ፈልግ

የፍልስጤም ሴቶች በቀዝቃዛው የክረምት ቀን ቤታቸው የፈረሰበት ቦታ ላይ የቤት እቃዎችን እያጠቡ የፍልስጤም ሴቶች በቀዝቃዛው የክረምት ቀን ቤታቸው የፈረሰበት ቦታ ላይ የቤት እቃዎችን እያጠቡ  

የክረምቱ የአየር ሁኔታ ፍልስጤማውያን ላይ ተጨማሪ ሰቆቃን እንደሚያመጣ ተነገረ

በአሁኑ ጊዜ በካምፖች እና በድንኳኖች ውስጥ ለሚኖሩ በሺዎች ለሚቆጠሩ ፍልስጤማውያን በክረምቱ ሳቢያ የተነሳው ቀዝቃዛማው የአየር ንብረት ሁኔታዎች እንዲባባሱ አድርጓል ተብሏል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

ድንገት የተከሰተው በጣም ቀዝቃዛማው የአየር ንብረት በካምፖች እና በድንኳኖች ውስጥ የሚኖሩትን በሺዎች የሚቆጠሩ ፍልስጤማውያን ሁኔታ እንዳባባሰው የተነገረ ሲሆን፥ የክረምቱ ቀዝቃዛማው የአየር ንብረት በክልሉ እየጨመረ መምጣቱ እና በሜዲትራኒያን ባህር ውስጥ ያለው የአየር ሁኔታ ባለፉት ጥቂት ቀናት ውስጥ በአስደናቂ ሁኔታ መለወጡ ተነግሯል።

በጋዛ የተከሰተው ከባድ አውሎ ንፋስ ቤታቸውን ጥለው በጊዚያዊ ካምፖች እና በመጠለያ ውስጥ ለሚኖሩ በመቶ ሺዎች ለሚቆጠሩ ፍልስጤማውያን ሌላ መከራ ይዞባቸው መምጣቱ ነው የተገለፀው።

አንድ ከፍተኛ የተባበሩት መንግሥታት ባለሥልጣን የፍልስጤም ግዛት ያለው የጤና አገልግሎት በመውደሙ ምክንያት ተላላፊ በሽታዎች እየተዛመቱ ነው፤ ቀጥሎ ደግሞ “የጤና ቀውስ” ሊከተል ይችላል ሲሉ አስጠንቅቀዋል።

በዚህ ሁሉ ሰቆቃ ውስጥ፥ እስራኤል ባለፉት 24 ሰዓታት ብቻ 250 ጥቃቶችን በማድረግ የቦምብ ድብደባዋን አጠናክራ ቀጥላለች።

ይህንንም አስመልክቶ ሃማስ እንደገለፀው 50 ፍልስጤማውያን ሲቪሎች ተገድለዋል ብሏል። በተመሳሳይ የእስራኤል ጦር ማክሰኞ ዕለት በጋዛ በተደረገ ውጊያ 10 ወታደሮችን ማጣቷ ተዘግቧል። ይህም የምድር ጥቃት ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ወታደሮቿ ላይ በአንድ ቀን የደረሰው ትልቁ የሞት ቁጥር ነው ተብሏል።

የተኩስ አቁም ጥያቄ

በሌላ ዜና፥ ማክሰኞ ዕለት በኒውዮርክ በተደረገ የተባበሩት መንግሥት ጠቅላላ ጉባዔ በፍጥነት ተኩስ አቁም እንዲደረግ ያቀረበው አስገዳጅ ያልሆነው የውሳኔ ሐሳብ በአብላጫ ድምፅ አልፏል።

አልፎም ጠንከር ያለ ንግግር ያሰሙት የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝደንት ጆ ባይደን እስራኤል “ጋዛ ላይ ባደረሰችው ጅምላ የቦምብ ጥቃት ምክንያት” በዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ ዘንድ ያላትን ድጋፍ እያጣች ነው በማለት ያላቸውን አስደንጋጭ ትችት ካቀረቡ በኋላ እስራኤል ይበልጥ የተገለለች እየመሰለች ነው።

ሃማስ የሚቆጣጠረው የጋዛ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር እስራኤል ዘመቻዋን ከጀመረች ጀምሮ እስከ አሁን ከ18,000 በላይ ሰዎች ተገድለዋል ብሏል። በመስከረም ወር መጨረሻ ላይ ሃማስ የእስራኤልን ድንበር በመጣስ ከ 1,200 በላይ ሰዎችን ከገደለ እና ከ 200 በላይ የሚሆኑ ሰዎችን አግቶ ከወሰደ በኋላ እስራኤል በጋዛ ሰርጥ ላይ የቦምብ ጥቃት መጀመሯ ይታወሳል።
 

14 December 2023, 12:54