ፈልግ

የፖርት ኦ-ፕሪንስ ነዋሪዎች መንግስትን በመቃወም  ሰላማዊ ሰልፍ ወጥተው የፖርት ኦ-ፕሪንስ ነዋሪዎች መንግስትን በመቃወም ሰላማዊ ሰልፍ ወጥተው 

ኬንያ ወደ ሄይቲ ሰላም አስከባሪ ኃይል ለመላክ ያቀረበችው ጥያቄ ተቃውሞ ገጥሞታል

ኬንያ ከሄይቲ ጋር የሁለትዮሽ ስምምነት የተፈራረመች ሲሆን፥ በዚህም ስምምነት በተቃዋሚዎች ሰልፍ እየተናጠች ላለችው የካሪቢያን ሀገር የሰላም አስከባሪ ሃይል ትልካለች። ነገር ግን የኬንያ ተቃዋሚ ፖለቲከኞች ይሄንን እርምጃ በመቃወም ከወዲሁ ስምምነቱን ለማደናቀፍ እየጣሩ እንደሆነ ተዘግቧል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

የሄይቲ ጠቅላይ ሚኒስትር ኤሪኤል ሄንሪ በኬንያ ያደረጉትን ስብሰባ ተከትሎ፥ ከኬንያ ፕሬዚዳንት ዊሊያም ሩቶ ጋር የእርስ በእርስ ስምምነት ተፈራርመዋል።

ኬንያ በተለያዩ ወንጀሎች እየተናጠች ወደምትገኘው ምዕራባዊ ደሃ ሃገር ሄይቲ በታጣቂዎች ከበባ ውስጥ የሚገኙትን ፖሊሶች እና መከላከያ ሃይል ለማጠናከር እና ለመደገፍ በተለይም በተቃውሞ ሰልፎች እየታመሰች ወደምትገኘው ዋና ከተማዋ ፖርት አው ፕሪንስ አንድ ሺህ የሰላም አስከባሪ ሃይል እንደምትልክ ታውቋል።

እንዲሁም ቤኒን 2,000 ወታደሮችን ለመላክ ያቀደች ሲሆን፥ ጃማይካ፣ አንቲጓ እና ባርቡዳ የተለያዩ ጉዳይ አስፈፃሚ ሠራተኞችን መላክ እንደሚፈልጉ ገልጸዋል።

የሰው ሃይሏን ለመላክ የተቆጠበችው ዋሽንግተን ለዚህ የሰላም አስከባሪ ሃይል ሁለት መቶ ሚሊዮን ዶላር የገንዘብ ድጋፍ ለማድረግ ቃል ገብታለች።

የኬንያው ፕረዚዳንት ሩቶ ስለጉድዩ ሲናገሩ “ለዚህ ሁለገብ አገራዊ ተልዕኮ መሳካት ኬንያ ያላትን ቁርጠኝነት በዚህ አጋጣሚ በድጋሚ እገልጻለሁ” ያሉ ሲሆን፥ የሄይቲ ጠቅላይ ሚኒስትር ሄንሪ በበኩላቸው “አገሪቷን ለማረጋጋት ምርጫ ማድረግ እንፈልጋለን” ካሉ በኋላ “ሰዎች በሃገራችን ኢንቨስት እንዲያደርጉ ለማበረታታት በሄይቲ ጠንካራ አስተዳደር ያስፈልገናል” ብለዋል።

የተባበሩት መንግስታት ይሁንታ

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ይህንን ተልዕኮ ባለፈው ዓመት ጥቅምት ወር ላይ ያፀደቀ ቢሆንም፥ ጥር ወር ላይ የኬንያ ከፍተኛ ፍርድ ቤት እቅዱን ኢ-ህገ መንግስታዊ ነው በማለት የሀገሪቱ የፀጥታው ምክር ቤት ፖሊስ ከአገሪቱ ውጭ መሰማራት እንዳይችል ፍቃድ እንዳይሰጥ ከልክሏል።

የኬንያ ተቃዋሚ ፖለቲከኛ ኢኩሩ ኦኮት የሁለትዮሽ ስምምነቱን ተገቢነት በመቃወም፥ ሚስጥራዊ ስምምነት ነው በማለት አጣጥለውታል።
 

04 March 2024, 20:29