ዶናልድ ትራምፕ በተደረገባቸው የግድያ ሙከራ መቁሰላቸው ተነገረ
አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ
የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝዳንታዊ ዕጩ ዶናልድ ትራምፕ በፔንስልቬንያ በትለር ከተማ በተካሄደው የምርጫ ቅስቀሳ ዘመቻ ላይ የግድያ ሙከራ ከተደረገባቸው በኋላ ፊታቸው ላይ ደም እየፈሰሰ ቀኝ እጃቸውን ወደላይ ከፍ አድርገው ‘እናሸንፋለን’ ሲሉ ታይተዋል።
ትራምፕ በፔንስልቪንያ ግዛት ለደጋፊዎቻቸው ንግግር እያደረጉ ሳለ በርካታ የተኩስ ድምጾች ተሰምተዋል።
ሪፐብሊካን ፓርቲን በመወከል ኅዳር 2017 ዓ.ም. በሚደረገው ምርጫ ላይ የሚሳተፉት ዶናልድ ትራምፕ የግድያ ሙከራው የተፈጸመባቸው በትለር በተባለችው የፔንሰልቪኒያ ከተማ የምርጫ ቅስቀሳቸውን እንደጀመሩ ነበር። የመንግሥት የደኅንነት ሠራተኞች የቀድሞ ፕሬዝዳንቱን ለመከላከል በፍጥነት ወደ መድረክ በመውጣት ዝቅ አድርገዋቸው ከሚተኮሰው ጥይት ሲከላከሉ ታይተዋል።
ፕሬዝዳንቱ ዝቅ ካሉበት ሲነሱ ፊታቸው እና ቀኝ ጆሯቸው ደም የታየበት ሲሆን፤ የግድያ ሙከራው ከተፈጸመባቸው ስፍራ ወደተዘጋጀላቸው መኪና ሲወሰዱ ቀኝ እጅቸውን በማንሳት የአይበገሬነት መልዕክት አስተላልፈዋል።
የቀድሞ ፕሬዝዳንት በአካባቢው ባለ ሆስፒታል የሕክምና ድጋፍ እንደተደረገላቸው ገልጸው፤ “ጥይት ቆዳዬን በስቶ ሲገባ ተሰማኝ፣ በጣም ብዙ ደም ፈሶኛል። ምን እየተፈጸመ እንደሆነ ግራ ገብቶኝ ነበር” በማለት በማህበራዊ ገፃቸው ላይ ጽፈዋል።
የግድያ ሙከራውን ፈጽሟል ተብሎ የታሰበው ግለሰብ በአሜሪካ ሴክሬት ሰርቪስ (ደኅንነት) አባላት መገደሉን የተቋሙ ቃል አቀባይ ተናግረዋል።
ከተጠርጣሪው በተጨማሪ አንድ ሰው በተኩስ ልውውጡ መገደሉ እና ሌሎች ሁለት ሰዎች ደግሞ በከፍተኛ ሁኔታ መቁሰላቸው ተገልጿል።
ትራምፕ በአካባቢው ወደሚገኝ ሆስፒታል ተወሰደው ህክምናቸውን ከተከታተሉ በኋላ ወደ ኒው ጀርሲ መመለሳቸውም ተገልጿል።
የፖለቲካዊ ጥቃቱ ላይ የደረሰው ዓለም አቀፋዊ ውግዘት
