ፈልግ

ሙስሊም ወንድሞቻችን እና እህቶቻችን እንኳን ለዒድ አል-አድሀ በዓል በሰላም አደረሳችሁ! ሙስሊም ወንድሞቻችን እና እህቶቻችን እንኳን ለዒድ አል-አድሀ በዓል በሰላም አደረሳችሁ! 

ሙስሊም ወንድሞቻችን እና እህቶቻችን እንኳን ለዒድ አል-አድሀ በዓል በሰላም አደረሳችሁ!

በዓለም ዙሪያ በሚገኙ የእስልምና እምነት በሚከተሉ ምዕመናን ዘንድ 1 ሺህ 441ኛው የዒድ አል-አድሀ በዓል በመከበር ላይ እንደ ሚገኝ ይታወቃል። እኛም በቫቲካን ሬዲዮ የአማርኛው የስርጭት ክፍል  ስም ሆነን ለመላው የእስልምና እምነት ተከታይ ወንድም እህቶቻችን እንኳን 1 ሺህ 441ኛው የዒድ አል-አድሀ በዓል በሰላም አደረሳችሁ ለማለት እንወዳለን። ክርስቲያኖች እና የእስልምና እምነት ተከታዮች በእምነት ደረጃ የተለያየ ሐይማኖት ያለን ብንሆንም ቅሉ ሁላችንም ሰብዓዊ ፍጡር በመሆናችን የተነሳ በአገራችን ኢትዮጲያ በወንድማማችነት፣ በአንድነት፣ በመተጋገዝ፣ በመደጋገፍ እና በመከባበር ላይ የተመሰረተው የሁለቱ እምነት  መልካም ግንኙነት ተጠናክሮ ይቀጥል ዘንድ እያንዳንዳችን የበኩላችንን ኃላፊነት ልንወጣ ይገባል ለማለት እንወዳለን።

የእዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በጥር 26/2011 ዓ.ም  “ሰብዓዊ ወንድማማችነት” በሚል መሪ ቃል በአቡ ዳቢ ተካሂዶ በነበረው የተለያዩ የሐይማኖት ተቋማት መሪዎች ስብስባ ላይ መሳተፋቸው የሚታወስ ሲሆን ቅዱስነታቸው በወቅቱ “በእግዚኣብሔር ላይ እያንዳንዳችን ያለን እምነት ኅበረት እንዲኖረን ያደርጋል እንጂ አይከፋፍለንም” በማለት በወቅቱ መናገራቸው ይታወሳል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በወቅቱ በአቡ ዳቢ በነበራቸው ቆይታ ከተለያዩ የእምነት ተቋማት መሪዎች እና ተወካዮቻቸው ጋር ቆይታ ማድረጋቸው የሚታወስ ሲሆን በተለይም ደግሞ እርሳቸው “ወንድሜ እና ጓደኛዬ” በማለት ከሚጠሩዋቸው የግብፅ ታላቁ የአልዓዛር መስጊድ እና ዩኒቬርሲቲ ኢማም ከሆኑት ሼክ አህመድ አል ጣይብ ጋር መገናኘታቸው እና በዓለም ዙሪያ ሰላም ይሰፍን ዘንድ የሁለቱ ሐይማኖት ተቋማት ተወካዮች ማለትም የክርስትና እና የእስልምና እምነት ተከታይ የሆኑ ምዕመናን በወንድማማችነት መንፈስ በመተጋገዝ እና በመደጋገፍ ይኖሩ ዘንድ የሚያስችላቸው የመግባቢያ የሰላም ሰነድ መፈራረማቸው ይታወሳል።

በወቅቱ “ሰብዓዊ ወንድማማችነት” የሚል አርእስት የተሰጠው የመግባቢያ ሰነድ መፈረሙን መግለጻችን የሚታወስ ሲሆን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራነችስኮስ በወቅቱ ባደረጉት ንግግር እንደ ገለጹት “የግብፅ ታላቁ የአልዓዛር መስጊድ እና ዩኒቬርሲቲ ኢማም ከሆኑት ሼክ አህመድ አል ጣይብ ጋር የተፈራረሙት የሰላም የመግባቢያ ሰንድ “ታሪካዊ” መሆኑን ገልጸው ይህ የሰላም መግባቢያ ሰነድ የተዘጋጀው “ከፍተኛ የሆነ አስተንትኖ እና ጸሎት ከተደረገ” በኋላ እንደ ነበረ የገለጹት ቅዱስነታቸው “ይህ የሰላም መግባቢያ ሰነድ በአሁኑ ወቅት በዓለማችን በከፍተኛ ሁኔታ በመንጸባረቅ ላይ ያሉ አስከፊ የሆኑትን “ጦርነቶች፣ ውድመቶችን እና የእርስ በእርስ ጥላቻን” ለማስወገድ በማሰብ በጥንቃቄ የተዘጋጀ እንደ ሆነ ቅዱስነታቸው ጨምረው ገልጸዋል።

