ፈልግ

በክሬሚያ የተመታው የሩሲያ የጦር መርከብ በእሳት ሲጋይ በክሬሚያ የተመታው የሩሲያ የጦር መርከብ በእሳት ሲጋይ  (AFP or licensors)

ሩሲያ የገና በዓል እየተከበረ ባለበት ወቅት የጦር መርከቧ እንደተመታባት አመነች

ሩሲያ በትናንትናው ዕለት ማክሰኞ ማለዳ ላይ በሩሲያ ቁጥጥር ሥር ባለችው ክሬሚያ ግዛት ባለው የጥቁር ባህር ወደብ ላይ በዩክሬን ጦር በደረሰ ጥቃት ከጦር መርከቦቿ አንዱ ተመቶባት ቢያንስ አንድ ሰው መሞቱን አምናለች። በባህረ ሰላጤው ላይ የተቃጣው ጥቃት የደረሰው ዩክሬን በጦርነት መሃል ሆና የመጀመርያውን የገና በዓልን በአዲስ ካላንደር ካከበረች በኋላ እንደሆነም ተገልጿል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

የሩሲያ መከላከያ ሚኒስቴር ማክሰኞ ዕለት እንዳስታወቀው ከዩክሬን የጦር አይሮፕላኖች የተወነጨፉት ሚሳኤሎች ኖቮቸርካስክ ተብሎ የሚጠራውን የጦር መርከቧን እንዳወደሙባት ገልጿል።

ሞስኮ የተመታው የሩሲያው የጦር መርከብ ምን ያህል ጉዳት እንደደረሰበት ባትገልፅም፥ ነገር ግን የተለያዩ ሚዲያዎች ባወጡት ቪዲዮዎች በወደቡ አካባቢ ከፍተኛ የእሳት ቃጠሎ እንዳለ አሳይተዋል።

ቀደም ሲል የዩክሬን አየር ኃይል ኃላፊ የጦር አውሮፕላኖቻቸው መርከቧን እንዳወደሟት ተናግረው እንደነበር እና ምናልባትም ሰው አልባ አውሮፕላኖችን ጨምሮ ጥይት ጭኖ ሊሆን እንደሚችል ገልጸዋል።

ሞስኮ በጥቃቱ የተሳተፉት ሁለቱ የዩክሬን ተዋጊ ጄቶች በፀረ-አይሮፕላን ጥቃት እርምጃ ተወስዶባቸው ወድመዋል ብትልም ነገርግን እስካሁን ከኪየቭ የተሰጠ ማረጋገጫ የለም ተብሏል።

በሩሲያ የተሾሙት የክሬሚያ መሪ ሰርጌይ አክሲዮኖቭ እንደገለጹት ማክሰኞ ዕለት በደረሰው ጥቃት አንድ ሰው ሲገደል በርካቶች ቆስለዋል ብለዋል።

በተጨማሪም ስድስት ህንጻዎች ላይ ጉዳት መድረሱን እና የተወሰኑ ነዋሪዎችም ወደ ጊዜያዊ መጠለያ ጣቢያዎች መወሰዳቸውንም አክለዋል።

በጥቃቱ ምክንያት የተቀሰቀሰውን የእሳት ቃጠሎ በቁጥጥር ስር ለማዋል አካባቢው ተዘግቶ የነበረ ቢሆንም የወደቡ የትራንስፖርት አገልግሎት ወደ መደበኛ አገልግሎቱ ተመልሷል ተብሏል።

ከቅርብ ወራት ወዲህ የዩክሬን ሃይሎች በክሬሚያ ዙሪያ በአብዛኛው በባህር ድሮኖች የሚያደርጉትን ጥቃቶች መጨመራቸውም ተገልጿል።

የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዘለንስኪ እንደተናገሩት እነዚህ ጥቃቶች ዩክሬን በጥቁር ባህር ላይ የነበራትን የባህር ጉዞ ወደነበረበት ለመመለስ እና በሚሊዮን ቶን የሚቆጠሩ የዩክሬን እህል ወደ ውጭ ለመላክ አስችሏቸዋል ብለዋል።

ባለፈው መስከረም ወር ላይ ዩክሬን የክሬሚያ ከተማ በሆነችው ሴቫስቶፖል በሚገኘው የሩሲያ የጥቁር ባህር መርከቦች ዋና መሥሪያ ቤት ላይ ባደረሰችው ጥቃት አንድ ሰው ሲሞት፥ በማግስቱም ተጨማሪ ሚሳኤሎችን በከተማዋ ላይ ማስወንጨፏ ይታወሳል።

ክሬሚያ በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ዘንድ በዩክሬን አካልነት ብትታወቅም በአውሮፓውያኑ 2014 ሩሲያ ተቆጣጥራ ወደ ራሷ ግዛት ጠቅልላታለች።

ዩክሬን የገና በዓልን በአዲስ ቀን አክብራለች

የማክሰኞው ጥቃት የደረሰው ዩክሬን እ.አ.አ. ከ1917 በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ የገናን በዓል በታህሳስ 15 በይፋ ካከበረች በኋላ ነው።

ባለስልጣናት እርምጃውን ሩሲያ የገናን በዓል ለማክበር በምትጠቀመው በጁሊያን ካላንደር መሰረት ታህሳስ 28 ይከበር የነበረው ቀን ወደ ታህሳስ 15 መቀየሩ ብቻ ሳይሆን ጉዳዩን ከዛ በላይ እንደሆነ አድርገው ይመለከቱታል።

ኪየቭ በሀገሪቱ ውስጥ ጉልህ የሆነ የባህል እና የሃይማኖት ለውጥ አካል መሆኑን እና የሞስኮን በጦርነቱ ከተቆጣጠረቻቸው ሃገራት ውስጥ ያላትን ተፅእኖ ለማጥፋት የተደረገ ሙከራ መሆኑን ግልፅ አድርጋለች።

ኪዬቭ የምዕራባዊያኑን ግሪጎሪያን ካላንደር መጠቀም መጀመሯ የአውሮፓ ህብረት አባል ለመሆን እና ወደ አውሮፓ ለመቀላቀል እያደረገች ያለውን ቀጣይ ሙከራ የሚያሳይ ምልክት ተደርጎ ይወሰዳል።

የኪየቭ ነዋሪ የሆነችው ሳሻ ሶሮኔቪች ቀኑን መቀየር ምሳሌያዊ ጠቀሜታ እንዳለው ተናግራለች። “ቀኑን ብቻ ሳይሆን በውስጣችን ያለውን ስሜት የሚቀይር መስሎ ይሰማኛል” ብላለች።
 

27 December 2023, 13:07