ፈልግ

ወይዘሮ ላቲፋ ቤን ዛያቲን እና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ አቶ አንቶኒዮ ጉተሬዝ ወይዘሮ ላቲፋ ቤን ዛያቲን እና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ አቶ አንቶኒዮ ጉተሬዝ 

እ.አ.አ የ2021ዓ.ም ለሰብዓዊ ወንድማማችነት ቀን የሚበረከተው የዛይድ ሽልማት አሸናፊዎች ይፋ ሆኑ!

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባሄ በዓለም አቀፍ ደረጃ በእየ አመቱ  ጥር 27 ቀን ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ ወንድማማችነት ቀን ሆኖ እንዲከበር መወሰኑን ተከትሎ ጥር 27/2013 ዓ.ም ላይ የመጀመሪያው ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ ወንድማማችነት ቀን ስብሰባ በበይነ መረብ አማካይነት እንደ ሚካሄድ ተገልጿል፣ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በእዚህ ስብሰባ ላይ እንደ ሚገኙም ተገልጿል። በእዚህ ስብሰባ ላይ የግብፁ አል-አዝሃር ታላቁ ኢማም አህመድ አህመድ-ታይየብ እንደ ሚካፈሉም ተዘግቧል። ዝግጅቱ ሼክ መሀመድ ቢን ዛይድ በተገኙበት በአቡ ዳቢ እንደ ሚሰተናገድም ተገልጿል።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ፀሀፊ አቶ አንቶኒዮ ጉተሬዝ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ይህንን አለም አቀፍ የሰብዓዊ ወንድማማችነት ቀን ከማወጁ በፊት እንደ ገለጹት ለሰው ልጆች ሁሉ አገልግሎት መስጠት አስፈላጊነት በመግለጽ ሁለቱ የእመት ተቋማት ማለትም የክርስትና እና የእስልምና እምነት ተቋማት በእዚህ ረገድ እያደረጉት የሚገኘውን መልካም ተግባር እና ተነሳሽነት እንደ ሚያደንቁ መግለጻቸው ይታወሳል። የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጥላቻ ንግግር እና የዘር ማጥፋት ዘመቻን ለመከላከል ይቻል ዘንድ ድርጅቱ በእዚህ አውድ የታቀዱትን ተግባራት ለመከታተል እና ከግብ ለማደርስ ይቻል ዘንድ በማሰብ ከእዚህ ኮሚቴ ጋር በመተባበር እንደ የሚሰራ  በተባበሩት መንግስታት ድርጅ ልዩ አማካሪ እና ጸሐፊ አድርገው አቶ አዳም ዳንግ የተባሉትን ግለሰብ ለእዚህ ጉዳይ መሾማቸውን ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ ጨምረው መግለጻቸው ይታወሳል።

በጥር 27/2013 ዓ.ም የመጀመሪያው የሰብዓዊ ወንድማማችነት ቀን በሚከበርበት ወቅት በዓለም ዙሪያ የሰብዓዊ ወንድማማችነት መንፈስ እንዲስፋፋ  ከፍተኛ አስተዋጾ ያደረጉ ሰዎች ለሁለተኛ ጊዜ “የዛይድ ሽልማት” በመባል የተሰየመውን ሽልማት እንደ ሚሸለሙ ከስፍራው የደረሰን ዘጋባ ያስረዳል። እ.አ.አ የ 2021 ዓ.ም የዛይድ የሰብዓዊ ወንድማማችነት ሽልማት አሸናፊ ሆነው የተመረጡት ሁለት ሰዎች በጥር 26/2013 ዓ.ም ያፋ መሆናቸው የተገለጸ ሲሆን ኢማድ በመባል የሚታወቀው የወጣቶች እና የሰላም ማህበር መስራች የሆኑት ላቲፋ ቤን ዛያቲን የተባሉ ሞሮኮአዊ እና ዘጠነኛው የተባበሩት መንግስታት ድርጅ ዋና ጸሀፊ የሆኑት አቶ አንቶኒዮ ጉተሬዝ መሆናቸው ተገልጿል። ወይዘሮ ላቲፋ ቤን ዛያቲን ልጃቸውን በሽብር ጥቃት ካጡ በኋላ በተሰማቸው ከፍተኛ የሆነ ሐዘን ውስጥ ገብተው የነበሩ ሲሆን ነገር ግን ይህንን ሐዘናቸው አንዳይደገም በማሰብ ወጣቶችን በማስተባበር ወጣቶች የሰላም መሳሪያ ይሆኑ ዘንድ በማሰብ የወጣቶች እና የሰላም ማሕበር በማቋቋም ውጤታማ ሥራ በማከናወን ላይ እንደ በመገኘታቸው የተነሳ ይህ ሽልማት እንደ ተበረከተላቸው ተገልጿል።