“እኛ አማኝ የሆንን ሰዎች እጅ ለእጅ መጨባበጥ፣ መተቃቀፍ፣ መሳሳም እና አብረን መጸለይ ካልቻልን፣ እምነታችን ተሸናፊ ይሆናል” በማለት ንግግራቸውን የቀጠሉት ቅዱስነታቸው በዚህም መሰረት ይህ እርሳቸው እና የግብፁ ታላቁ የአልዓዛር መስጊድ እና ዩኒቬርሲቲ ኢማም የሆኑት ሼክ አህመድ አል ጣይብ የተፈራረሙት የሰላም የመግባቢያ ሰነድ “የተወለደው የሁሉም አባት ከሆነውና የሰላም አባት ከሆነው በእግዚአብሔር ላይ ካለን እምነት ነው፣ እርሱም በታሪክ ውስጥ የመጀመሪያው የአሸባሪዎች ጥቃት ከሆነው ከቃየን የሽብር ዘመቻ ጀምሮ ያሉትን ውድመቶች እና የአሸባሪዎች ጥቃት ያወግዛል” ማለታቸው ተገልጹዋል።

ይህ በጥር 26/2011 ዓ.ም ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ለመጀመሪያ ጊዜ የእስልምና እምነት መነሻ በሆነው በአረብ ባህረ-ሰላጤ የሚያደርጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት እርሳቸው በክርስትናና በእስልምና እምነት ተከታይ ሕዝቦች መካከል ያለውን የጋራ የሆነ የእምነት እውቀት እና በተጨማሪም በሁለቱ የሐይማኖት ተቋማት መካከል የነበሩ ግንኙነቶች እና ውይይቶች ተጠናክረው ይቀጥሉ ዘንድ፣ ልዩነቶችን ለማጥራት ቁርጠኛ በመሆን፣ እነዚህ ጉዳዮች ተጠናክረው ይቀጥሉ ዘንድ የመሸጋገሪያ ድልድይ የሚገነባ ሐዋርያዊ ጉብኝት ሲሆን የክርስትና እና የእስልምና እምነት ተከታዮች እርስ በእርሳቸው እንዲተማመኑ በማድረግ ወንድማማቾች መሆናቸውን እንዲገነዘቡ የሚረዳ ሐዋርያዊ ጉብኝት ጭምር ነው።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ አብዛኛው ሕዝባቸው የእስልምና እምነት ተከታይ በሆኑ አገራት ውስጥ የሚያደርጓቸው ጉብኝቶች እና ልዩ ልዩ ስብሰባዎች በመላው ዓለም በሚገኙ የእስልምና እምነት ተከታይ በሆኑ ሕዝቦች እና ለመላው ዓለም ሳይቀር የሰባዊ ፍጡር ሊኖረው ስለሚገባው ፍቅር ትምህርት የሰጠ አጋጣሚ ነበር።

በእስልምና እምነት ውስጥ የሚታዩ በጎ ነገሮች

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሆነው ከተመረጡ በኋላ አብዛኛው ሕዛባቸው የእስልምና እምነት ተከታይ በሆኑ አገራት ውስጥ ተገኝተው ሐዋርያዊ ጉብኝት ማድረጋቸው የሚታወስ ሲሆን እ.አ.አ በ2014 ዓ.ም ወደ ቅድስት አገር አድርገውት ከነበረው ሐዋርያዊ ጉዞ በመቀጠል ዮርዳኖስን መጎብኘታቸው የሚታወስ ሲሆን በዚያ ከዮርዳኖስ ንጉሥ አብዱላ ሁለተኛ ጋር ተገናኝተው በነበረበት ወቅት ቅዱስነታቸው “በእስልምና እምነት ውስጥ የሚገኙ መልካም ባሕሪያት እና ስነ-ምግባሮች፣ የተለያየ እምነት ተከታዮች ሰላማዊ አንድነት እንዲመሰርቱ የተሻለ ግንዛቤ የሚፈጥር በመሆኑ የተነሳ ለሙስሊሙ ማህበረሰብ ያላቸውን ጥልቅ አክብሮትና አድናቆት” ገልጸው እንደ ነበረ ይታወሳል። በዚህ አጋጣሚ "በክርስቲያኖችና በሙስሊሞች መካከል ጥሩና ወዳጃዊ ግንኙነት እንዲሰፍን" አስተዋጾ እንደሚያበረክት ተስፋ እንደ ሚያደርጉም መግለጻቸው ይታወሳል።

