ፈልግ

የሄይቲ ጠቅላይ ሚኒስትር አሪኤል ሄንሪ ሥልጣናቸውን ለቀቁ የሄይቲ ጠቅላይ ሚኒስትር አሪኤል ሄንሪ ሥልጣናቸውን ለቀቁ  (ANSA)

የሄይቲ ጠቅላይ ሚኒስትር ከስልጣን መልቀቃቸውን አስታወቁ

የካቶሊክ ቤተክርስትያን የካሪቢያን ሀገር በሆነቿ ሄይቲ ታጣቂ ቡድኖች በሃይማኖታዊ ተቋማት ላይ እያደረሱት ያለውን ጥቃት አጥብቃ እየተሟገተች ባለበት ወቅት፥ ጠቅላይ ሚኒስትር ኤሪኤል ሄንሪ ስልጣን መልቀቃቸውን አስታውቀዋል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

የሄይቲ ጠቅላይ ሚኒስትር አሪኤል ሄንሪ ሰኞ ዕለት አመሻሽ ላይ ከፖርቶ ሪኮ በይፋዊ የቪዲዮ አድራሻ ስልጣን መልቀቃቸውን አስታውቀዋል።

ለሳምንታት የዘለቀውን ከፍተኛ ጫና እና በአገሪቱ እየጨመረ ያለውን የከፋ ነውጥ ተከትሎ የሄይቲ ጠቅላይ ሚኒስትር ኤሪየል ሄንሪ ከስልጣን ለመልቀቅ መስማማታቸውን አስታውቀዋል።

የቀጣናው መሪዎች በሄይቲ የፖለቲካ ሽግግር ላይ ለመምከር ሰኞ ዕለት በጃማይካ መገናኘታቸውንም ተከትሎ ነው የጠቅላይ ሚኒስትሩ ከስልጣን ለመልቀቅ መስማማታቸው የተነገረው።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአሁኑ ወቅት በታጠቁ ቡድኖች ወደ አገራቸው እንዳይመለሱ በመከልከላቸው በፖርቶ ሪኮ ውስጥ እንደሚገኙም ለማወቅ ተችሏል።

በጃማይካ መዲና ኪንግስተን የተካሄደውንም የካረቢያን ሃገራት የመሪዎች ስብሰባ ተከትሎ የካሪቢያን አገራት ማህበረሰብ ሊቀመንበር እና የጋያና ፕሬዚዳንት ኢርፋን አሊ እንደተናገሩት “የሽግግር ፕሬዚዳንት ምክር ቤት እንደሚቋቋም፣ ጊዜያዊ ጠቅላይ ሚኒስትር እንዲሰየም እንዲሁም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከስልጣን መልቀቃቸውን እናረጋግጣለን” ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሽግግር ፕሬዚዳንታዊ ምክር ቤት እና ጊዜያዊ ጠቅላይ ሚኒስትር ሲቋቋሙ ከስልጣን ለመልቀቅ ተስማምተዋል። “የሽግግር ምክር ቤቱ ሥራ ከጀመረ በኋላ ወዲያው ለቀን እንወጣለን፥ ጠቅላይ ሚኒስትርና አዲስ ካቢኔ እስኪሰየሙ ድረስ ተጠባባቂ መንግሥት እንሆናለን” ሲሉ አቶ ሄንሪ ተናግረዋል።

የሄይቲ ህዝብ ስለሰጣቸው እድል አመስግነው፥ "ሰላም እና መረጋጋት በተቻለ ፍጥነት እንዲሰፍን የተቻላቸውን ሁሉ እንዲያደርጉ እና እንዲረጋጉ" አበረታቷቸዋል።

ባለፉት ሳምንታት እየተባባሰ የመጣው ብጥብጥ

የካቲት ወር መጨረሻ ላይ የታጣቂ ቡድኖች ጥምረት በፖሊስ ጣቢያዎች ላይ ጥቃት በመሰንዘር እንዲሁም ሁለቱን የሄይቲ ትላልቅ እስር ቤቶች መውረራቸውን ተከትሎ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የዓለም አቀፍ የጸጥታ ኃይል በአገራቸው እንዲሰማራላቸው ውል ለመፈረም በኬንያ ተገኝተው ነበር።

ሆኖም በዋና ከተማው በፖርት ኦ ፕሪንስ እሳቸው በሌሉበት ብጥብጡ ተባብሶ ከኬንያ ሲመለሱም ጠቅላይ ሚኒስትሩን የጫነው አውሮፕላን በተከተታይ ጥቃት ባስተናገደው የሄይቲ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን እንዳያርፍ ተደረገ። በመሆኑም የአሜሪካ ግዛት ወደሆነችው ፖርቶ ሪኮ እንዲቆዩ ተደረገ።

በ2013 ዓም ፕሬዚዳንት ጆቬኑል ሞይስ ከተገደሉ በኋላ ስልጣን የተቆናጠጡት ጠቅላይ ሚኒስትር ሄንሪ የጸጥታው ሁኔታ መሻሻል አለበት በሚል ምክንያት ምርጫውን በተደጋጋሚ በማራዘማቸው ከፍተኛ ትችት ገጥሟቸዋል። የመጨረሻ ምርጫ የተካሄደውም በ2008 ዓ.ም. እንደሆነ ይታወቃል።