የሽልማቱ ተቀባዮች ረቡዕ ጥር 26/2013 ዓ.ም ይፋ መሆናቸው የተገለጸ ሲሆን እነዚህ አሸናፊዎች በገለልተኛ ዳኞች ተመርጠው የመጡ ሲሆን በመንግስት ፣ በባህል እና በሃይማኖት ጉዳዮች መሪዎች የተሰየሙ ከ30 ሀገራት የተውጣጡ ሰዎች በውድድሩ ላይ መሳተፋቸው ተገልጿል።

ስለ ተሸላሚዎቹ

እ.አ.አ የ2021 ዓ.ም የዛይድ የሰብዓዊ ወንድማማችነት ሽልማት አሸናፊ የሆኑትን ተወዳዳሪዎችን ያቀረቡት የሰብዓዊ ወንድማማችነት ማሕበር ከፍተኛ ኮሚቴ የሆኑት ዋና ፀሃፊ የሕግ ባልሙያው ሞሃመድ አብደል ሰላም እንደ ሆኑ የተገለጸ ሲሆን እርሳቸውም ይህንን ሽልማት በተመለከተ በበኩላቸው እንደ ተናገሩት “ይህ ገለልተኛ አለም አቀፍ ሽልማት ሁላችንም የድርሻችንን እንድንወጣ የሚያበረታቱንን ሰዎች ለማበረታታት እና እውቅና ለመስጠት ታስቦ የተሰጠ ሽልማት ነው። የበለጠ ግንዛቤ ፣ ሁሉን አቀፍ እና ሰላማዊ ዓለም ለመፍጠር የእኛ ድርሻ ምን መሆን እንዳለበት አውቀናል። ሁሉቱም የ2021 ዓ.ም ተሸላሚዎች ሥራ እና ተጽዕኖ በመመርመር ለመጪው ትውልድ ፣ ለዓለም መሪዎችና በተመሳሳይ ሁኔታ መልካም እና በክብር የተሞላ የሰላም ጥረት ውስጥ ለሚሳተፉ ሁሉ አርአያ መሆናቸው ግልጽ ነው” ማለታቸው ተገልጿል።

ታላቁ ኢማም እና ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ የሰብዓዊ ወንድማማችነት ሰነድ ይፋ ባደረጉበት ወቅት ታላቅ የሆነ አክብሮ የተሰጣቸው ሲሆን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ የሆኑት አቶ አንቶኒዮ ጉተሬዝ እና ወይዘሮ ላቲፋን ሁእለተኛው የዛይዲ ሽለማት ተሸላሚዎች መሆናቸው ደግሞ ይህ ሰብዓዊ ወንድማማችነት በአለም ዙሪያ ተጠናክሮ እንዲቀጥል የራሱ የሆነ አስተዋጾ እንደ ሚኖረው ተገልጿል።