መከባበር እና መተባበር

እ.አ.አ በመስከረም ወር 2014 ዓ.ም ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ የአልባኒያ ዋና ከተማ የሆነችውን ቲራና በጎበኙበት ወቅት በአገሪቷ "በአልባኒያ ያለው ቱባ ባሕል ለሁሉም የአገሪቷ ሕዝብ እንክብካቤ እና ትኩረት የሚሰጥ መሆኑን በመመልከቴ እና በመገንዘቤ ተደስቻለሁ” በማለት ማናገራቸው የሚታወስ ሲሆን “የተለያየ እምነት በሚከተሉ ሰዎች መካከል ሰላማዊ ትስስር እና ትብብር” እንዳለ መመልከታቸውን በደስታ መግለጻቸው ይታወሳል። በካቶሊክ፣ በኦርቶዶክስና በሙስሊም እምነት ተከታዮች መካከል ያለው የመከባበርና የመተማመን መንፈስ ለአገሪቷ እጅግ የከበረ ሐብት ሲሆን አሁን ከፍተኛ ትኩረት ለሚፈልገው ዓለማችን ደግሞ መልካም የሆነ አብነት እና አስተምህሮ የሚሰጥ ተሞክሮ እንደ ሆነ” መግለጻቸው ይታወሳል።

ለሰላም የሚደረግ የጋራ ጸሎት

እ.አ.አ በታኅሳስ ወር 2014 ዓ.ም ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ የቱርክ ዋና ከተማ በሆነችው በስታንቡል ሐዋርያዊ ጉብኝት ማድረጋቸው የሚታወስ ሲሆን በወቅቱ ቅዱስነታቸው በእዚያ አድርገውት የነበረውን ጉብኝት አጠናቀው ወደ ቫቲካን በመመለስ ላይ በነበሩበት ወቅት በወቅቱ በቱርክ የነበራቸውን ሐዋርያዊ ጉብኝት በተመለከተ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ የሚከተለውን ብለው ነበር “እኔ ወደ ቱርክ የሄድኩት እንደ አገር ጎብኝ ሆኜ ሳይሆን እንደ አንድ መንፈሳዊ ተጓዥ በመሆን ነበር። መስጊድ ለመጎብኘት በሄድኩበት ወቅት በወቅቱ ይህንን መስጊድ ስያስጎበኘኝ የነበረው ሙፍቲ በታላቅ ትህትና በመስጊዱ ውስጥ ያሉትን ነገሮች አስገራሚ በሆነ ሁኔታ ሲገልጹልኝ እና ሲያብራሩልኝ በነበረበት ወቅት በቁርዓን ውስጥ ስለማርያምንና ስለመጥምቁ ዮሐንስን የተጠቀሱትን ጥቅሶች በሚገባ አብራርቶልኝ ነበር። በዚያን ወቅት እኔም በዚያው ስፍራ ሆኜ መጸለይ እንደ ሚገባኝ ተሰማኝ። ሙፍቲውን ‘ትንሽ እንጸልይ ወይ?’ ብዬ ጠየኩት። እርሱም እንዴታ! አዎን ይቻላል! በሚገባ መጸለይ ይችላሉ! ብሎ መለሰልኝ። እኔም ለቱርክ፣ ለሰላም፣ ለሙፍቲው፣ ለሁሉም እና ለእራሴ ጭምር ጸሎት አድርጌ ነበር። እኔም እንዲህ ብዬ ጸልዬ ነበር "ጌታ ሆይ እነዚህ ሁሉ ጦርነቶች ማብቂያ እንዲያገኙ አባክህን አድርግ” ይህ ከልብ የመነጨ ጸሎት ነበር” በማለት መናገራቸው ይታወሳል።

