሚቀጥለው ሳምንት በክፍል ሁለት እስከምንገና ጤናን፣ ሰላምን እና ፍቅርን የምመኝላችሁ የጽሑፉ አዘጋጅ ዮሐንስ መኰንን ነኝ።