ፈልግ

አጊቱ ኢዶ ጉደታ አጊቱ ኢዶ ጉደታ  

በትሬንትኖ ውስጥ የተገደለችው “የደስተኛ ፍየሎች ንግሥት” ኢትዮጵያዊቷ አጊቱ ኢዶ ጉደታ ማን ናት?

አጊቱ ኢዶ ጉደታ በታኅሳስ 21/2013 ዓ.ም ምሽት ላይ በመኖሪያ ቤቷ ውስጥ መገደሏ ይታወሳል። የአጊቱ ኢዶ ጉደታ ገዳይ እንደ ሆነ በፖሊስ ተጠርጥሮ በቁጥጥር ስር የዋለው ደግሞ ሱለይማን አዳምስ የሚባል በጣሊያን ውስጥ ለተወሰኑ ዓመታት የኖረ፣ የ32 ዓመት እድሜ ያለው ጋናዊ እረኛ ሲሆን አጊቱን በመግደል ወንጀል ተጠርጥሮ በፖሊስ ቁጥጥር ሥር በዋለበት ወቅት በወቅቱ ለፖሊስ በሰጠው ቃል “መዶሻውን አንስቼ መታኋት። ገድያታለሁ እናም ለሰራሁት ክፉ ሥራ ለመሞት ዝግጁ ነኝ” በማለት መናገሩ ተዘግቧል።

የእዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን

የጣሊያን ግዛት አንዷ በሆነችው በመላው ትሬንትኖ ታዋቂ እና የተከበረች የ 43 ዓመቷ ኢትዮጵያዊው ታታሪ የግብርና ሰራተኛ መገደሏ ብዙዎቹን አስደንግጧል። በሞቼኒ ሸለቆ ውስጥ የመሠረተው የ "ሌ ካፕሬ ፌሊቼ” (ደስተኛ ፍየሎች) የፍዬል ማርቢያ ጣቢያ ባለቤት እና መስራች የነበረችው አጊቱ ኢዱ ጉደታ ደፋር እና ጠንካራ ሴት እንደ ነበረች ይነገርላታል።

አጊቱ በታኅሳስ 21/2013 ዓ.ም በመኖርያ ቤቷ ውስጥ በሚገኘው መኝታ ቤቷ ውስጥ ተገድላ ተግኝታላች። እንደ ተለመደው ጥዋት ላይ ከቤት ባለመውጣቷ ግራ የተጋቡ ጎረቤቶቿ ወደ ቤቷ ዝልቀው ሲገቡ አጊቱ ጉደታ ሙታ ተገድላ ያገኟታል። ጉዳዩ እስካሁን ድረስ በመጣራት ላይ የሚገኝ ሲሆን ይህ በመላው ጣሊያን ሁሉንም ያስደነገጠው ክስተት ሕዝቡ በከፍተኛ ትኩረት በመከታተል ላይ ይገኛል።

የታታሪዋ አጊቱ ጉደታ አስክሬን ከጣልያን በክብር ወደ ትውልድ አገሯ ኢትዮጲያ መሸኘቱ የሚታወስ ሲሆን የአጊቱ ጉደታ አስክሬን ከጣሊያን ተነስቶ ወደ አዲስ አበባ ሲገባ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤን እና በም/ከንቲባ ማዕረግ የመንግስት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት አስተባባሪ አቶ ጃንጥራር አባይን ጨምሮ ቤተሰቦቿ እና ሌሎች የመንግስት የስራ ኃላፊዎች ቦሌ አለም አቀፍ አየር ማረፊያ በመገኘት አስክሬኑን መቀበላቸው ይታወሳል፡፡

የታታሪዋ የአጊቱ ጉደታ የሕይወት ታሪክ

በታታሪነቷ እና በዘርፈ ብዙ ተምሳሌትነቷ በመላው ዓለም ታዋቂነትን ያተረፈችው የአጊቱ ጉደታ ሥርዓተ ቀብር ሽኝት ጥር 5/2013 ዓ.ም. በሕይወት እያላች ስታገለግልበት በነበረው ቅዱስ ዮሴፍ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ውስጥ ተከናወኗል።

አጊቱ ኤደኦ ጉደታ ከአባትዋ ከአቶ ኤደኦ ጉደታ እና ከእናትዋ ከወይዘሮ እሌፍነሽ ተካ ታህሳስ 23/1970 ዓ.ም ተወለደች። አዲስ አበባ ተወልዳ ያደገችው አጊቱ፣ አንደኛ እና መለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርትዋን በማሪያም ጽዮን ትምህርት ቤት ተከታትላለች፤ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርትዋን ደግሞ በየካቲት 12 ትምህርት ቤት ተከታትላ በ1987 ዓ.ም. አጠናቅቃለች፡፡ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርትዋን ካጠናቀቀች በኋላ በ1988 ዓ.ም ነጻ የትምህርት እድል አግኝታ ወደ ጣልያን አገር በማቅናት ከትሬንቲኖ ዩኒቨርስቲ በማኅበረሰብ ሳይንስን (Sociology) በዲግሪ ተመረቃለች።