የክርስቲያኖች እና የሙስሊሞች ወንድማማችነት

እ.አ.አ በ2015 ዓ.ም ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስ በመካከለኛው የአፍሪካ ሪፖብሊክ ዋና ከተማ በሆነችው በባንጉዊ ሐዋርያዊ ጉብኝት ማድረጋቸው የሚታወስ ሲሆን በወቅቱ በእዚያው በመካከለኛው የአፍሪካ ሪፖብሊክ በባንጉዊ በክርስትና እና በእስልምና እምነት ተከታይ በሆኑ ሕዝቦች መካከል ግጭት ተነስቶ በርካታ ሰዎች ለዕልፈት፣ ለስቃይ እና ለስደት መዳረጋቸው የሚታወስ ሲሆን በወቅቱ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በአገሪቷ ባደርጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት የሁለቱን እምነት ማለትም የእስልምና እና የክርስትና እምነት ተቋማት መሪዎችን ፊት ለፊት በማገናኘት ግጭቶች ሁሉ በውይይት ይፈቱ ዘንድ፣ ተገናኝቶ በመወያየት ግጭቶችን የመፍታት ባሕል ያዳብሩ ዘንድ ጥሪ ማቅረባቸው ይታወሳል። ቅዱስነታቸው በወቅቱ በመካከለኛው አፍሪካ ሪፖብሊክ በነበራቸው ቆይታ ይህንን ሰላም የማውረድ ጥረታቸውን በመቀጠል በባንጉዊ በሚገኘው መስጊድ ውስጥ ተገኝተው የሚከተለውን ንግግር አድርገው ነበር፡ “እኛ ክርስቲያኖች እና እናንተ የእስልምና እምነት ተከታይ የሆናችሁ ሁላችሁ እኛ ወንድማማቾች ነን። ስለዚህ እራሳችንን እንደዚህ አድርገን በመቁጠር በዚህ አግባብ መኖር ይኖርብናል። በቅርቡ በአገራችሁ የተከሰቱት አሰቃቂ ክስተቶች እና ግጭቶች በሃይማኖት ምክንያት የተከሰቱ ችግሮች እንዳልሆኑ በሚገባ እንገነዘባለን። በአምላክ አምናለሁ የሚል ማነኛውም ሰው የሰላም ሰው መሆን ይኖርበታል። በአገራችሁ ክርስቲያኖች፣ ሙስሊሞች እና ባህላዊ የሆኑ እምነቶችን የሚከተሉ ሕዝቦች ሁሉ ለብዙ አመታት በሰላም አብረው ኖረዋል” በማለት መናገራቸው ይታወሳል።

አምላክ ለሐይማኖት አካራሪዎች እውቅና አይሰጥም

ምንም እንኳን በአገሪቷ የሚገኙ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ምዕመናን ቁጥር 900 ያህል ብቻ የነበረ ቢሆንም እ.አ.አ በ2016 ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በአብዛኛው የእስልምና እምነት ተከታይ የሆኑ ሕዝቦች በሚኖሩባት አዘረበጃን ሐዋርያዊ ጉብኝት ማድረጋቸው ይታወሳል። ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በወቅቱ የአዘረበጃን ዋና ከተማ በሆነችው ባኩ የሚገኘውን መስጊድ ከጎበኙ በኋላ የሚከተለውን ንግግር አድርገው ነበር፡ “የግል ፍላጎቶቻችንን ለማሳከት እና የራስ ወዳድነት ስሜቶቻችንን ለሟሟላት እግዚአብሔርን ልንጠቀመው አንችልም፣ እርሱ ማንኛውንም ዓይነት አክራሪነት፣ መነኛውንም ዓይነት አስገዳጅ ጫናዎችን እና የሐሳብ ቅኝ አገዛዝን እምላክ በፍጹም አይቀበልም። በድጋሚ ይህ ቦታ በጣም ትልቅ የሆነ ትርጉም ያለው ቦታ በመሆኑ የተነሳ በእግዚአብሔር ስም ምንም ዓይነት ግፍ መፈጸም አይገባም! የሚል ድምጽ ያሰማል። የእርሱ ቅዱስ ስም የሚፈልገው እንዲሰገድለት ነው እንጂ በሰዎች ላይ ግፍ እና ጥላችን እንድነዛራ ግን አይፈቅድም” ማለታቸው ይታወሳል።

