የተባበሩት መንግስታት በፍልስጤማውያን ላይ እየደረሰ ባለው የኢሰብአዊነት ድርጊት ማዘኑን ገለጸ
አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ
በዌስት ባንክ የሚፈጸመውን የሰብአዊ መብት ረገጣ የሚያትተው ይህ የተባበሩት መግስታት ያወጣው ዘገባ ፍልስጤማውያን በእስራኤል ኃይሎች እና ሰፋሪዎች በሚደርስባቸው የኃይል ጥቃት የማያቋርጥ ሽብር ውስጥ ይገኛሉ ብሏል።
ሪፖርቱ እንደሚያሳየው የሃማስ ጥቃትን ተከትሎ በነበሩት ሳምንታት ውስጥ፣ ሰፋሪዎቹ በፍልስጤማዊያን ላይ የሚያደርሱት ጥቃቶች መጨመራቸውንም በመግለጽ፥ በአጠቃላይ ከታህሳስ 23/2015 ዓ.ም. እስከ ታህሳስ 17/2016 ዓ.ም. ድረስ ባሉት ጊዜያቶች ውስጥ በእስራኤል ጦር 492 ፍልስጤማውያን መሞታቸውን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አረጋግጧል።
የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ መብት ሃላፊ የሆኑት ቮልከር ቱርክ በዌስት ባንክ ሰፋሪዎች እያደረሱ ያለው ጥቃት በአስቸኳይ እንዲቆም እንዲሁም ሁለቱም ድርጊቱን የሚያነሳሱ እና ወንጀሉን የሚፈጽሙ አጥፊዎች ለህግ እንዲቀርቡ ጠይቀዋል።
ይህ ዓመት በዌስት ባንክ ብዙ ህፃናት የሞቱበት ዓመት ነው
ባለፈው ሐሙስ መገባደጃ ላይ ዩኒሴፍ ለጋዜጠኞች በሰጠው መግለጫ ዘንድሮ በምስራቃዊ ዌስት ባንክ፥ እየሩሳሌምን ጨምሮ ከግጭቱ ጋር በተያያዘ ጥቃት ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ ከፍተኛ የህጻናት ሞት መመዝገቡን ገልጿል።
ባለፉት አስራ ሁለት ሳምንታት ውስጥ ብቻ 83 ህጻናት እንደተገደሉ እና ይህ አሃዝ በ2022 ከተገደሉት ህጻናት ቁጥር በእጥፍ እንደሚበልጥም ተዘግቧል። ይህም ወታደራዊ እና የህግ አስከባሪ አካላት በብዛት ባሉበት ወቅት መሆኑ ድርጊቱን ልዩ ያደርገዋል ተብሏል። በተጨማሪም ዩኒሴፍ ከ576 በላይ ሰዎች መቁሰላቸውንና በርካቶች መታሰራቸውን ዘግቧል።
“ምስራቅ እየሩሳሌምን ጨምሮ በዌስት ባንክ የሚኖሩ ህጻናት ለብዙ ዓመታት አስከፊ ጊዜ ውስጥ የነበሩ ቢሆንም፥ ከመስከረም 26ቱ የሃማስ ዘግናኝ ጥቃት ወዲህ ግን በከፍተኛ ሁኔታ ጨምሯል” ሲል ዘገባው አመልክቷል።
“ከ2023 መጀመሪያ ጀምሮ ከእስራኤል - ሃማስ ግጭት ጋር በተያያዘ 124 ፍልስጤማዊያን ህጻናት እና 6 እስራኤላዊያን ህፃናት ህይወታቸውን አጥተዋል” በማለትም አክሏል ዘገባው።
ዘገባው በመጨረሻም ህጻናትን ከግጭት ጋር ከተያያዙ ጥቃቶች ለመጠበቅ እና በህይወት የመኖር መሰረታዊ መብቶቻቸውን ለማስጠበቅ በዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ህግ መሰረት ሁሉም ወገኖች ያለባቸውን ግዴታ እንዲወጡ ዩኒሴፍ አሳስቧል። “ልጆች ማንም ወይም የትም ይሁኑ የጥቃት ኢላማ መሆን የለባቸውም” ሲል ድርጅቱ ገልጿል።