ፈልግ

ሩሲያ ኪየቭን በሚሳኤል ካጠቃች በኋላ ሩሲያ ኪየቭን በሚሳኤል ካጠቃች በኋላ 

ሩስያ በኪየቭ ላይ በወሰደችው የሚሳኤል ጥቃት በርካታ ሰዎች መሞታቸው ተነገረ

የዩክሬን ባለስልጣናት እንደተናገሩት የሩስያ ጦር በዋና ከተማዋ ኪየቭ ላይ በ44 ቀናት ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ በወሰደው የሚሳኤል ጥቃት አንድ ህፃን ልጅን ጨምሮ 10 ሰዎች የቆሰሉ ሲሆን፥ በተጨማሪም በሰሜኑ የሃገሪቱ ክፍል ባከናወነችው የአየር ላይ ጥቃት በትንሹ የ5 ሰዎች ህይወት ማለፉ ተነግሯል። ጥቃቱ የተፈፀመው ዩክሬን የሩሲያን ወረራ ለመመከት በሩስያ ግዛት ውስጥ ያሉትን አካባቢዎች በማጥቃቷ እንደሆነ የተገለጸ ሲሆን፥ በግጭቱ ምክንያት በሺዎች የሚቆጠሩ ህጻናት ከድንበር አከባቢዎች እንዲወጡ እንደተደረገም ተነግሯል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

በዩክሬን ዋና ከተማ ኪየቭ ላይ ሚሳኤሎች በተተኮሱበት ወቅት ጭሱ ከሩቅ ይታይ እንደነበር እና በበርካታ ሰዎች ላይም ጉዳት ማድረሱ ዘገባዎች አሳይተዋል።

ሆኖም የዩክሬን አየር ሃይል አዛዥ የሆኑት ሚኮላ ኦሌሹክ ኢላማቸውን ኪየቭ ላይ ያደረጉት 31 የሩስያ ሚሳኤሎች ተመትተው እንደወደቁ በመግለጽ፥ ከነዚህም መካከል 2 ባለስቲክ ሚሳኤሎች እና 29 ክራይዝ ሚሳኤሎች ይገኙበታል ብለዋል።

የኪየቭ ከንቲባ ቪታሊ ክሊችኮ በበኩላቸው የሮኬት ፍንጥርጣሪዎች በሲቪያቶሺኒስኪ አውራጃ ውስጥ በሚገኘው መዋለ ህፃናት ላይ እና በከተማው የተለያዩ ቦታዎች መውደቃቸውን እንዲሁም የመኖሪያ ህንጻዎችን መምታታቸውን በመግለጽ፥ በብዙ አካባቢዎች የእሳት ቃጠሎ ማስነሳታቸውንም አክለው አመልክተዋል፡፡ ከንቲባው እንዳሉት በዚህ ጥቃት የ11 ዓመት ታዳጊን ጨምሮ ቢያንስ አስር ሰዎች ተጎድተዋል ብለዋል፡፡

በጥቃቱ ምክንያት አብዛኛው ነዋሪ አካባቢውን ለቆ እንደተፈናቀለ እና በርካቶች በኪየቭ የምድር ውስጥ ባቡር ጣቢያ ህፃናት ልጆቻቸውን ይዘው እንደተሸሸጉ ተነግሯል።

የሩሲያ ሚሳኤል ከኪየቭ በተጨማሪ ረቡዕ ዕለት ሰሜናዊ ዩክሬን በምትገኘው ካርኪቭ ከተማ የሚገኘውን የኢንዱስትሪ መንደር በመምታቱ ቢያንስ አምስት ሰዎች መሞታቸው ተዘግቧል።

የአከባቢው ባለሥልጣናት እንደተናገሩት ሚሳኤሉ በማተሚያ ቤት ውስጥ ከፍተኛ የሆነ የእሳት አደጋ በማድረስ ቢያንስ ስምንት ሰዎች እንደቆሰሉ እና ሌሎች ተጨማሪ ሰዎችን ደግሞ ማግኘት እንዳልተቻለ ተናግረዋል።

ይህ በእንዲህ እያለ ሩሲያም ጥቃት እንደደረሰባት የተነገረ ሲሆን፥ በዩክሬን ወታደራዊ የስለላ ድርጅት የሚንቀሳቀሱ የዩክሬን ሰው አልባ አውሮፕላኖች ረቡዕ ዕለት ሩሲያ ግዛት ውስጥ የሚገኘውን የኢንግልስ አየር ማረፊያ መምታታቸውን ባለስልጣናት ተናግረዋል።

