የአባይ ወንዝ ውሃ አጠቃቀም ለኢትዮጵያ፣ ለግብጽ እና ለሱዳን አለመግባባት ምክንያት መሆኑ ተገለጸ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
ኢትዮጵያ ሕዝቦቿን ከጨለማ ለማውጣት እና ምጣኔ ሃብቷን ለማሳደግ በሚል ዓላማ፣ በአፍሪካ ውስጥ ግዙፉን የሕዳሴ ግድብ ግንባታ በ2003 ዓ. ም መጀመሯ ይታወሳል። ከኢትዮጵያ ዋና ከተማ አዲስ አበባ 700 ኪሎ ሜትር ያህል ርቀት፣ በሰሜን ምዕራብ የአገሪቱ ክፍል የሚገኝ ታላቁ የሕዳሴ ግድብ ጉባ በተባለ አካባቢ እየተገነባ መሆኑ ይታወቃል። ግድቡ የሚይዘው የውሃ መጠን 74 ቢሊየን ሜትር ኪዩብ እንደሚሆን እና የሚተኛበት የመሬት ስፋት 1,875 ካሬ ኪሎ ሜትር እንደሚደርስም ተገልጿል።
የኢትዮጵያ እይታ
የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ፣ እሁድ የካቲት 13/2014 ዓ. ም የታላቁ ሕዳሴ ግድብ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት ለመጀመሪያ ጊዜ ባስጀመሩበት ዕለት ባደረጉት ንግግር፥ የኃይል ማመንጫው ሀገሪቱ በጀመረችበት የኢኮኖሚ ልማት ጉዞን በማፋጠን እና እ. አ. አ በ2025 ከካርቦን ልቀት ነፃ ለመሆን ለታቀደው ዘላቂ ግብ ድጋፍ እንደሚሆን እንዲሁም ከታዳሽ ምንጮች ከፍተኛ የኃይል ምርት ሊያስገኝ እንደሚያስችል አስረድተዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ አክለውም፣ የግድቡ ሥራ ሙሉ በሙሉ ሲጠናቀቅ ለክልሉ አገሮች እውነተኛ የኃይል ማዕከል እንደሚሆ ገልጸው፣ ሀገሪቱ ንፁህ እና ታዳሽ ሃይልን በማመንጨት ወደ ውጭ አገራት በመላክ በዓመት ከ2 ሚሊየን ቶን በላይ የካርቦን ልቀትን ማስቀረት እንደምትችል አስረድተዋል።
በጣሊያን ውስጥ በሚገኝ ሳሌንቶ ዩኒቨርሲቲ የዓለም አቀፍ ግንኙነት ታሪክ ፕሮፌሰር የሆኑት መምህር ዳንኤል ዴ ሉካ ለቫቲካን የዜና አገልግሎት ባካፈሉት አስተያየታቸው፣ ያለፈውን ታሪክ ስንመለከት የአባይ ወንዝ የሚጫወተው መሠረታዊ ሚና እንዳለ ገልጸዋል። ወንዞች ለሥልጣኔ ዕድገት ምን ጊዜም መሠረታዊ መሆናቸውን የገለጹት መምህር ዳንኤል፣ የአባይ ወንዝ አስፈላጊነት ደግሞ በጂኦፖለቲካዊ ደረጃም ቢሆን ምሳሌያዊ ነው በማለት አፅንኦት ሰጥተው፣ ውሃ ሁል ጊዜ ከኃይል ምንጭነት አንፃር ወሳኝ መሆኑን አስረድተዋል። በዚህ አኳያ የአባይ ወንዝ ግድብ የመሰለ ግዙፍ ግድብ በአገሮች መካከል ያለውን ግንኙነት የበለጠ ሊያጠናክር አለበለዚያም ግንኙነትን ሊያሽእክር ይችላል በማለት ገልጸዋል። ኢትዮጵያ የግድቡን ግንባታ ከጀመረችበት ጊዜ አንስቶ የግንባታውን ሂደት ከጊዜ ወደ ጊዜ በማሳደግ እስከ ውሃ ሙሌት እቅዷን ተግባራዊ ማድረግ እስከ ጀመረችበት የአውሮፓውያኑ 2020 ዓ. ም ድረስ የተከታተሉት ፕሮፌሰር ዳንኤል፣ ግድቡ የሚይዘው የውሃ መጠን ብዙ እንደሆነ ገልጸዋል።
የግብጽ ስጋት
