ፈልግ

በዋና ከተማዋ ፖርት አው ፕሪንስ የሚገኝ የሄይቲ ብሔራዊ ማረሚያ ቤት በዋና ከተማዋ ፖርት አው ፕሪንስ የሚገኝ የሄይቲ ብሔራዊ ማረሚያ ቤት  

በሄይቲ ጠበኛ ቡድኖች እስር ቤቱን ወርረው ታራሚዎችን ነጻ ማድረጋቸው ተነገረ

ከ3000 የሚበልጡ የሄይቲ ብሔራዊ ማረሚያ ቤት እስረኞች፥ በሄይቲ የሚገኙ ጠበኛ ቡድኖች በተቋሙ ላይ ጥቃት ባደረሱበት ወቅት ብጥብጥ መቀስቀሱ ተነግሯል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በዋና ከተማዋ ፖርት አው ፕሪንስ በሚገኝ የሄይቲ ብሔራዊ ማረሚያ ቤት ውስጥ በእስር የቆዩ ከሦስት ሺህ በላይ ታራሚዎች በታጠቁ የጎዳና ላይ ዎሮበሎች ነፃ ከወጡ በኋላ በከተማይቱ ጎዳናዎች ላይ ሲዘዋወሩ ታይተዋል። ከማረሚያ ቤቱ ውጭ የጦር መሣሪያ ተኩስ ሲሰማ ፖሊሶች እገዛ እንዲደረግላቸው ቢጠይቁም የደረሰላቸው እንደሌለ ተነግሯል።

በመጀመሪያ 3,686 ታራሚዎችን እንዲይዝ ተብሎ የተገነባው ማረሚያ ቤቱ ለረጅም ጊዜ ተጨናንቆ እንደነበር ተነግሯል። ዋና መግቢያ በሮቹ በታጠቁ ወሮበሎች ሲሰበሩ በመቶዎች የሚቆጠሩ እስረኞች ማረሚያ ቤቱን ለቅቀው ሲያመልጡ ታይተዋል። እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ2021 ዓ. ም. በፕሬዚደንት ጆቬኔል ሞይስ ግድያ የተከሰሱ አሥራ ስምንቱን የኮሎምቢያ ቅጥረኞችን ጨምሮ አንድ መቶ እስረኞች ለሕይወታቸው በመፍራት በማረሚያ ቤቱ ውስጥ መቆየትን እንደመረጡ አንድ የማረሚያ ቤት በጎ ፈቃደኛ ተናግሯል። በግርግሩ ወቅት አምስት ሰዎች በጥይት ተመትተው መውደቃቸው ተነግሯል።

በመዲናይቱ የሚገኝ ሌላ ማረሚያ ቤትም ወረራ እንደተፈጸመበት እና ወንበዴዎቹ ወደቡን ለመቆጣጠር ሙከራ ማድረጋቸውን ከሥፍራው የሚወጡ መረጃዎች ገልጸዋል።

ወንበዴዎች መንግሥትን የመጣል ዓላማ አላቸው

የቅርብ ጊዜው ብጥብጥ ተቀሰቀሰው የሄይቲ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኤሪኤል ሄንሪ ኬንያን ጎበኝተው በአገር አቀፍ ደረጃ ያለውን ሥርዓት አልበኝነት ለመቅረፍ ሙከራ በማድረግ ላይ በነበሩበት ወቅት እንደሆነ ታውቋል።

የጎዳና ላይ ቡድኖች ጥምረት እመራለሁ የሚለው የቀድሞ የፖሊስ አባል ጂሚ ቼሪዚየር፥ የፖሊስ አዛዡን እና የመንግሥት ሚኒስትሮችን ለመያዝ፣ መንግሥትንም በማፍረስ ጠቅላይ ሚኒስትር ኤሪኤል ሄንሪ ወደ ሄይቲ እንዳይመለሱ ለማድረግ ዓላማ እንዳላቸው ተናግሯል።

ሄይቲ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ ከ2016 ዓ. ም. ጀምሮ ብሔራዊ ምርጫ ሳታካሂድ የቆየች ስትሆን፥ የወቅቱ የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኤሪኤል ሄንሪ በየካቲት ወር ስልጣናቸውን ለመልቀቅ ያቀዱ ቢሆንም እየተካሄደ ያለው ትርምስ እና ብጥብጥ ያ እንዳይሆን ማገዱ ታውቋል።

 

05 March 2024, 16:59