ዩክሬን በትንሳኤ በዓል ዕለት ከፍተኛ ጥቃት እንደደረሰባት ተነገረ
አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ
የዩክሬን ክርስቲያኖች በዚህ የትንሳኤ እሑድ ለአምልኮ በተሰበሰቡበት ወቅት፥ የሩስያ መከላከያ ሚኒስቴር እንደገለጸው ዩክሬንን ለማጥቃት ‘ኢላማውን የማይስት ረጅም ርቀት የሚጓዝ የጦር መሳሪያ’ እና ሰው አልባ አውሮፕላኖችን መጠቀሙን ገልጿል።
ሩሲያ አርብ እለት ወደ ዩክሬን የተኮሰቻቸው በደርዘን የሚቆጠሩ ሚሳይሎች እና 60 ሰው አልባ አውሮፕላኖች በሦስት ኃይል ማመንጫዎች ላይ ጉዳት ማድረሳቸውን እና ከፍተኛ የኤሌክትሪክ መቋረጥ ማስከተላቸውን የዩክሬን ባለስልጣናት አስታውቀዋል።
የሩሲያ መከላከያ ሚኒስቴር በመግለጫው እንዳስታወቀው ባደረሰው ጥቃት ምክንያት “የጦር መሳሪያዎችን እና ጥይቶችን በማምረት እና በመጠገን ላይ የነበሩ የዩክሬን መከላከያ ኢንደስትሪ ኢንተርፕራይዞች እንቅስቃሴዎች ተስተጓጉለዋል” ብሏል። በዚህም የታለሙት ኢላማዎች በመመታታቸው የተወጠኑት ግቦች በሙሉ መሳካታቸውን መግለጫው አክሎ ገልጿል።
የዩክሬን አየር ሃይል እሁድ ማምሻውን እንደገለጸው፣ ሩሲያ በአንድ ሌሊት ባደረገችው ጥቃት 16 ሚሳኤሎችን እና 11 ሰው አልባ አውሮፕላኖችን ማስወንጨፏን ካስታወቀ በኋላ፥ አየር ሃይሉ 9ኙን ሰው አልባ አውሮፕላኖች እና ዘጠኝ ሮኬቶች ማውደሙንም ገልጿል።
በዩክሬን የኦዴሳ ክልል የሚገኙ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ተመቶ የወደቀው የሩስያ ሰው አልባ አውሮፕላን በሃይል ማመንጫ ጣቢያ ላይ ወድቆ ባደረሰው የእሳት አደጋ ምክንያት የኃይል አቅርቦት ተቋርጦባቸው እንደነበር ተነግሯል። በጥቃቱ ምክንያት ወደ 170,000 የሚጠጉ ቤቶች ለጊዜያዊ የመብራት መቆራረጥ መጋለጣቸውን ባለስልጣናት አስታውቀዋል።
በዚህ ምክንያት ዩክሬን ከአውሮፓ የምታስገባውን የኃይል መጠን የጨመረች ሲሆን፣ በምላሹ ሰው አልባ አውሮፕላኖችን በመጠቀም በሩሲያ የነዳጅ ዘይት ፋብሪካዎች ላይ የምታደርሰውን ጥቃት አጠናክራ ቀጥላለች።
ጥቃቶቹ የተፈፀሙት ዩክሬን የትንሳኤ በዓል እና በርካታ ሰው እንዳለቀበት የሚነገርለትን የቡቻ ከተማ ነፃ የወጣበት 2ኛ ዓመት ክብረ በዓል እያከበረች ባለችበት ወቅት ሲሆን፥ ይህም የካቲት 2014 ዓ.ም. ሩሲያ ሀገሪቱን ከወረረች በኋላ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ለሞት እና ለአካል ጉዳት ያደረሰውን ጦርነት አስከፊ ገፅታዎች መገለጫ ነው ተብሏል።
ሩሲያ ሙሉ ወረራዋን በጀመረችበት ወቅት ከዋና ከተማዋ ኪየቭ 25 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የምትገኘው የቡቻ ከተማን ተቆጣትራ የነበረ ሲሆን፥ የሰብአዊ መብት መርማሪዎች እና አቃቤ ህጎች እንደሚሉት ሩሲያ በወቅቱ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሲቪሎችን ገድላ በጅምላ መቃብር ውስጥ ቀብራለች ያሉ ሲሆን፥ እነዚህም አስከሬኖች የተገኙት ዩክሬን መጋቢት 2014 ዓ.ም. ላይ አካባቢውን እንደገና ከተቆጣጠረች በኋላ መሆኑን ገልጸዋል።
በተጨማሪም ዩክሬን ምዕራባውያን የሚያደርጉላት ድጋፍ እየቀነሰ በመምጣቱ በጦርነቱ ልትሸነፍ ትችላለች የሚሉ ስጋቶች እያየሉ መጥተዋል።
በቅርብ ቀናት ውስጥ የሩሲያ ጦር አካባቢውን ለመቆጣጠር ጥረት እያደረገ ባለበት ወቅት ቢያንስ አንድ የዩክሬን ታንከኛ ምድብ በባክሙት አቅጣጫ በሚገኘው የሩሲያ እግረኛ ጦር ላይ የመድፍ ጥቃት አድርሷል። ሆኖም ግን በአከባቢው የነበሩ አንድ የዩክሬን ጦር አዛዥ የጦርነቱ የፊት መስመር ላይ የጦር መሳሪያ አቅርቦት እየቀነሰ በመምጣቱ ቅሬታቸውን አቅርበዋል።
የመጀመሪያ ስማቸውን ብቻ የገለጹት ኮማንደር ኢጆር “በግንባሩ መስመር ላይ ያለው ሁኔታ የተወሳሰበ ነው። የመሳሪያ እጥረት አለብን። አቅርቦቱ ቢኖር ለእግረኛ ወታደሮቹ በጣም ቀላል ይሆን ነበር” ብለዋል።
ሁለቱ ሃገራት በተለያየ ጊዜ የሰላም ድርድር እንዲያደርጉ ጥሪ ቀርቦላቸው የነበረ ቢሆንም፥ ሞስኮ እና ኪየቭ ጦርነቱን ማቆም የሚቻልባቸው ቅድመ ሁኔታዎች ላይ መግባባት አልቻሉም። ለዚያም ነው ገና ዕድሜያቸው ያልደረሱትን ጨምሮ በርካታ ወንዶች ከአንደኛው የዓለም ጦርነት ጋር እየተመሳሰለ በሚገኘው የጦር ግንባር እየተቀላቀሉ የሚገኙት።