‘ካሪኮም’ ተብሎ የሚታወቀው የካሪቢያን አገራት ማህበረሰብ ቡድን ለሄይቲ መረጋጋት ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንቅፋት ሆነዋል ብሎ አቋም መያዙን ተከትሎ እና የሽግግር ምክር ቤት ለመመስረት መንገዱን እንዲያመቻቹ ካሳሰቡ በኋላ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ስልጣን መልቀቅ ይጠበቃል።

ቤተክርስቲያን ‘የብርታትና የእርዳታ ምንጭ ናት’

በሀገሪቱ ውስጥ ባለው ሁከት እና በርካታ ማህበራዊ ጉዳዮች መካከል፣ ቤተክርስቲያን ለብዙዎች የጥንካሬ እና ውጤታማ የእርዳታ ምንጭ መሆኗን ቀጥላለች።

በጄሬሚ ከተማ ውስጥ በሚገኘው በተራራማ መንደር አዲስ የተቋቋመው የእመቤታችን ዘላለማዊ ረድኤት ሃገረስብከት ካህን የሆኑት አባ ማሲሞ ሚራሊዮ ከቫቲካን ዜና ባልደረባ ፌደሪኮ ፒያና ጋር ባደረጉት ቆይታ፥ “ቤተክርስቲያኒቷ ሁል ጊዜ የሄይቲን ህዝብ በታላቅ ጥንካሬ እና በታላቅ ድፍረት ታጅባለች” በማለት በሄይቲ እንዴት ቤተክርስቲያን የጥንካሬ እና የእርዳታ ምንጭ እንደሆነች ተናግረዋል።

አባ ሚራሊዮ የካቶሊክ ተቋማት በማኅበራዊ ልማቶች፣ ትምህርት ቤቶች፣ ሆስፒታሎች፣ የምገባ ማዕከላት እና የመሳሰሉ አገልግሎቶችን እጅግ ድሃ በሆኑ አካባቢዎች ላይ እንደምትሰጥና በዚያ ያሉት ልጆች የነገ ሃገር ተረካቢ ዜጋ እንዲሆኑ የሚያዘጋጃቸውን ወሳኝ ትምህርታዊ ፕሮግራሞችን ለማካሄድ የሚሞክሩባቸው ትምህርት ቤቶች በማንፃት የምትሰራቸውን ሥራዎች በማንሳት፥ ብዙ ሃይማኖታዊ ማህበረሰቦች በየቀኑ የሚያካሂዱትን ሥራ አወድሷል።

ሄቲን መልሶ በመገንባት ላይ የቤተ ክርስቲያን ሚና

አባ ሚራሊዮ ቤተክርስቲያን አዲስ እና “የተለየ ገጽታ ያላት ሄይቲ” በመገንባት ረገድ የምትጫወተው ሚና ከፍተኛ እንደሆነ ያምናሉ። ይሄንንም በማስመልከት “ሄይቲን እንዴት እንደገና መገንባት እንደሚቻል እና አዲስ ገፅታ ስለሚኖራት ሄይቲ ከአሁን ጀምሮ ማሰብ አስፈላጊ ነው” ብለዋል።

ሄይቲ ከደረሱባት የተፈጥሮ አደጋዎች በኋላ ስለምታገኘው የአስቸኳይ ጊዜ ዕርዳታ መርሃ ግብሮች ብቻ ሳይሆን ማሰብ ያለባት፥ ሃገሪቷ አሰቃቂ ሰው ሰራሽ ግጭቶች ውስጥ እንደመገኘቷ ለመልሶ ግንባታው ትክክለኛ ዕቅድ እንደሚያስፈልገው በአጽንዖት ገልጸዋል።

በሄይቲ የሚገኙ ሁሉም ሃይሎች በጠረጴዛ ዙሪያ ተሰብስበው ሀገሪቱን የመገንባቱን እቅድ እንደሚያዘጋጁ ያላቸውን እምነት ገልፀዋል።

የሃገረ ስብከቱ ካህን በተጨማሪም ወጣቶች፣ እንዲሁም ቀደም ሲል ከታጣቂ ቡድኖቹ ጋር ሲንቀሳቀሱ የነበሩትን ወደ ህብረተሰቡ እንዲቀላቀሉ ለማስቻል የቤተክርስቲያንን ሚና ከፍተኛ እንደሆነ አመላክተዋል።

አባ ሚራሊዮ ቃለ ምልልሱን ሲያጠቃልሉ ቤተክርስቲያን “ለተአማኒነቷ እና በነዚህ ሁሉ ዓመታት ከሄይቲ ህዝብ ጋር በመሆን ላከናወነችው ታላቅ ስራ አንፃር አሁንም መሰረታዊ ሚና ይኖራታል” ብለዋል።
 

13 March 2024, 14:48