ፈልግ

በኩትሮ ፣ ካላብሪያ የአደጋው አንደኛ ዓመት ሲከበር በኩትሮ ፣ ካላብሪያ የአደጋው አንደኛ ዓመት ሲከበር 

የጀልባ አደጋው 1ኛ ዓመት አከባበር ስደተኞች የሚያጋጥሟቸውን አሰቃቂ ሁኔታዎች ያሳያል ተባለ

ጣሊያን ውስጥ ደህንነትን እና ጥገኝነት የሚፈልጉ በደቡብ ኢጣሊያ በምትገኘው ኩትሮ የባህር ዳርቻ ላይ ወደ 100 የሚጠጉ ወንዶች፣ ሴቶች እና ህጻናት ስደተኞች በመርከብ አደጋ ሰጥመው ከሞቱ አንድ ዓመት ቢያስቆጥርም፥ ስደተኞች ግን አሁንም የተዘጉ ወደቦች፣ እንግልት እና አደገኛ ሁኔታዎች ይጠብቃቸዋል ተብሏል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

የካቲት 19 ቀን 2015 ዓ.ም. ፥ ሰኞ ማለዳ 10 ሰዓት ላይ፥ ልክ ከአንድ ዓመት በፊት፥ በርካታ ስደተኞችን የያዘች 'የበጋ ፍቅር' የተሰኝችው ጀልባ ከጣሊያን የባህር ዳርቻ 100 ሜትሮች ርቃ በመስጠሟ ወደ 100 የሚጠጉ ወንዶች፣ ሴቶች እና ህጻናት ህይወት ተቀጥፏል። ይሄንን ክስተት ለማስታወስ በደቡባዊ ኢጣሊያ ካላብሪያ ግዛት፣ በኩትሮ የባህር ዳርቻ በጸሎት የታጀበ ሥነ ሥርዓት ተካሂዷል።

የነፍስ አድን ሰራተኞች አደጋው የደረሰበት ቦታ ለመድረስ ለምን አራት ሰአታት እንደፈጀባቸው ለማወቅ አሁንም ምርመራው እንደቀጠለ ቢሆንም፥ ትዕይንቱ አሁንም ድረስ ትላንትና የተከሰተ እስከሚመስል ድረስ በብዙዎች አዕምሮ ውስጥ አለ።

በሥነ ሥርዓቱ ላይ ፖለቲከኞች፣ የቤተክርስቲያን ተወካዮች፣ ከአደጋው የተረፉት እና የሟቾች እና የጠፉ ሰዎች ዘመዶች እንዲሁም በርካታ የከተማው ነዋሪዎች የተሳፉ ሲሆን፥ በአደጋው የሞቱትን ህፃናት ለማስታወስ ሲባል ሰዎች የተለያዩ አሻንጉሊቶች በቦታው አስቀምጠው ነበር።

በኩትሮ ላይ የነበረው ሀዘን በቀላሉ የሚታይ ነው ፤ ነገር ግን ስለ ኩትሮ ብቻ ሳይሆን ወደ ጣሊያን የሚሰደዱትን ስደተኞች ስቃይ የሚያሳይ በርካታ አሳዛኝ ክስተቶችም ነበሩ።

የር.ሊ.ጳጳሳቱ ቅርበት እና መገኘት

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ ብዙ ጊዜ ለቁጥር የሚያታክቱ ስደተኞች የተሻለ ሕይወት ለማግኘት ሲሉ ቤታቸውን ጥለው የተሰደዱበት የሜዲትራኒያን ባህርን ‘መቃብር’ ሲሉ ገልጸውታል።

ከንግግራቸው በተጨማሪ ቅዱስ አባታችን ሐምሌ 6 ቀን 2005 ዓ.ም. የጵጵስና ዘመናቸው የመጀመርያው ጉዟቸው በሆነው ወደ ደቡብ ኢጣሊያ ደሴት ላምፔዱሳ ካደረጉት ጉዞ አንስቶ፣ በተለያዩ ጊዜያት ለስደተኞች ያላቸውን ቅርበት በግል በመልእክቶቻቸው ሲያቀርቡ እንደነበር ይታወቃል።

ብጹእነታቸው በኋላ ላይ በ2008 ዓ.ም. እና በ2013 ዓ.ም. የግሪክ ከተማ በሆነችው ሌስቦስ የሚገኘውን ታዋቂ የስደተኞች ካምፕ ጎብኝተዋል። እንዲሁም በቅርብ ጊዜ ማለትም መከረም 2015 ዓ.ም. ወደ ደቡብ ፈረንሳይ ወደምትገኘው የወደብ ከተማ፣ ማርሴይ ተጉዘዋል።

