ፈልግ

ቡርኪናፋሶ፣ በዓለም ላይ በጣም የተዘነጋ የመፈናቀል ቀውስ ያለባት ሃገር ቡርኪናፋሶ፣ በዓለም ላይ በጣም የተዘነጋ የመፈናቀል ቀውስ ያለባት ሃገር  (AFP or licensors)

በቡርኪናፋሶ ውስጥ ያለው የመፈናቀል ቀውስ በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በጣም መዘንጋቱ ተነገረ

የምዕራብ አፍሪካዊቷ ሀገር ቡርኪናፋሶ በኖርዌይ የስደተኞች ምክር ቤት ለሁለት ተከታታይ ዓመታት በዓለም እጅግ የተዘነጋ የመፈናቀል ቀውስ ያለባት ሃገር ተብላለች።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

የኖርዌይ የስደተኞች ምክር ቤት (NRC) ሰኞ ዕለት ባወጣው ዘገባ መሠረት ቡርኪናፋሶ ለተከታታይ ሁለት ዓመታት በዓለም እጅግ ችላ ከተባሉ ቀውሶች ያሉባቸው ሃገራት ዝርዝር ውስጥ ቀዳሚ ሆናለች።

በምዕራብ አፍሪካዊቷ ሀገር በአሁኑ ወቅት ወደ 2 ሚሊዮን የሚጠጉ ተፈናቃዮች እንደሚገኙ የገለጸው ግብረሰናይ ድርጅቱ፣ ለአብዛኞቹ ተፈናቃዮች ሰብአዊ እርዳታ እንደማይደርሳቸው አረጋግጧል።

የኖርዌይ የስደተኞች ምክር ቤት በየዓመቱ በዓለም ላይ በጣም የተዘነጉ የመፈናቀል ቀውሶች ያሉባቸው የአስር ሃገራት ዝርዝር ያወጣል። የመፈናቀል ምክንያቶቹ በሦስት መመዘኛዎች ላይ የተመሰረተ ነው ያለው ተቋሙ፥ እነዚህም “የሰብአዊ ድጋፍ እጦት፣ የሚዲያ ትኩረት እጦት እና የዓለም አቀፍ የፖለቲካ እና የዲፕሎማሲ ውጥኖች እጥረት” እንደሆኑም አትቷል።

ድጋፎቹ በቂ አይደሉም

በኖርዌይ የስደተኞች ምክር ቤት የጥብቅና ሥራ አስኪያጅ ማሪን ኦሊቬሲ ለቫቲካን ዜና እንደተናገሩት “በእነዚህ ሃገራት አንዳንድ የሰላም እጦት አዝማሚያዎች እየተባባሱ በመሆናቸው በእነዚህ አገሮች ውስጥ ላሉ ተፈናቃዮች እርዳታ ለመስጠት ባለን አቅም ላይ ተጽዕኖ አሳድረዋል ያሉት ሃላፊዋ ምክንያቱም ደግሞ የእርዳታ ፍላጎቶች በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ መምጣቱ እና ለዚህ እርዳታ የሚሆን የገንዘብ ድጋፎች በበቂ ሁኔታ አለመገኘት ናቸው” በማለት ያለውን ችግር ገልጸዋል።

የጦርነቱ ሰለባዎች

በ 2015 ዓ.ም. በቡርኪና ፋሶ ውስጥ ከሁከት ጋር በተያያዘ የተከሰተው የሞት ቁጥር በእጥፍ መጨመሩ የተነገረ ሲሆን፥ በእነዚህም ግጭቶች ከ8,000 በላይ ሰዎች ተገድለዋል ተብሏል። ወ/ሮ ማሪን ኦሊቬሲ ስለዚህ ጉዳይ ሲያብራሩ “ያለፈው ዓመት ለቡርኪናፋሶ በጣም አስከፊው ዓመት ነበር፥ ምክንያቱም በሃገሪቷ ከ 5 እና 6 ዓመታት በፊት ግጭቱ ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ ከሞቱት ሰዎች በበለጠ ሁኔታ ባለፈው ዓመት በተፈጠረው ሁከት ብዙ ሰዎች ሞተዋል” ብለዋል።

ሁኔታውን ለማሻሻል የገንዘብ ድጋፍ ማድረግ ያስፈልጋል

ለተቋሙ የጥብቅና ሥራ የሚሰሩት ሓላፊዋ እንደሚሉት ይህ ዓመታዊ ግምገማ እንደሚያሳየው የዓለም አቀፍ ድጋፍ እና የሚዲያ ሽፋን ማሽቆልቆሉን ጠቁሟል፥ ይህም የሆነበት ምክንያት በከፊል በዝርዝሩ ውስጥ በተካተቱ በብዙ ሀገራት ውስጥ የሚዲያ ነፃነት አለመኖር እና እንዲሁም ቀጣይነት ያለው የሰብአዊ ድጋፍ መቀነስ እንደሆነ ያሳያል።

ወ/ሮ ማሪን ኦሊቬሲ ሲያጠቃልሉ “በዓለም ላይ በጣም ቸል ለተባሉ ቀውሶች የገንዘብ ድጋፎችን እንፈልጋለን” በማለት ጥሪያቸውን ካቀረቡ በኋላ፥ “እነዚህ የገንዘብ ድጋፎች ተፋላሚ ወገኖችን ለማግኘት በዲፕሎማሲያዊ መንገድ መደረግ እንዳለባቸው፥ እንዲሁም ከለጋሽ ሀገራት ፍላጎት ጋር የሚመጣጠን የገንዘብ ድጋፍ ማድረግ አለባቸው” ብለዋል።
 

05 June 2024, 13:59