ፈልግ

የፍልስጤም እና የእስራኤል ጦርነት የፍልስጤም እና የእስራኤል ጦርነት  (AFP or licensors)

የቦምብ ጥቃት ያሰጋቸው የጋዛ ነዋሪዎች አስተማማኝ መሸሸጊያን በመፈለግ ላይ እንደሚገኙ ተነገረ

በደቡብ እና ሰሜን የአገሪቱ ክፍሎች የሚገኙ የጋዛ ነዋሪዎች በፍጥነት መጠለያቸውን ለቀው መውጣታቸውን እና ብዙዎችም ያለ ምንም ንብረት መሰደዳቸው ታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ጋዛ ውስጥ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች የእስራኤልን የቦምብ ጥቃት በመስጋት አስተማማኝ መጠለያን በመፈለግ ላይ እንደሚገኙ ሲነገር፥ አካባቢወን ለቅቀው እንዲወጡ የተሰጠውን ትእዛዝ ተከትሎ በሰሜን እና በደቡብ ጋዛ የሚገኙ አንዳንድ ነዋሪዎች ያለ ምንም ንብረት መኖሪያቸውን ለቅቀው በመሸሽ ላይ እንደሚገኙ ታውቋል። ጋዛ ውስጥ ብዙዎቹ ሲፈናቀሉ ይህ የመጀመሪያቸው አይደለም።

የጋዛ ተፈናቃዮችን እና የጦር ጉዳተኞችን በማገዝ ላይ የሚገኝ የዕርዳታ ማስተባበሪያ ድርጅት “UNWRA” እንዳስታወቀው፥ በጋዛ ሰርጥ ያሉ ሰዎች ቀጣይነት ባለው መፈናቀል እና ለኑሮ ምቹ ባልሆኑ ሁኔታዎች ውስጥ እንደሚገኙ እና ከጊዜ ወደ ጊዜ በተጨናነቁ አካባቢዎች ታጥረው እንደሚገኙ ገልጿል።

“በጋዛ ውስጥ ምንም ዓይነት ደህንነቱ የተጠበቀ ሥፍራ የለም” ያለው የዕርዳታ ማስተባበሪያ ድርጅቱ፥ አካባቢውን ለቅቀው እንዲወጡ የተሰጠውን ትእዛዝ ሰፊውን የጋዛ ሰርጥ እንደሚያካትት እና ተፈናቃዮቹ ወደ ሌላ አካባቢዎች ለመሄድ የሚችሉባቸው አማራጮች ውስን ናቸው” ሲል የዕርዳታ ማስተባበሪያ ድርጅቱ “UNWRA” አስታውቋል።

እርምጃው የጀመረው ሰኞ ዕለት በሺዎች የሚቆጠሩ ፍልስጤማውያን በጋዛ ሰርጥ ደቡባዊ ክፍል በምትገኘው ከተማ ላይ የእስራኤል ጦር አዲስ የቦምብ ጥቃቶችን ከፈጸመ በኋላ ሲሆን፥ ‘በአሸባሪ ድርጅት ላይ የተካሄደ ኦፕሬሽን’ በተባለው የእስራኤል ጥቃት በሺዎች የሚቆጠሩ ፍልስጤማውያን በድንጋጤ ተውጠው ከአካባቢው መሸሻቸው ተነግሯል።

በሃማስ የሚመራው የጋዛ ሰርጥ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር እንደተናገረው፥ በእስራኤል ጦር በተከበበው የፍልስጤም ግዛት ግጭት ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ 39,090 ሰዎች መሞታቸው የሚታወስ ሲሆን፥ ከነዚህም መካከል አብዛኞቹ ሲቪሎች መሆናቸውን አስታውቋል።

በሌላ በኩል በመስከረም 26/2016 ዓ. ም. ሃማስ በእስራኤል ላይ በፈጸመው ጥቃት 1,197 ሰዎች መሞታቸው እና ከእነዚህ መካከልም አብዛኛዎቹ ሲቪሎች መሆናቸው ይታወሳል።

የእስራኤል ጦር እንደገለጸው በመስከረም ሃማስ በፈጸመው ጥቃት 251 ሰዎች መታገታቸው፣ ጋዛ ውስጥ አሁንም 72 ሰዎች ታስረው እንደሚገኙ እና ታፍነው የተገደሉ የሌሎች 44 ሰዎች አስከሬን በፍልስጤም እስላማዊ እንቅስቃሴ ቡድን እጅ እንደሚገኝ ተዘግቧል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከጥቅምት 16/2016 ዓ. ም. ጀምሮ በጋዛ ተኩስ እንዲቆም ጥሪዎችን ሲያቀርቡ መቆየታቸው ሲታወስ፥ እነዚህ ጥሪዎች የዓለም መሪዎች ካቀረቧቸው ጥሪዎች በቁጥር እንደሚበልጡ ታውቋል።

 

27 July 2024, 16:13