ግፍ መፈጸም የቅድስናን መንፈስ ያርቃል

እ.አ.አ በሚያዚያ ወር 2017 ዓ.ም ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በግብፅ ሐዋርያዊ ጉብኝት ማደርጋቸው የሚታወስ ሲሆን በወቅቱ የአልዓዛር ታላቁ መስጊድ እና ዮኒቬርሲቲ ታላቁ ኢማም ከሆኑት አህመድ ሙሀመድ ኣል ታይብ ጋር በተገናኙበት ወቅት የሚከተለውን ንግግር አድረገው ነበር “የሃይማኖት ተቋማት መሪዎች እንደመሆናችን መጠን ማነኛውንም ዓይነት ቅድስናን የሚያጎድፉ ብጥብጦችን እና ግጭቶችን፣ የኋጢኣት ሁሉ መንስሄ የሆነውን የራስ ወዳድነት መንፈስን በማውገዝ እውነተኛ የሆኑ የውይይት መድረኮችን መክፈት ይኖርብናል። በሰው ልጆች ክብር እና ሰብአዊ መብት ላይ የተፈጸሙ ጥሰቶችን ለማውገዝ፣ በሐይማኖት ተቋማት ውስጥ ጥላቻዎችን በመፍጠር፣ እነዚህን ጥላቻዎች በሐይማኖትና በእግዚኣብሔር  ስም እውነተኛ እንደሆኑ አስመስሎ ለማቅረብ የሚደርጉትን ጥረቶች በሙሉ ለማጋለጥ እና እነዚህን ጉዳዮች የእውነተኛው አምላክ ፍላጎቶች ሳይሆኑ ነገር ግን የጣዖት አምላክ ፍላጎቶች መሆናቸውን በማሳወቅ፣ የእውነተኛው እግዚኣብሔር ስም ቅዱስ፣ እርሱ የሰላም አምላክ፣ እግዚኣብሔር ሰላም መሆኑን በድፍረት መመስከር ይኖርብናል። ስለዚህ የተቀደሰ ነገር የሚባለው ሰላም ብቻ ነው፣ ስለሆነም በእግዚአብሔር ስም ምንም ዓይነት ግፍ፣ ብጥብጥ፣ ግጭት ሊፈጸም አይችልም፣ ምክንያቱም በእግዚኣብሔር ስም የሚፈጸሙ ግፎች ቅዱሱን የእግዚኣብሔር ስም ያረክሱታልና” በማለት መናገራቸው ይታወሳል።

በሐይማኖት ተቋማት ውስጥ ያሉ ልዩነቶች ይቅርታ የማድረግ ኃይል ናቸው

እ.አ.አ በታኅሳስ ወር 2017 ዓ.ም ከጠቃላይ ሕዝቧ መካከል 88% የሚሆነው ሕዝቧ የቡዳ እመነት ተከታይ የሆነችውን ማያንማር (በርማ) እና ከጠቃላይ ሕዝቧ መካከል 90% የእስልምና እምነት ተከታዮች የሚገኙባትን ባንግላዲሽን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በቅደም ተከተል መጎብኘታቸው የሚታወስ ሲሆን ቅዱስነታቸው በበርማ ዋና ከተማ በያንጎን ከአግሪቷ የምንግሥት ባለስልጣናት እና የሲቪክ ማህበረሰቦች ጋር በተገናኙበት ወቅት የሚከተለውን ብለው ነበር “በሐይማኖት ተቋማት መካከል ያሉ ማነኛቸውም ልዩነቶች የመከፋፈል እና የልዩነት ምንጭ መሆን የለባቸውም፣ ነገር ግን ለአንድነት፣ ለይቅርታ፣ ለመቻቻል እና ለሀገር ግንባታ ጥበባዊ ሚና ሊጫወቱ ይገባል” ማለታቸው ይታወሳል።

የግጭትን ባሕል በውይይት ባሕል መቀየር

ከላይ ለመጥቀስ እንደ ተሞከረው ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በማያን ማር ዋና ከተማ በያንጎን አድርገውት ከነበረው ሐዋርያዊ ጉብኝት በመቀጠል 90 % ሕዝቦቹ የእስልምና እምነት ተከታይ የሆኑ ሕዝቦች በሚኖሩባት በባንግላዲሽ ቅዱስነታቸው ባደርጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት በመዲናዋ በዳካር የሚከተለውን ንግግር አድርገው ነበር “የሐይማኖት ተቋማት መሪዎች በሐይማኖት ስም እና ሽፋን የሚፈጸሙትን ዓመጾች እና ብጥብጦች በአንድ ድምጽ ሲያወግዙ እና የግጭትን ባሕል በውይይት ባሕል ለመቀየር ሲተጉ እነሱ የእነርሱ የተለያዩ ባህሎች ውስጥ በጥልቀት ስሩን ዘርግቶ የሚገኘውን መንፈሳዊነትን ያውጃሉ” በማለት መናገራቸው ይታወሳል።

 

31 July 2020, 10:27