ፈልግ

ከሊቢያ ወደ ጣሊያን እንዲመጡ ሕጋዊ የጉዞ መንገድ የተመቻቸላቸው ስደተኞች ከሊቢያ ወደ ጣሊያን እንዲመጡ ሕጋዊ የጉዞ መንገድ የተመቻቸላቸው ስደተኞች 

ከሊቢያ ወደ ጣሊያን ለሚገቡ የአፍሪካ ስደተኞች አዲስ የጉዞ መሥመር መዘርጋቱ ተገለጸ

የጣሊያን መንግሥት ለስደተኞች ዕርዳታን ከሚሰጡት የቅዱስ ኤጂዲዮ ማኅበረሰብ፣ “ANCI” ከተሰኘ ማህበር እና ከወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት ፌዴሬሽን ጋር ባጸደቀው ውል መሠረት ሕጻናት፣ ሴቶች እና አቅመ ደካሞች የሚገኙበት 97 የስደተኞች ቡድን ከሊቢያ ተነስተው በተዘጋጀላቸው የጉዞ መሥመር ወደ ሮም መድረሳቸው ታውቋል። በተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች መርጃ ድርጅት ወደ ጣሊያን የገቡት እነዚህ ስደተኞች ራሳቸውን እንዲችሉ እና ከማኅበረሰቡ ጋር እንዲቀላቀሉ ለማድረግ ድጋፍ እንደሚያደርግላቸው ታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በተዘጋጀላቸው አዲስ የጉዞ መስመር የተጓዙት ስደተኞቹ ከዚህ በፊት ወደ አውሮፓ ለመድረስ ተደጋጋሚ ሙከራዎችን አድርገው ያልተሳካላቸው እንደነበሩ ታውቋል። ከዚህም በተጨማሪ በሊቢያ ውስጥ ባሳለፉት የእስር ቤት ቆይታ ይደርስባቸው የነበረውን እጅግ አስቸጋሪ ሁኔታ ተቋቁመው ያለፉ እንደሆነ ታውቋል። በሰብአዊ የጉዞ መስመር በኩል በሮም ወደሚገኝ ፊውሚሲኖ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ከደረሱት 97 ስደተኞች መካከል ኤርትራዊያን፣ ኢትዮጵያውያን፣ ሶርያውያን፣ ሶማሊያውያን፣ ሱዳናውያን እና ደቡብ ሱዳናውያን እንደሚገኙበት ታውቋል።

ከሊቢያ የተነሳ የመጀመሪያ በረራ

ስደተኞቹ በመጀመሪያ በረራቸው ወደ ሮም እንዲደርሱ የተመቻቸላቸው፥ የጣሊያን የሀገር ውስጥ እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ኤጀንሲ (ዩኤንኤችሲአር)፣ ከቅዱስ ኤጂዲዮ ማህበረሰብ፣ ከወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት ፌዴሬሽን፣ ከጣሊያን የጤና፣ የስደተኞች መርጃ እና ድህነት ማስወገጃ ሚኒስቴር ጋር እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በታህሳስ 2023 በተፈራረሙት ስምምነት መሠረት እንደሆነ ታውቋል። ስምምነቱ በሚቀጥሉት ጥቂት ዓመታት ውስጥ 1,500 ስደተኞች ወደ ጣሊያን እንደሚመጡ የገለጸ ሲሆን፥ ስደተኞች ወደ ጣሊያ ከደረሱ በኋላ ልጆች ወደ ትምህርት ቤት እንዲሄዱ፣ ጎልማሶች የጣሊያንኛ ቋንቋ እንዲማሩ እና ሥራ ለማግኘት እገዛ የሚደረግላቸው እንደሆነ ታውቋል።

"አዲስ የሕይወት ጉዞ"

በሮም የቅዱስ ኤጂዲዮ ማህበረሰብ ፕሬዝዳንት አቶ ማርኮ ኢምፓሊያዞ ለቫቲካን የዜና አገልግሎት እንዳስረዱት፥ ስደተኞቹ ከዓመታት በፊት ሊቢያ የደረሱ፣ በጉዞው ወቅት ብዙ መከራ የደረሰባቸው እና በሊቢያ እስር ቤቶች  ውስጥ ከፍተኛ ስቃይ ይደርስባቸው የነበሩ ከአፍሪካ የመጡ ስደተኞች እንደነበሩ አስረድተዋል። ፕሬዝዳንቱ አክለውም ስደተኞች በእውነት ዕርዳታ የሚያስፈልጋቸው እንደ ነበሩ ገልጸው፥ ከሁሉም በላይ ጣሊያን ውስጥ አዲስ የሕይወት ጎዳና እንዲጀምሩ እና ከማህበረሰቡ ጋር እንዲዋሃዱ ድጋፍ እንደሚደረግላቸው አስረድተዋል።

የስደተኞች መርጃ ድርጅት ሊቢያ ውስጥ አደጋ እንዳለ አስታውቋል

በተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች መርጃ ድርጅት “UNHCR” በሊቢያ ውስጥ ሥራውን በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ እያከናወነ እንደሚገኝ እና በጭንቀት ውስጥ የሚገኙ ስደተኞችን ለማገዝ ጥረት እያደረገ እንደሚገኝ አስረድቷል።

በተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች መርጃ ድርጅት “UNHCR” የጣሊያን፣ የቅድስት መንበር እና የሳን ማሪኖ  ተወካይ ወ/ሮ ኪያራ ካርዶሌቲ፥ “ሊቢያ ለስደተኞች አስተማማኝ አገር አይደለችም” ሲሉ ገልጸዋል። ሊቢያ ለስደተኞች በጣም አስቸጋሪ እና ብዙ መሻሻል ያልታየባት አገር እንደሆነች እናውቃለን” ብለው፥ እስከ አሁን ድረስ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ የ1951 የስደተኞች ስምምነትን ያለፈረመች፣ በስደተኞች ማቆያ ማዕከላት ውስጥ በሚገኙ ወንዶች እና ሴቶች ላይ ከፍተኛ ጥቃት ሳይቀር ብዙ ክስተቶችን የምናይባት አገር ናት ብለዋል።

እንደ ጎርጎሮሳውያኑ ከ 2017 ዓ. ም. ጀምሮ ወደ ስምንት ሺህ የሚጠጉ ስደተኞች ወደ ጣሊያን፣ ፈረንሳይ እና ቤልጂየም የደረሱት ስደትን ለመቋቋም ከወጡት ጥቂት ሕጋዊ መንገዶች ውስጥ በአንዱ እና በስምምነት በተመቻቸላቸው ልዩ የጉዞ መስመሮች አማካኝነት እንደሆነ አስረድተዋል።

06 March 2024, 15:43