ፖርቹጋላዊው ፖለቲከኛ አቶ አንቶኒዮ ጉተሬዝ የተባበሩት መንግስታት ዘጠነኛ ዋና ፀሀፊ ሆነው እያገለገሉ እንደ ሚገኙ ይታወቃል። መላው ዓለም ከባለፈው አመት ጀምሮ በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በተጠቃበት ወቅት አቶ አንቶኒዮ ጉተሬዝ በተለያዩ አጋጣሚዎች ድምጻቸውን ከፍ አድርገው “በሁሉም የዓለም ማዕዘናት ውስጥ እየተካሄዱ የነበሩ ጦርነቶች እንዲቆሙ የተጀመረው የተኩስ አቁም ስምምነት የኮርና ቫይረስ ወረርሽኝን ለመመከት አስተዋጾ አለው” ብለው አበክረው በመናገራቸው የተነሳ በተለያዩ አከባቢዎች እየተደርጉ የሚገኙት ጦርነቶች እንዲያበቁ የራሳቸውን ጥረት በማደረጋቸው የተነሳ የተበረከተላቸው ሽልማት እደ ሆነ ተገልጿል። ሽልማቱን አስመልክቶ አቶ አንቶኒዮ ጉተሬዝ ሲናገሩ “ለሰብአዊ ወንድማማችነት የዛይድ ሽልማት ተሸላሚ በመሆኔ ክብር እንደተሰማኝ በትህትና ጥልቅ የሆነ ምስጋናዬን ማቅረብ እፈለጋለሁ። ሰላምን እና ሰብአዊ ክብርን ለማሳደግ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በየቀኑ ፣ በየትኛውም ቦታ እያከናወነ ላለው ስራም እውቅና እንደ ሆነ እመለከተዋለሁ” ብለዋል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ የሆኑት አቶ አንቶኒዮ ጉተሬዝ የዛይዲ ሽልማት አሸናፊ መሆናቸው ከተነገራቸው በኋላ በትዊተር ገፃቸው ላይ እንዳስታወቁት “ለሰብዓዊ ወንድማማችነት ማሕበር ከፍተኛ ኮሚቴ ለዚህ እውቅና ስለሰጠኝ ምስጋናዬን አቀርባለሁ፣ በተለይም ደግሞ በሐይማኖት ተቋማት መካከል ውይይት እንዲደረግ በከፍተኛ ሁኔታ በመስራት ላይ የሚገኙት ወይዘሮ ላቲፋ ቤን ዛያቲን ጋር በጋራ ይህንን ሽለማት በመሸለሜ እጅግ ደስ ብሎኛል። ሰላምን እና የሰውን ልጅ ክብር ለማጎልበት በየቀኑ የሚሰሩ የስራ ባልደረቦቼ ..... በጣም ተጋላጭ ለሆኑት ሰዎችን ለማገዝ እና ለመደገፍ ከዚህ ሽልማት ጋር የተጎዳኘ የገንዘብ ሽልማት ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስደተኞች መርጃ ኤጄንሲ እለግሳለሁ፣ ይህንንም በማደረጌ ኩራት ይሰማኛል” ብለዋል።

የኢማድ የወጣቶች እና የሰላም ማህበር መስራች የሆኑት ወይዘሮ ላቲፋ ቤን ዛያቲን የሞሮኮ ተወላጅ መሆናቸው የተገለጸ ሲሆን  የአምስት ልጆች እናት ናቸው።  እ.ኤ.አ. በ 1977 ዓ.ም በአሥራ ሰባት ዓመታቸው ወደ ፈረንሳይ አገር በመሄድ በእዚያው መኖር ጀመሩ። ከልጆቿ መካከል ኢማድ በመባል የሚታወቀው አንድ ወንድ ልጇ የፈረንሳይን የጦር ኃይል በመቀላቀል ወታደር ሆነ። ይህ ኢማድ በመባል የሚታወቀው ልጇ በፈረንሳይ አገር በቱሉዝ አቅራቢያ እ.አ.አ በ2012 ዓ.ም ተገደለ። ከእዚያም በኋላ የልጇ ገዳይ መሃመድ መራህን የተባለ ሰው እንደ ሆነ የተረዱት ወይዘሮ ላቲፋ ቤን ዛያቲን ይህ የልጇ ገዳይ ይህንን ግድያ ለመፈጸም ያነሳሳው ምን እንደሆነ ለመረዳት ፈለጉ። በእዚህን ጊዜ ብዙ ወጣቶች ብቻቸውን የሆኑ እና በአጠቃላይ ህብረተሰቡን ለመቀላቀል የሚያስችላቸው ስነልቦና ማዳበር ባለመቻላቸው የተነሳ ብዙ ተመሳሳይ ጥፋት ሊከተል እንደ ሚችል ተረዱ። ወይዘሮ ላቲፋ የኢማድን የወጣቶች እና የሰላም ማህበር ከመሰረቱበት እለት ጀምሮ ታሪካቸውን ለወጣቶች ለማጋራት ከወጣቶች ጋር ለመገናኘት በመላው ፈረንሳይ ተጉዘዋል። ተስፋቸው በቀድሞዎቹ እና በወጣት ትውልዶች መካከል እንዲሁም በፈረንሣይ በተወለዱት እና በስደተኞች መካከል “ማህበራዊ መግባባት” እንዲኖር አስተዋጾ ማድረግ ነው።