በማርሴይ በተካሄደው ለአንድ ሳምንት የዘለቀው የሜዲትራኒያን ሃገራት ስብሰባ የመዝጊያ ሥነ ስርዓት ላይ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ ባደረጉት ንግግር ‘ያልተጠበቁ ሰዎችን (ስደተኞችን) በመቀበል፣ ጥበቃ በማድረግ፣ በማስተዋወቅ እና በማዋሃድ በሚደረጉ ተግባራት ላይ ለሚከሰቱ ችግሮች እውቅና የሰጡ ቢሆንም፥ ነገር ግን ዋናው መስፈርት የራስን ሰብዓዊነት ብቻ መጠበቅ ሊሆን አይችልም፥ ይልቁንም የሁሉንም የሰው ልጅ ክብር መጠበቅ አስፈላጊ ነው” ብለዋል።

ብጹእነታቸው ስደተኞችን ለመጠበቅ ለሶስትዮሽ አህጉራዊ ሂደት ያቀረቡት ጥሪ

ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ደጋግመው እንደተናገሩት፣ በሰው ልጆች ላይ እየደረሰ ያለውን ብዝበዛ ለመጋፈጥ፥ “መፍትሔው አለመቀበል ሳይሆን፣ ከትውልድ አገራቸው መንግስት ጋር በመተባበር እንደየአቅማቸው መጠን፣ ሕጋዊና መደበኛ የሆኑ ስደተኞችን በመቀበል ማረጋገጥ ነው” ብለዋል።

ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ “በሜዲትራኒያን ባህር ዙሪያ ሶስት አህጉራትን በሚያካትት፣ በጥበብ በአርቆ አስተዋይነት መመራት ባለበት የውይይት ሂደት” ላይ ያቀረቡት አቤቱታ ምንም ይሁን ምን፥ ጣሊያን ከብዙ የአውሮፓ ጎረቤት ሃገሮች ጋር በመሆን ጀልባዎቹ ወደ ባህር ዳርቻዎች ሲደርሱ ወደ ኋላ የምትመልሳቸው ከሆነ የአደጋው ክስተት እና ሞት ይቀጥላል።

ከአልባኒያ ጋር የተደረገ አከራካሪ ስምምነት

የጣሊያን የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር እንደገለጸው በ 2015 ዓ.ም. ብቻ ከ157,000 በላይ የሚሆኑ ሰዎች በጀላባ ጣሊያን መድረሳቸውን የገለፀ ሲሆን፥ ወደ ጣሊያን ግዛት የሚደርሱት የስደተኞች ጀልባዎች ቁጥር እየጨመረ ቢሄድም፥ ስደተኞቹ ምንም ዓይነት ዋስትና እንደሌላቸው ተነግሯል።

ይልቁንም፣ የጣሊያን መንግሥት ሁልጊዜም እንደሚያደርገው ጥቂት ስደተኞች ብቻ እንዲገቡ የሚፈቅድ ሲሆን፥ በሴኔት ውስጥ ስደተኞችን ወደ አልባኒያ ማዘዋወር የሚያስችል አወዛጋቢ እርምጃ አስተላልፏል።

ጥቅምት 26 ቀን 2015 ዓ.ም. የጣሊያን ጠቅላይ ሚኒስትር ጆርጂያ ሜሎኒ እና የአልባኒያ ጠቅላይ ሚኒስትር ኢዲ ራማ በጀልባ ወደ ጣሊያን የሚደርሱ ስደተኞችን በአልባኒያ ምድር ወደ ሚገኘውና በጣሊያን በሚመራው ማዕከላት ለመላክ ተስማምተዋል።

ወደ አልባኒያ የሚላኩት ስደተኞችም በጣሊያን ወታደራዊ አካላት የተያዙትን እንጂ በመንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች የተያዙትን ሴቶችና ሕፃናትን አይጨምርም ሲል የስምምነቱ አንቀጽ ይዘረዝራል። ከዚያ ስምምነት በኋላ የጣሊያን ሴኔት አወዛጋቢውን ሰነድ 93 ለ 61 በሆነ ድምጽ አሳልፏል።

በአውሮፓ ህብረት ህግ መሰረት ማንኛውም ስደተኛ ወይም ፍልሰተኛ የጥገኝነት ጥያቄው እስኪታይ ድረስ ወዲያውኑ ወደ ሀገር ቤት መመለስ ህገወጥ ድርጊት ነው፤ ሆኖም አልባኒያ ይህንን የአውሮፓ ህብረት ህግ የመከተል ግዴታ የለባትም ተብሏል።