በሌላ ዜና በሩሲያ ውስጥ በሚገኙ የድንበር አካባቢዎች የሚንቀሳቀሱ በዩክሬን የሚደገፉ ታጣቂዎች ላይ በርካታ ጥቃቶች ተፈጽመዋል።

የሩሲያ ባለስልጣናት እንደተናገሩት ጦርነቱ እየተባባሰ በመሄዱ እና ዩክሬን ባለማቋረጥ በምትወስደው ጥቃት ምክንያት 9,000 የሚጠጉ ህጻናትን ከድንበር አካባቢ ለማስወጣት እቅድ እንዳላቸው ገልጸዋል።

የአካባቢው ገዥ የሆኑት ቭያቼስሌቭ ግላድኮቭ እንዳሉት ህፃናቱ ከዩክሬን ድንበር ርቆ በሚገኘው ምስራቃዊው የቤልጎሮድ ክልል ይወሰዳሉ ብለዋል።

ይህ መግለጫ የወጣው የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን የድንበር ክልሎችን ከረጅም ርቀት እና ድንበር ዘለል የዩክሬን ጥቃቶች ለመጠበቅ የክሬምሊን መንግስት የመከላከያ ቀጠና ለማቋቋም እንደሚፈልግ ከገለፁ በኋላ ነው።

ጦርነቱ ሶስተኛ ዓመቱን የያዘ ቢሆንም፥ በቅርቡ እንደሚያበቃ ምንም ፍንጭ አልተገኘም። ለዚህም ማሳያ ረቡዕ ዕለት ምዕራባውያን ለዩክሬን ተጨማሪ ወታደራዊ እና ሰብአዊ ዕርዳታ ለመስጠት ቃል ገብተዋል።

የኔዘርላንድ መከላከያ ሚኒስትር ካጃሳ ኦሎንግረን ወደ ኪዬቭ በማቅናት እንደተናገሩት ኔዘርላንድ ለኤፍ-16 ተዋጊ ጄት ጥይቶች እና ዘመናዊ የስለላ ሰው አልባ አውሮፕላኖች መግዣ 350 ሚሊዮን ዩሮ ወይም 380 ሚሊዮን ዶላር ለዩክሬን እንደምትሰጥ ተናግረዋል።

የአውሮጳ ኅብረት ሥራ አስፈፃሚ ኮሚሽን እንደገለጸው ጦርነት ላይ ያለችውን ዩክሬን ለመደገፍ አዲስ በተቋቋመው የአውሮፓ ኅብረት ድርጅት በኩል የመጀመሪያውን 4.5 ቢሊዮን ዩሮ ወይም 5 ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ ድጋፍ መስጠቱን ገልጿል።

የአውሮፓ ህብረት መሪዎች ከታገዱ የሩሲያ የፋይናንስ ንብረቶች ያስገኙ ከነበረው ዓመታዊ 3 ቢሊዮን ዩሮ ትርፍ ለዩክሬን የጦር መሳሪያ ለመግዛት ስለሚቻልባቸው መንገዶች ሃሙስ ዕለት ሲወያዩ እንደነበርም ተነግሯል።

ዩክሬን የምዕራቡ ዓለም በሚያደርግላት ተጨማሪ ድጋፍ በዓመት 2 ሚሊዮን ሰው አልባ አውሮፕላኖችን ማምረት እንደምትችል ተናግራለች።

ይሁን እንጂ ጦርነቱ ተጠናክሮ በቀጠለ ቁጥር የሟቾች ቁጥር እየጨመረ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ለሞት እና ለጉዳት እየዳረገ ይገኛል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ቢሮ ባወጣው አዲስ ሪፖርት ሩሲያ ወርራ በተቆጣጠረቻቸው የዩክሬይን አካባቢዎች ነዋሪዎችን በፍርሃት እያሸማቀቀች መሆኗን አመልክቷል። ከ2300 የሚበልጡ ሰለባዎችና ዕማኞችን በማነጋገር የተጠናቀረው ሪፖርት የሞስኮ ኃይሎች ሕዝቡን የሩስያ ቋንቋ እንዲናገር እያስገደዱት ዩክሬናዊ ማንነቱንና ባሕሉን እንዳያሳይ እያፈኑት መሆናቸውን አውስቷል፡፡
 

22 March 2024, 12:06