የግድያ ሙከራው ላይ ዓለም አቀፋዊ ውግዘት የደረሰበት ሲሆን፥ በመጪው ህዳር ወር ላይ በሚካሄደው ፕረዚዳንታዊ ምርጫ የትራምፕ ተፎካካሪ የሆኑት ፕረዚዳንት ጆ ባይደን ከጥቃቱ በኋላ ከትራምፕ ጋር ተገናኝተው የተነጋገሩ ሲሆን፥ በኋላ ላይ የማህበራዊ ድህረ ገጽ በሆነው የኤክስ ገፃቸው ላይ “[ትራምፕ] ደህንነታቸው የተጠበቀ እና ከአደጋው እያገገሙ መሆኑን በመስማቴ አመሰግናለሁ። ስለጥቃቱ ተጨማሪ መረጃ እስከምናገኝ ድረስ ለእሳቸው እና ለቤተሰባቸው እንዲሁም በሰልፉ ላይ ለነበሩት ሁሉ እጸልያለሁ” ካሉ በኋላ፥ ባይደን አክለውም፣ “በአሜሪካ ውስጥ ለእንደዚህ አይነት ጥቃት ምንም ቦታ የለንም። እንደ አንድ ሀገር ተባብረን ማውገዝ አለብን” በማለት ጽፈዋል።
ብጹአን ጳጳሳት ፖለቲካዊ ጥቃቱን አውግዘዋል
ጥቃቱን ተከትሎ የዩናይትድ ስቴትስ የካቶሊክ ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዝዳንት ብጹእ አቡነ ቲሞቲ ብሮሊዮ በሰጡት መግለጫ “ወንድሞቼ ከሆኑት ብጹአን ጳጳሳት ጋር ፖለቲካዊ ይዘት ያለውን ይሄንን ጥቃት እናወግዛለን፣ ለፕሬዚዳንት ትራምፕ፣ ለሞቱት እንዲሁም ለቆሰሉት ሰዎች እንጸልይላቸዋለን፥ እንዲሁም ለፖለቲካዊ አለመግባባቶች መፍትሄ የማይሆነው ይህ ፖለቲካዊ ጥቃት ከሀገራችን እንዲወገድ እንጸልያለን” በማለት ገልጸዋል።
ሊቀ ጳጳስ ብሮሊዮ “ለሀገራችን ሰላም እንድንጸልይ የበጎ ፈቃድ ያላቸው ሰዎች ሁሉ አብረውን እንዲጸልዩ እጠይቃለሁ” ካሉ በኋላ፥ የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እናት እና የአሜሪካ ጠባቂ የሆነችውን የቅድስት ድንግል ማርያም አማላጅነትን ለምነዋል።
ብጹእ አቡነ ዙቢክ ጸሎት እንዲደረግ ጥሪ አቀረቡ
የበትለር ከተማን የሚያካትተው የፒትስበርግ ሃገረስብከት ሊቀ ጳጳስ ብጹእ አቡነ ዴቪድ ዙቢክ “ከአቢያተ ክርስቲያኖቻችን አንዱ በሆነው ቤተክርስቲያናችን በቅርብ ርቀት በሚገኝ ቦታ የተፈጸመውን ጥቃት ዜና ስሰማ ጥልቅ ድንጋጤ ተሰምቶኛል” በማለት ስለሁኔታው ከገለጹ በኋላ፥ “ለሁሉም ጤንነት እና ደህንነት፣ ለፈውስ እና ሰላም፣ እንዲሁም በዓለማችን ላይ ያለው ይህ የአመፃ አየር እንዲያበቃ” ጸሎቶች እንዲደረጉ ጥሪ አቅርበዋል።
ቅድስት መንበር ስጋቷን ገልጻለች
ቅድስት መንበር ጉዳዩን አስመልክታ እሁድ ማለዳ ላይ ባወጣችው መግለጫ “በትላንትናው ዕለት የተፈጸመው ሕዝብንና ዴሞክራሲን ያቆሰለው፣ እንዲሁም ለመከራና ለሞት የዳረገው የጥቃት ትዕይንት” እንዳሳሰባት ከገለጸች በኋላ፥ መግለጫው በመቀጠል “ቅድስት መንበር የአሜሪካ ብጹአን ጳጳሳት የአመጽ ዓላማ ፈጽሞ እንዳይሳካ ለአሜሪካ፣ ለተጎጂዎች እና ለአገሪቱ ሰላም ከሚያቀርቡት ጸሎት ጋር ሁሌም ትተባበራለች” ብሏል።