የግብጽ ስጋት “በተፋሰሱ ውስጥ ያለው የውሃ ክምችት ለተወሰኑ ዓመታት የውሃ ሃብቴን ሊጎዳ ይችላል” የሚል እንደሆነ የገለጹት ፕሮፌሰር ዳንኤል፣ “ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የሁለቱ ሀገራት መንግሥታት የአባይ ውሃ አጠቃቀምን በተመለከተ ዓለም አቀፍ መስፈርቶችን አላከበሩም በማለት እርስ በርሳቸው ሲወነጅሉ ቆይተዋል” ብለዋል።
በሱዳን በኩል የሚታዩ ውስብስቦች
እ. ኤ. አ. ከህዳር 2020 ጀምሮ ከሱዳን ጋር ያለው ግንኙነትም በበኩሉ የውሃ አቅርቦቱን የበለጠ እንዲወሳሰብ ማድረጉን የገለጹት ፕሮፌሰር ዳንኤል፣ እ. አ. አ ከጥቅምት ወር 2021 መፈንቅለ መንግስት ከተካሄደባት ጊዜ ጀምሮ ሱዳን በፖለቲካ እና በኢኮኖሚ ችግሮች ውስጥ በምትገኝበት ጊዜ፣ በሰሜን ኢትዮጵያ ትግራይ ክልል የተቀሰቀሰው የእርስ በርስ ግጭት በሺዎች የሚቆጠሩ ተፈናቃዮች ወደ ግዛቷ እንዲሸሹ ማድረጉን እና በሱዳን እና በኢትዮጵያ መካከል ያለውን የግዛት ይገባኛል ጥያቄ ውዝግብንም ጠቅሰዋል
በአገሮቹ መካከል የተደረሰ ስምምነት የለም
ግብፅ ግድቡ ያለ ፈቃድ ሊካሄድ አይችልም ስትል ከሱዳን ጋር የተደረጉ ሁለት ዓለም አቀፍ ስምምነቶችን፣ የመጀመሪያው በቅኝ ግዛት ዘመን እ. አ. አ. በ1929 የተደረገ፣ ሁለተኛው እ. አ. አ በ 1959 ዓ. ም. የተደረገውን ስምምነት በማስረጃነት አቅርባለች። የመጀመሪያው ስምምነት ግብፅ በአባይ ወንዝ የመሠረተ ልማት ግንባታን በተመለከተ ከፍተኛ ስልጣን የሚሰጣት ሲሆን፣ ሁለተኛው ስምምነት ግብፅ 66 በመቶ የሚሆነውን የአባይ ውሃ እንድትወስድ፣ 22 በመቶ የሚሆነው ደግሞ የሱዳን ድርሻ እንዲሆን የሚያደርግ መሆኑ ታውቋል። የኢትዮጵያ መንግሥት ሁለቱም የቅኝ ግዛት ዘመን ስምምነቶች፣ ኢትዮጵያን ሳያካትት የተፈረሙ በመሆናቸው፣ ራሷንም የማልማት መብት አለኝ በማለት ለሁለቱም ስምምነቶች እውቅና አልሰጥም ስትል ምላሽ መስጠቷ ይታወሳል። እ. ኤ. አ. በ2010 የናይል ተፋሰስ አገራት፣ ግብፅ እና ሱዳንን ሳይጨምሩ ከግብፅ ፍላጎት ውጪ ወንዙን የተለያዩ የልማት ሥራዎችን ለማካሄድ ስምምነት ማድረጋቸው ይታወሳል። ከዚህ ባለፈም ኢትዮጵያ የምትገነባው የሕዳሴ ግድብ፣ ግብጻውያን ከሚፈሩት በተቃራኒ ወደ ግብፅ በሚደርስ የውሃ መጠን ላይ ምንም አይነት ተጽዕኖ እንደማይኖረው ኢትዮጵያ ሁሌም ስትገልጽ መቆየቷ ይታወሳል።
ከበስተጀርባው ያሉ ሌሎች ጉዳዮች
ይህን የመሰለ ሁኔታ ሌሎች ድብቅ ግጭቶችን በግዛቶች መካከል እንዲፈጠሩ የሚያደርግ መሆኑን ያስታወሱት ፕሮፌሰር ዳንኤል ዴ ሉካ፣ ሱዳን በለውጥ ሂደት ውስጥ የምትገኝ አገር መሆኗን ገልጸው፣ ቀደም ሲል በሽብርተኝነት ይመድቧት የነበሩ ምዕራባውያን አገራት የነበራቸውን አመለካከት መለወጣቸውን ገልጸዋል። ፕሮፌሰር ዳንኤል ዴ ሉካ በመጨረሻም፣ በውሃ ላይ የሚነሱ ውዝግቦችን የመሳሰሉ ሁኔታዎች በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ብቻ ሊፈቱ እንደማይችሉ ተናግረው፣ በሌላ በኩል በአሁኑ ጊዜ ዓለም አቀፍ ፖለቲካው በዩክሬን ቀውስ ላይ ማትኮሩን ተናግረዋል።