ወይዘሮ ላቲፋ ቤን ዛያቲን የዛይዲ ሽልማት አሸናፊ መሆናቸውን የሚገልጽ ዜና ሲደርሳቸው “እኔ እና ሌሎች ብዙዎች በየቀኑ ለምንሰራው ስራ ፣ እኔ ምንም እንኳን ፅንፈኝነትን በመፍታት ረገድ በወጣቶች መካከል ውይይት እንዲደረግ በርትተን በመሥራታችን የሰብዓዊ ወንድማማችነት ለዛይድ ሽልማት በመብቃታችን፣ እንዲሁም ለምንሰራው ስራ እውቅና በማግኘታችን ትልቅ ክብር ይሰማኛል፣ በእርግጥ በትሕትና ተቀብያለሁ። ውይይት ፣ የጋራ መከባበር እና በሰላም አብሮ መኖር በጣም አስፈላጊ ነገሮች ሲሆኑ ይህ ሽልማት እነዚህን ጥረቶች ማስቀጠል አስፈላጊ ስለመሆኑ በታዳሚዎች ዘንድ በሰፊው ግንዛቤን ለማሳደግ ይረዳል የሚል ተስፋ አለኝ” ብለዋል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮም ሆኑ ታላቁ የአል-አዝሃር ኢማም በበይነ መረብ አማካይነት በሚሳተፉበት ሥነ ሥርዓት ላይ ሽልማቱ እንደ ሚበረከት ተግልጿል።

ስለ ሽልማቱ

የዛይድ ሽልማት ለሰብዓዊ ወንድማማችነት አስተዋጾ ላደረጉ ሰዎች የሚበረከት ሲሆን እ.አ.አ በየካቲት 04/2019 ዓ.ም ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ እና ታላቁ የአል-አዝሃር ኢማም የሆኑት አልጣይብ ሰብዓዊ ወንድማማችነትን በተመለከተ በጋራ ያሰናዱት ሰነድ ላይ ፊርማቸውን ባስፈሩበት ወቅት ሁለቱም የመጀሪያው የዛይዲ ሽልማት ተቀባዮች እነርሱ እንደ ነበሩም ይታወሳል።

በኋላ ላይ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በበርማ ወይም በማያንማር ለሚኖሩ የሮሂንጋያ ስደተኞች የተበረከተላቸውን ሽላማት ሙሉ መጠን መለገሳቸው የሚታወስ ሲሆን በሰብዓዊ ወንድማማችነት ላይ ያተኮረው ሰነድ የተፈረመበት የመጀመሪያ አመት የምስረታ በዓል ላይ ሼክ አብዱላሂ ቢን ዛይድ አል ናህያን የዛይድ ሽልማት ለሰብዓዊ ወንድማማችነት ዓመታዊ ዝግጅት እንደሚሆን ማስታወቃቸው ይታወሳል።

ሽልማቱ የተከፋፈሉ ሕዝቦችን የሚያስተሳስሩ ድልድዮችን ለሚገነቡት ሁሉ እውቅና ይሰጣል ፣ ይህም ለሁሉም ነፃነትና ደህንነት የማረጋገጥ ሥራን እና እውነተኛ ሰብዓዊ ግንኙነቶች ያጠናክራል። በተጨማሪም የዛይድ ሽልማት የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ መሥራች የሆኑት ሼክ ዛይድ በሰላም አብሮ የመኖር እሴቶችን የሚዘክር ሽልማት እንደሆነም ተገልጿል።

ሽልማቱ በዓለም አቀፍ ደረጃ ሰላምን ፣ ስምምነትን እና የባህል ውይይትን ለማሳደግ የአገራት እና የሃይማኖት መሪዎች እያበረከቱ ለሚገኙት ጥረት እውቅና ለመስጠት የተባበሩት መንግስታት ጠቅላላ ጉባሄ ያወጀው ዓለም አቀፍ የሰብዓዊነት ቀን አካል ነው።

04 February 2021, 13:04