ጥገኝነት ጠያቂዎችን ወደ ሩዋንዳ ለመላክ ዩናይትድ ኪንግደም ያቀረበችውን ሞዴል በመኮረጅ ነው የሚሉት ታዛቢዎች እንደሚናገሩት፥ ማዕከሉ በጣልያን ፈንድ የሚገነባ እና በጣሊያን የመንግስት ሰራተኞች የሚሰራ ሲሆን፥ በወር እስከ 3,000 የሚደርሱ ጥገኝነት ጠያቂዎችን እንደሚያስተናግድ ሲኤንኤን ዘግቧል።

የአምነስቲ ኢንተርናሽናል ዋና የስደተኞች ተመራማሪ የሆኑት ማትዮ ዲ ቤሊስ በመግለጫቸው እንዳብራሩት፥ አልባኒያ የደረሱ ስደተኞች ለ18 ወራት ማዕከሎቹ ውስጥ እንደሚቆዩ እና መውጣት እንደማይችሉ ተናግረዋል።

በማቆያ ማእከላት ውስጥ የሚከሰት ሞት እና ህገ ወጥ የሆነ አያያዝ

በባህር ላይ ከሚደርሰው ሞት እና ስደት በተጨማሪ የተመዘገቡ እና የታሰሩ ሰዎች የሚከፍሉት ዋጋ በየጊዜው እየጨመረ መሆኑ ዘገባዎች ያሳያሉ።

ጥር 27 በሮም አቅራቢያ በሚገኝ ማዕከል በተፈጠረው አለመረጋጋት 15 ሰዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸው እና የ21 ዓመት ጊኒያዊ ወጣት ህይወቱን በማጥፋቱ፥ በጣሊያን ማቆያ ማእከላት ውስጥ ያሉ ችግሮች ይፋ ወጥተዋል።

ከዓመቱ መጀመሪያ ጀምሮ ከቱኒዚያ በበለጠ ሁኔታ ስደተኞች ከሊቢያ እየመጡ በመሆናቸው ጣሊያን ጠንካራ አቋም መያዟን ቀጥላለች።

መሃል ላይ ማስቀረት፣ ሞት፣ መጥፋት

ከእነዚህ ስደተኞች በተጨማሪ የዓለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት (አይ ኦ ኤም) እንደዘገበው ከዓመቱ መጀመሪያ ጀምሮ 1,000 የሚጠጉ ተጨማሪ ስደተኞች በባህር ላይ ተይዘው ወደ ሊቢያ ግዛት ተወስደዋል። በሌላ በኩል በቱኒዚያ ባለስልጣናት የሚከናወኑ ስደተኞቹን የመጥለፍ እርምጃዎች መረጃ እስካሁን አልተገኘም።

አይ ኦ ኤም በጥር ወር መገባደጃ ላይ በማዕከላዊ እና ምስራቃዊ ሜዲትራኒያን ውስጥ ወደ 100 የሚጠጉ ሰዎች ሞተዋል ወይም ጠፍተዋል ሲል ገልጿል።

ሌላው አቢይ ጉዳይ የነፍስ አድን ጀልባዎች ብዙውን ጊዜ የማይኖሩ ወይም ወደ አስፈላጊው ቦታ መቅረብ ባለመቻላቸው፣ በዚህ መንገድ ስደተኞች ብዙ ጊዜ እንዲቆዩ ይደረጋል።

አስከፊው ሁኔታ እና አመለካከቱ ምንም ይሁን ምን፥ ብዙ ድርጅቶች ሁሌም በመከራ ውስጥ ያሉትን ለመርዳት፣ በሁሉም ሁኔታዎች፣ በጨለማ ውስጥ የብርሃን ፍንጭ በመስጠት፣ ሁሉም ነገር የጨለመ በሚመስልበት ጊዜ የማይቋረጥ ተግባራቸውን በቁርጠኝነት ቀጥለዋል።

ብፁእ አባታችን ለስደተኞች “እንኳን ደህና መጣችሁ”፣ “ጥበቃ”፣ “አስተዋውቁ” እና “አዋህዱ” የሚሉ ለስደተኞች የሚያደርጉት ተደጋጋሚ የአራት ቃላቶች ጥሪ፥ ሃይማኖታዊ ግንኙነት በሌላቸው በብዙ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች፥ ለስደተኞቹ የወደፊት ህይወት ለመስጠት እንደ መጠቀሚያ ዘዴ ተወስደዋል።
 

27 February 2024, 17:33