ለአጊቱ የግብርና ስራ የነፍስ ጥሪዋ ነበር። የከተማ ሌጅ ብትሆንም ገጠር ከሚኖረው አያትዋ ጋር የተለየ ቁርኝት ነበራት። ከትሬንቲኖ ዩኒቨርስቲ ከተመረቀች በኋላ ወደ አገርዋ ተመልሳ ዘላቂ የግብርና ሥራዎች ላይ ለመስራት ጥረት አደረገች። አርሶ አደሮችን አደራጀች፤ አሰለጠነች፤ እንዲሁም አርሶ አደሮችን በግብርና ማሽኖች በማገዝ ጥረት አደረገች።

አጊቱም በአገርዋ ለመስራት ያቀደችው ባይሳካም የነፍስ ጥሪዋን ከማሳደድ ግን አላገዳትም። በሰሜናዊ ጣልያን ትሬንቲኖ ግዛት ውስጥ አሌፓይን ገጠራማ አካባቢ ጥቅም ላይ ያሌዋለ የእንሣት እርባታ መሬት በመግዛት 15 አገር በቀሌ ፍየልችን ማርባት ጀመረች። አስር ዓመት ባልሞላ ግዜ ውስጥም የምትደነቅ ሥራ ፈጣሪ ሆነች። በትሬንቲኖ ግዛት ውስጥ ፍየልችን በማርባት፣ በተለይ ደግሞ በአይብ ምርት ሥራ ታዋቂና ተወዳጅ ለመሆን በቅታለች። በተጨማሪም “ሌ ካፕሬ ፌሊቼ” ወይም “the Happy Goats” (ደስተኛ ፍየል) የተባለ ድርጅት በማቋቋም ሰመ ጥር አምራች ሆነች። የበርካታ ዓለም ዓቀፍ ግዙፍ ሚዲያዎችም ዓይንና ጆሮ ሳበች።

በሀገርዋ ኢትዮጵያም የተሻሻሉ ቴክኖሎጂዎችን በማስተዋወቅና በማስፋፋት የአገርዋን አርሶ አደር ሕይወት ለማሻሻል ከኦሮሚያ ህብረት ሥራ ባንክ ጋር እየሠራች ነበር። በጣልያን አገር ስኬታማ የሆነችበትን ጥምር ግብርና በአገርዋ የመድግም ራእይም ነበራት።

አጊቱ በሥራዋ ለስደተኞች የአዲስ ሕይወት ተስፋና ተምሳሌት ከመሆኗ ሌላ ለስደተኞች መብት በመቆምም ትታወቃለች። በዚሁ ዘርፍ ባበረከተችው የተለያዩ አስተዋጽዖዎችም የተለያዩ ሽልማቶች ተበርክተውላታል። የጣልያን ሀገር ሚዲያዎች እና ፖለቲከኞች “የአካባቢ ጥበቃ አርበኛ፣ የጣልያን ማህብረሰብ እና ስደተኞችን ያዋሃደች ብሔራዊ ጀግኒት” ሲሉ አሞካሽተዋት ነበር። አጊቱ ካቶሊካዊ አገልግሎትዋን በማጠናከር በባሌ ሮቤ የሚገኘው የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ሲገነባ ከፍተኛ ገንዘብ ለግሳለች። በተጨማሪም ከትላልቅ ዓለም ዓቀፍ ለጋሾች ጋር በተመባበር እዚያው ባላ ሮቤ ውስጥ ሆስፒታል እያስገነባች ነበር።

የአጊቱ አስከሬን ጥር 04/2013 ዓ.ም. ክብርት ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ በተገኙበተ በአዲስ አበባ አቀባበል ከተደረገለት በኋላ ጥር 5/2013 ዓ.ም. ብፁዕ ካርዲናል ብርሃነየሱስ፣ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች፣ ካህናት፣ ደናግላን፣ የአጊቱ ቤተሰቦች እና ወዳጆች አንዲሁም ምዕመናን በተገኙበት በጴጥሮስ ወጳውሎስ የካቶሊክ መካነ መቃብር በክብር አርፏል።

ፈጣሪ ነፍስዋን በአጸደ ገነት ያኑርልን። ለቤተሰቦችዋ እና ለዘመድ አዝማድ እንዲሁም ለወዳጆችዋ መጽናናትን እንመኛለን።

Photogallery

አጊቱ ኢዶ ጉደታ
14 January 2021, 11:07